የክቡር ሚኒስትሩ ከብስጩ ሚስታቸው ከዲያስፖራው ከሹፌራቸው እና ከአማካሪያቸው ጋር ተወያዩ::


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ብርሃነ ገብረክርስቶስ

ብርሃነ ገብረክርስቶስ

የክቡር ሚኒስትሩ ሚስት ተበሳጭተዋል

– ምን ሆነሻል?
– ምን ሆንኩ?
– ፊትሽ የጠቋቆረው::
– ለምን አይጠቁር?
– እኮ ምን ሆነሻል?
– ተያዘ::
– ያ ሱቅ?
– ክፈል ክፈል ብዬ ስንቴ ነው የነገርኩህ?
– እና ሱቁ ተያዘ?
– ሱቁማ ቢሆን የተሻለ ነበር::
– እና ሱቁ አልተያዘም?
– እኔ ስለሱቁ አይደለም የማወራህ::
– እና ምኑ ነው ተያዘ የምትይው?
– አዳራሹ ነዋ::
– የምን አዳራሽ?
– የእህቴ ልጅ ሠርግ መድረሱን ረሳኸው?
– ደረሰ እንዴ?
– አንተ ምን ሐሳብ አለብህ?
– የማላስበውን ብጠይቂኝ ይሻላል?
– እኮ ምን ታስባለህ?
– ስለዚች አገር ነዋ::
– ይቺን አገር ስለመቦጥቦጥ?
– ይህቺን አገር ስለማልማት ነው እንጂ::
– ራሴን ስለማልማት ነው ያልከኝ?
– እውነትም ተናደሻል ማለት ነው?
– እንዴት አልናደድ?
– አታስቢ::
– ጤንነትህን ግን መጠራጠር
ጀምሬያለሁ::
– ለምንድን ነው የምትጠራጠሪው?
– የሠርጉ ወረቀት እኮ ተበትኗል::
– ይበተና ምን ችግር አለው?
– ወረቀቱ ላይ የተጻፈው አዳራሽ ለሌላ
ተከራየ እያልኩህ እኮ ነው::
– ያ ሆቴል አይደል እንዴ?
– አዎን ነው::
– ባለሆቴሉ እኮ ልማታዊ ነው::
– ቢሆንስ ታዲያ?
– በአንድ ስልክ ነዋ የምጨርሰው::
– ምኑን?
– የእኛ ሠርግ እዛ እንዲሆን::
– እኛ እኮ ስላልከፈልን ነው ለሌላ ሠርግ
ያከራዩት::
– አንድ ነገር አትርሺ::
– ምን?
– የእኛ ሠርግ ልማታዊ ነው::
– እ…
– እኛ የተከራየነውን አዳራሽ ለመከራየት
የፈለጉት ደግሞ…
– ምን?
– ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው::
– እኛ እኮ ስላልከፈለን ነው እነሱ
የከፈሉት::
– አየሽ ኪራይ ሰብሳቢዎች መሆናቸውን
የምታውቂው ቀድመው ሒሳብ
በመክፈላቸው ነው::
– አንተ እውነትም ለይቶልሃል::
– ለማንኛውም አታስቢ::
– ለምን አላስብ?
– እኔ እጨርሰዋለሁ::
– እኮ እንዴት?
– ሆቴሉን ተቆጣጥሬዋለሁ::
– እ…
– 100 ፐርሰንት::
[አንድ ዳያስፖራ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለ]
– ክቡር ሚኒስትር አገሪቱ እንዴት ናት?
– እየተመነደገች ነው::
– ኧረ የምሰማው ነገር አሳስቦኛል::
– ምን ሰማህ?
– ይኸው ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ
ተከስቷል::
– እኛ ምን እናድርግ ታዲያ?
