በዲሲ ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ መፈንቅለ ቦርድ ያደረገው ቡድን የሆድ ተስካር አወጣ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ውስጥ የምትገኘውን ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ውስጥ ከአራት ወራት በፊት መፈንቅለ ቦርድ በማድረግ ቤተክርስቲያኒቷን በህገ ወጥ መንገድ የተቆጣጠረው ቡድን የደረሰበትን ስኬት አስመልክቶ ለደጋፊዎቹ ግብር ማብላቱን በለቀቀው ቪዲዮ አሳውቋል። ድግሱ ጮማ የተቆረጠበትና የውስኪ፣ የወይን ጠጅና የማር ጠጅ የአልኮል መጠጦች የተንቆረቆሩበት እንደነበርና መፈንቅለ ቦርዱ በተሳካ ሁኔታ በመካሄዱ መወድስ የወረደበት፣የተፎከረበትና የተቅራራበት ነበር። ድግሱ የተካሄደው ሆድ ለመሙላትና ለመሳከር ብቻ እንደነበር በግልጽ የሚታይ ከመሆኑም ሌላ “ግብረ ኃይል” የተባሉት ተሳዳቢዎችና ጋጠወጦች መፈንቅለ ቦርዱን የሚቃወሙትን ምዕመናን ለቅዳሴ በሚመጡበት ጊዜ እያነቁ የሚያስወጡና የሚያዋርዱ የጥፋት አጋፋሪዎች የተመሰገኑበትና የተበረታቱበት መድረክ ነበር።

የድግሱ ዋና አጋፋሪ የነበሩት ቀደም ሲል በሰሩት አስተዳደራዊ ጥፋቶች ከአገልግሎት የተወገዱትና ቤተክርስቲያኒቷ አሁን ለደረሰባት ችግር በኃላፊነት ከሚጠየቁት ግለሰቦች አንዱ የሆኑት ርዕሰ ደብር አብርሃም ሐብተ ስላሴ ነበሩ። እኝህ ሰው አድራሻና ስም የሌለው በራሪ ወረቀት ከአቶ አዲሱ አበበ ጋር በመሆን በምዕመናን መኪና ማቆሚያ ቦታዎችና በቤተክርስቲያኗ ግጽር ግቢ አካባቢ ከስርዓተ ቤተክርስቲያን ውጭ በስውር ሲበትኑ የነበሩ መሆናቸው ይታወቃል። በሆድ ተስካሩ ላይ ርዕሰ ደብር አብርሃም በቢላዎ እየጎመዱ ያወራረዱትን ቁርጥ ስጋ በውስኪ ካንሸራሸሩ በኋላ ባደረጉት ንግግር መፈንቅለ ቦርዱን በስኬት እንዲጠናቀቅ ቁልፍ ሚና የተጫወቱትንና የተቆለፈ በር ሰብረው የገቡትን ኬላ ሰባሪዎች በማመስገን ቫቲካን ውስጥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንን የሚጠብቁት ከስዊዝ መጡ ያሉዋቸውን ልዩ ልብስ ለብሰው ጦር ይዘው ከሚቆሙ ዘበኞችን ሁኔታ ጠቁመው “ግብረ ኃይል” የሚባሉትን የመፈንቅለ ቦርዱን አገልጋዮች አሞግሰዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከካቶሊክ እምነት ጋር  ጥልቀት ያለው ልዩነት ያላትና ደም የተቃባች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን ነገር ለማሳመርም ሆነ በሌላ ምክንያት ሌሎች እህት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት እያሉ ወደ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሻገር ከአንድ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ካህን የሚጠበቅ አይደለም። በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት ጊዜ አገራችን ውስጥ የገቡት ፖርቱጋሎች የካቶሊክን ሐይማኖት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖትን አጥፍተው ለማሰራጨት ያደረጉትን ጫና መቃወም በሽዎች የሚቆጠሩ የተዋህዶ አማኞች መሰዋታቸው የሚዘነጋ አይደለም። ካቶሊኮች ከዚህም በላይ “ፀጋና ቅባት” በማለት የኦርቶዶክስን እምነት ሲያጠቁና ሲፈታተኑ መኖራቸውን ታሪክ ይመሰክራል። ይህን በቤተክርስቲያኒቷና በአጠቃላይም በአገሪቷ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈን ታሪክን እንደገና በማደስ እንዲሁም ከአሁን በፊትም በደረሱት መጽሃፍም ላይ ጭምር ከካቶሊክ እምነት አየቀላወጡ ባመጡት ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጋር በተጣረሰ ስብከታቸው ተለይተው የሚታወቁት ርዕሰ ደብር አብርሃም ቫቲካን ውስጥ የሚገኙትን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠባቂዎችን ከመፈንቅለ ቦርዱ አጋፋሪዎች ጋር እያመሳሰሉ በውስኪ ትንፋሻቸው መወድስ አሰምተዋል።