– ሐዋሳ ላይም መሬት መንቀጥቀጥ
እንደነበር ሰምቻለሁ::
– ይህ እንግዲህ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው::
– ሰሞኑን ደግሞ በማኅበራዊ ድረ ገጽ
የምሰማው ጉድ ነው::
– በየማኅበር ቤቱ አለመሄድ ነዋ::
– ኧረ እኔ ፌስቡክን ማለቴ ነው::
– ፌስቡክ እኮ የወሬኞችና የሥራ ፈቶች
ነው::
– አይ ክቡር ሚኒስትር አሁን አሁን እኮ
ጥሩ የመረጃ ምንጭ ሆኗል::
– ለመሆኑ ምን ሰምተህ ነው?
– ይኸው ድሬዳዋ ዓሳ ዘነበ እየተባለ ነው::
– ለምን ይመስልሃል የዓሳ ሚኒስቴር
ያቋቋምነው?
– እ…
– ይኼ እንደሚመጣ ቀድመን አውቀን
ነበር::
– እየቀለዱ ነው?
– የምን ቀልድ ነው? በዕድገት ቀልድ
የለም::
– የምን ዕድገት?
– ይኼ የህዳሴያችንና የዕድገታችን
ውጤት ነው::
– እንዴት ሆኖ?
– ገና ወርቅ ይዘንባል::
– ወርቃችንማ ተጠርጐ እየተወሰደ ነው::
– ምን አልክ አንተ?
– ሰምተዋል::
– ለማንኛውም ይኼ ዜና ሊያስደስትህ
ይገባ ነበር::
– የእግዚአብሔር ቁጣ ነው እኮ ይኼ::
– ይኼማ ቁጣ ሳይሆን ደስታ ነው እንጂ::
– እንዴት ሆኖ?
– መጽሐፍ ቅዱስ አታነብም እንዴ?
– አነባለሁ ኧረ::
– ታዲያ እግዚአብሔር ለእስራኤሎች
በየቀኑ መና ያዘንብላቸው ነበር እኮ::
– አዎን እሱን አውቃለሁ::
– መና የሚያዘንብላቸው ስለሚወዳቸው
ነበር::
– ልክ ነው::
– ይኸው በእኛም ዕድገት በጣም
በመገረሙ ዓሳ ማዝነብ ጀመረ::
– እና እግዚአብሔር ዓሳ ያዘነበው
በዕድገቱ ተገርሞ ነው::
– በእኛ ዕድገት ብዙ ነገር ይዘንባል::
– ብዙ ነገር መዝነቡንማ አውቃለሁ::
– ማለት?
– የወጣቶች ሊግ፣ የሴቶች ሊግ…
– እ…
– የወጣቶች ፎረም፣ የሴቶች ፎረም፣
የባለሀብቶች ፎረም…
– እያሽሟጠጥክ ነው::
– በእናንተ ጊዜ ያዘነባችኋቸውን ነገሮች
እየነገርኩዎት ነው እንጂ::
– ወሬኛ ነገር ነህ::
– ይኸው ሰሞኑን ደግሞ ሌላ ነገር
ማዝነቡን ተያይዛችሁታል::
– ምን?
– ደላላ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]
– ስብሰባው አለቀ አይደል ክቡር
ሚኒስትር?
– የምኑ ስብሰባ?
– የመሪዎቹ ስብሰባ::
– ተሸኙ እኮ ወደ አገራቸው::
– መቼም ጥሩ መዝናኛ ነው::
– ምኑ ነው መዝናኛው?
– ስብሰባው ነዋ::
– እንዴት ማለት?
– ያው በዓመት አንዴ ለሳምንት በደንብ
ተዝናንተው ይሄዳሉ::
– አትሳሳት::
– እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
– ሲጀመር ስብሰባው በዓመት አንዴ
ሳይሆን ሁለቴ ነው::
– ያው ሁሌ በዚህ ሰሞን ነው የሚመጡት
ብዬ ነው::
– ሁለተኛው ደግሞ አንዱ የአፍሪካ አገር
ነዋ የሚካሄደው::
– እናንተም በተራችሁ እንድትዝናኑ?
– ምን ይላል ይኼ? መዝናናት ሳይሆን
ሥራ ነው::
– እሱን እንኳን ተውት::
– እንዴት ማለት?
– ሰሞኑን አይደል እንዴ ጉዱን
ያወቅኩት?
– አልገባኝም::
– ለሳምንት ዕረፍት የወጣሁት የአንዱ
ዲፕሎማት ሾፌር ለመሆን ነበር::
– እሺ::
– በቃ የአዲስ አበባ ጭፈራ ቤት አንድ
አልቀረኝም::
– እ…
– ክቡር ሚኒስትር አዲስ አበባን
አውቃታለሁ ብለው ያስባሉ አይደል?
– በሚገባ እንጂ::
– እኔ ግን እንደማያውቋት
እነግርዎታለሁ::
– እንዴት ማለት?
– ክቡር ሚኒስትሩ ማሳጅ ቤቱ ቢሉ፣
ሺሻ ቤቱ ቢሉ፣ ገስት ሃውሱ ቢሉ ኧረ
ስንቱ::
– ምንድን ነው የምታወራው?
– ብቻ ይኼ የስብሰባ ተሳታፊ ነኝ የሚል
ሁሉ የሚገኘው እኮ እዛ ነው::
– እ…
– እንዲያውም አንዳንዴ የስብሰባው ቦታ
የተቀየረ ነው የሚመስለው::
– ማለት?
– በቃ ሁሉም ተሳታፊዎች ያሉት
በየማሳጅ ቤቱ፣ በየሺሻ ቤቱና በየጭፈራ
ቤቱ ነዋ::
– ወይ ጣጣ::
– ለማንኛውም እርስዎም ሲሄዱ ይዘውኝ
ቢሄዱ ደስ ይለኛል::
– የት?
– ስብሰባ ሲሄዱ::
– ሞላጫ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
– መቼም የሙጋቤን ንግግር
ተከታትለኸዋል?
– አዎን ክቡር ሚኒስትር::
– ልክ ልካቸውን እኮ ነው የነገረልኝ::
– እነ ማንን?
– ኒዮሊብራሎቹን ነዋ::
– እሱ እኮ ሁሌም ነው የሚናገረው::
– ከእንግዲህ ግን ቀልድ የለም ብሏል::
– የምን ቀልድ?
– የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር
ቤቱ ውስጥ መግባት አለብን::
– እንዲህ በቀላሉ::
– እኮ አሁን መዘጋጀት አለብን::
– ለምኑ?
– ምክር ቤቱ እኛ እንድንገባ ኒዮሊብራሎቹ
አይፈልጉም::
– እሱማ የታወቀ ነው::
– ስለዚህ በራሳችን እናቋቁማለን::
– ምንድን ነው የምናቋቁመው?
– የራሳችንን የተባበሩት መንግሥታት::
– እየቀለዱ ነው?
– በዚህ ቀልድ የለም::
– እና ምን ይደረግ?
– ኮሚቴ ይቋቋም::
– የምን ኮሚቴ?
– የራሳችንን የተባበሩት መንግሥታት
የሚያቋቁም ኮሚቴ::
– ኮሚቴ ግን አልበዛም?
– አየህ ኮሚቴ ሲኖር ግልጽነትና
ተጠያቂነት ይኖራል::
– ስለዚህ ኮሚቴው እንዴት ይዋቀር?
– ያው እንደተለመደው ከሴቶች ፎረም፣
ከወጣቶች ፎረም፣ ከነጋዴዎች ፎረም
… የተውጣጡ ይሁኑ::
– የብሔር ተዋፅኦስ?
– እሱማ ጥያቄ የሌለው ጉዳይ ነው::
– የኮሚቴው ሥራ ምንድን ነው
የሚሆነው?
– ኮሚቴው በአዲሰ አበባ ያሉ
ዲፕሎማቶችን የማሳመን ሥራ
ይሠራል::
– እሺ ክቡር ሚኒስትር::
– ይህን ለማድረግ ደግሞ ዲፕሎማቶችን
እናደራጃቸዋለን::
– በምን?
– በአንድ ለአምስት!