የአልኮል መጠጦችን በቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ ማቅረብ የሚያስከትለው የስነ-ምግባር ጉድለት ተጠያቂነት እንዳለ ሆኖ ከህግም ጋር የሚያላትም ድርጊት ነው። በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ውስጥ የአልኮል መጠጥ ፈቃድ ሳይኖር ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ መጠጥ ማቅረብ ቤተክርስቲያኗን በኃላፊነት የሚያስጠይቅና የህግ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል ድርጊት ነው። በቪዲዮ ላይ እንደሚታየው ከደረቅ አልኮል መጠጥ አንስቶ እስከ ጠጅ ድረስ በይፋ ሲቀዳና በታላቅ ልግስና ሲታደል ህጋዊነቱን የሚያረጋግጥ ፍቃድ ለመኖሩ የተገለጸ ነገር የለም። በዚሁ ዝግጅት ላይ ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ኃይሌ፣ ቀሲስ ኃይሉ ዘለቀ፣ ቀሲስ ኤሊያስ መዐዛና ሌሎችም ካህናት የውስኪ ጠርሙስ ፊት ለፊታቸው ተሹሞ በታዳሚነት ሲስተናገዱ ይታያሉ። እንዲሁም ቤተክርስቲያኒቷን መስርቻለሁ እያለ ሁል ጊዜ የሚመጻደቀው የወያኔው ተላላኪ የንጉሴ ወልደማርያም ባልደረባ የሆነው ከሃሊ ወንዳፈረውም ሲቀባጥር ይታያል። የመፈንቅለ ቦርዱ ዋና አቀናባሪ ታደለ ገብረ ወልድም ታድሟል። ከአሁን በፊት በቤተክርስቲያን ውስጥ የአልኮል መጠጦችን ካህናት ሲጨልጡ ያልተመለከቱ ምዕመናን ይህንን ቪዲዮ ከተመለከቱ በኋላ፣ ለካስ እነዚህ ካህናት ለሆዳቸው ኖራል ምዕመናንን የበጠበጡትና ያመሱት በማለት በመረረ ሃዘን ሲናገሩ መደመጣቸው ተጠቁሟል።

በገዛ እጃቸው በለቀቁት ቪዲዮ ገበናቸው መጋለጡ የተሰማቸው የመፈቅለ ቦርዱ አጋፋሪዎች ቪዲዮውን ከዕያታ አውርደውት ነበር። ሆኖም ከመረጃ ማህደራችን ያስቀመጥነውን የቪዲዮውን ቅጅ እንደገና ለቀነዋል። “ቀድመሽም ባልዘፈንሽ፣ ከዘፈንሽም ባላፈርሽ” እንደሚባለው በኩራትና በጉራ የለቀቁት ቪዲዮ የሚያዋርዳቸውና ለትዝብትም የሚዳርጋቸው መሆኑንና ፈቃድ ሳይኖራቸው የተራጩበት የአልኮል መጠጥ ከህግ አኳያም የሚያስከትልባቸውን ችግሮች በመፍራት የለቀቁትን ቪዲዮ አውርደዋል። ለመርጃ ክፍላችን በደረሰን ጥቆማ መሠረት መፈንቅለ ቦርዱን ያደረገው ቡድን ቤተክርስቲያኗን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ በየጊዜው የጥሬ ስጋና የመጠጥ ፈንጠዝያዎችን በቤተክርስቲያኗ ቅጽር ግቢ ውስጥ ሲያካሂድ እንደነበረና ሰው ይታዘበናል የሚል ይሉኝታ የሌላቸው አይን አውጣዎችና ጋጠወጦች መሆናቸውን ማሳየታቸው ተገልጾልናል። እራሱ አስረጅ የሆነውን ቪዲዮ እዚህ ላይ በመጫን ይመልከቱ።

 

https://www.youtube.com/watch?v=mQwchpe0dvM