አሁን ለነ ዶር ብርሃኑ የምጠይቀው …… – ግርማ ካሳ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
አሁን ለነ ዶር ብርሃኑ የምጠይቀው …… – ግርማ ካሳ
አንዳንንድ ወገኖች በግንቦት ሰባቶች ላይ የግል ችግር ያለብኝ ይመስላቸዋል። አይደለም። ከነርሱ ጋር የአላማ ልዩነት የለኝም። ልዩነት ያለኝ የስትራቴጂ ልዩነት ነው። ግንቦት ሰባት ዉስጥ ያሉ ወገኖች ዳይናሚክ የሆኑ ትልቅ ፖቴንሻል ያላቸው እንደሆነ አውቃለሁ። ሊቀምንበሩ ዶር ብርሃኑ ነጋ፣ በቅንጅት ጊዜ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ መሪ ናቸው። ብዙዎቻችንን ኢንስፓየር ያደረጉ። ሆኖም በግንቦት ሰባት አመራርነት የወሰዱት ስትራቴጂ ግን ያላቸዉን ፖቴንሻል እንዲጠቀሙበት የረዳቸው አይመስለኝም። ኢትዮጵያዉያንን በሙሉ እንደ መሪ አስተባብረው፣ በሰላማዊው ትግል ትልቅ ንቅናቄ የመፍጠር አቅም የነበራቸው መሪ፣ ከአረመኔው ኢሳያስ ጋር በመቆራኘት ከብዙ ደጋፊዎቻቸው ጋር ተጋጩ። ራሳቸውን አሳነሱ። ሆኖም ዶር ብርሃኑ ያሉ ካለፉት ስህተቶቻቸው ተምረው፣ በጥበብ ከተንቀሳቀሱ የቅንጅቱ ዶር ብርሃኑ ነጋ የማይመለሱበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
“ግልጽ ደብዳቤ ለግንቦት ሰባት መሪዎችና አባላት” በሚል ርእስ ከሁለት አመታት በፊት አንጽ ጽሁፍ ለአንባቢያን አስንብቤ ነበር። ያኔ የጻፍኩት ጽሁፍ አሁን ያለዉን ሁኔታ የሚያንጸባርቅ ነው። በኤርትራ በኩል የሚደረገው ትግል ዉጤት እንደማያመጣና ስህተት እንደሆነ ነበር መረጃዎችን በግልጽ በማስቀመጥ ለማሳየት የሞከርኩት።
ይኸው ዶር ብርሃኑ ራሳቸው ወደ ስንት ወራት ነው፣ እዚያ ከርመው መጡ። እንደ ፕሮፖጋንዳ ከሚነገረው ዉጭ በተጨባጭ በትጥቅ ትግሉ ዘርፍ የታየ ውጤት የለም። አንድ ነጻ የወጣ ቀበሌ ወይንም ወረዳ እንዳለ አልሰማንም። ብዙዎች ሕይወታቸዉን አደጋ ላይ በመጣል ወደ ኤርትራ ሄደዋል። ዉትድርና እየሰለጠኑ እንደሆነ፣ ተመረቁ ሲባልም እንሰማለን። የተለያዩ ፎቶዎችና ቪዲዮዎችንም እናያለን። ግን በተግባርና በተጨባጭ ግን የታየ ነገር የለም።
ይህ የሆነበት ምክንያት በግንቦት ሰባቶች ዘንድ ቁርጠኝነት ስለሌላ ሳይሆን፣ ከኤርትራ ተነስቶ ዉጊያ ማድርግ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው። አንደኛ መዋጋት እንደ ማዉራት ቀላል አይደለም። ሁለተኛ አካባቢው በጣም ሚሊተራይዝድ የሆነ ነው። እጅግ በጣም ብዙ፣ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁ፣ የአየር ኃይል የበላይነት ያላቸው የወያኔ ታጣቂዎች በዚያ አሉ። የአሜሪካን ሳተላይት መረጃም ይሰጣቸዋል። በዚህ ምክንያት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ወታደሮች ለማስገባት በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ሶስተኛ ሱዳን የወያኔዎች አጋር ናት። አራተኛ ሻእቢያ ዉስጥ የወያኔ ሰዎች አሉ፤ መረጃ የሚያቀብሉ። አንዳርጋቸውን ያስያዙት እነዚሁ ሻእቢያ ዉስጥ ያሉ ለወያኔ የሚሰሩት ናችው። አምስተኛና ዋናው ሻእቢያ በመርህ ደረጃ ከወያኔዎች ጋር ዉጊያ አይፈለግም። ዉጊያ ከተጀመረ፣ ወያኔዎች አስመራ ሊገቡ እንደሚችሉ ያውቃል። ሻእቢያ በሕዝቡ እጅግ በጣም የተጠላ ነው።በመሆኑም ብዙ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ከወያኔ ጎን ናቸው። በመሆኑም ወያኔዎች የኤርትራ ተቃዋሚዎችን ይዘው ኢሳያስን በቀላሉ የማስወገድ አቅም አላቸው። በርግጥም በኤርትራ በኩል ትግል ማድረግ እጅግ በጣም ከባድና ዉስብስብ ነው።
በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ህዝቡ ነፍጥ አንስቶ የተነሳበት ሁኔታ አለ። በወልቃይት ጠገዴ፣ በአርማጭሆ፣ ጭላጋ በመሳሰሉት ቦታዎች በቴፒ ፣ በጋምቤላ ..ግፍና ጭቆና የመረረው ወገናችን የትጥቅ ትግል የጀመረበት ሁኔታ አለ። በነዚህ ሁሉ ዉስጥ ግን ግንቦት ሰባት ዕጁ የለበትም። ግንቦት ሰባት ምንም አይነት የተረጋገጠ የዉትድርና እንቅስቃሴ ያደረገበት ሁኔታ የለም።
ለዚህም ነበር ግንቦት ሰባቶች በተቸላ መጠን ትኩረታቸው ፣ ላለፉት 2 ወራት በኦሮሚያ እንደታየው፣ በሰላማዊ የእምቢተኝንት እንቅስቃሴ ላይ እንዲሆን ስንመክር የነበረው።
“ወቅቱ ትብብርን ይጠይቃል። በተቃዋሚዉ ጎራ ያለው ወገን ሁሉ በአንድነት ይሰባሰብ ዘንድ፣ እናንተም የተቃዋሚዉ አንዱ አካል እንደመሆናችሁ፣ እናንተ ዘንድ ያሉ፣ መሰባሰብ እንዳይኖር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን፣ ትመረምሩና ታስተካክሉ ዘንድ ይሄን ጽፊያልሁ። ክስ ሳይሆን፣ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ምክር አዘል አስተያየት በማቅረብ፣ ቻሌንጅ ላደርጋቹህ እሞክራለሁ።” ስል ነበር ከሁለት አመታት በፊት የጻፍኩላቸው።
“ይሄን መረዳት አለባችሁ፣ ነጻነታችንን ኢሳያስ አፈወርቂ አይሰጠንም። ጠዋትና ማታ አገዛዙን ስለረገምን ለዉጥ አናመጣም። በአሁኑ ወቅት ብቸኛው አማራጭ እኛው እራሳችን የምናደርገዉ የተባበረ ሰላማዊ ትግል ነዉ። ኢትዮጵያዉያን በአንድ ላይ ተባብረን፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ ጥቂቶች የዘረጉትን ቀንበር መስበር እንችላለን። እባካችሁ የኢትዮጵያን ሕዝብ ኃይል አሳንሳችሁ አትመልከቱ። ከሻእቢያን ጥገኝነት ዉጡ። ወደ ቀደሞዉ ወደ «ቅንጅት» መንፈስ ተመለሱ። ያኔ በዘጠና ሰባት የጠበቅነዉን ያላገኘነው፣ በቂ ድርጅታዊ ሥራ ስላተሰራና በአመራር አባላት መካከል መከፋፈል ስለተፈጠረ፣ ሕዝቡ በአንድ ላይ በተደራጀት መልኩ፣ በሁሉም ክልሎች ማንቀሳስቀስ ስላልተቻለ እንጂ፣ የሰላማዊ ትግል ስላልሰራ ወይን የኢትዮጵያ ሕዝብ አቅም ስለደከመ አልነበረም። ካለፈዉ ትምህርት በመዉሰድ፣ ጥንቃቄ በተሞላበት፣ በክልሎች ሁሉ መረብን በመዘርጋት ፣ አቅማችንን፣ ገንዘባችንን በሙሉ አንድ ላይ በማሰባሰብ፣ የሚደረግ ሕዝባዊ ፣ ሰላማዊ የእምቢተኝነት ዘመቻ በርግጥ ዉጤት ያመጣል።” ነበር ያልኳቸው።
“ሸንጎ፣ የብሄራዊ ሽግግር ምክር ቤት፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ የመሳሰሉ በርካታ ደርጅቶች ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ተማምነዉ፣ አገር ቤት ለሚደረገዉ ሰላማዊ ትግል አጋርነታቸውን እየገለጹ ነዉ። የእናንተ ድርጅት፣ ግንቦት ሰባት፣ ከሻእቢያ ጋር ያለዉን ግንኙነት በአስቸኳይ በጥሶ፣ ከነዚህ ድርጅትች ጋር አብሮ ለመስራት ይሞክር። እዚህ ላይ አበቃለሁ። የሚሰማ ጆሮ ካለ እንግዲህ ይሰማል።” ስልም በድርጅቶ መካክከል መሰባሰብ እንዲኖር ጠይቄ ነበር።
ከሻእቢያ ጋር ይላቸውን ግንኙነት ፣ ከሁለት አመታት በፍት እንደጻፍኩት፣ በቀላሉ ሊበጥሱት አይችሉም። ቢበጥሱት ደስ ይለኛል፤ ግን ፕራክቲካልም መሆን አለብኝ። ሆኖም ሁሉንም ነገር አንድ ጆንያ ዉስጥ መክተት የለባቸውም። በኤርትራ በኩል እናደርጋለን የሚሉት ያ የነርሱ ጉዳይ ነው፤ ግን በሰላማዊ ትግል እናምናለን ስለሚሉም፣ በተቻለ መጠን በሰላማዊ ትግሉ ረገድ፣ ከሌሎች ጋር በአጋርነት ቢሰሩ በጣም ጥሩ ነው የሚሆነው።
አሁን ለነ ዶር ብርሃኑ የምጠይቀው፣ ቢያንስ መግባባት መፍጠር ከሚቻልባቸው እንደ ኦዴፍ፣ ሸንጎ፣ የሽግግር ምክር ቤቱ …ካሉ ደርጅቶች ጋር አስቸኳይ የሆነ፣ ትግሉን የሚያቀናጅ ግብረኃይል እንዲቋቋም ነው። አቅም፣ የመሪነትና የማስባሰብ ችሎታው እንዳላቸው አዉቃለሁ። ይሄንን ሳያደርጉ፣ ወደ አሰመራ ከተመለሱ ግን ( የሚመለሱ ከሆነ) ትልቅ እድል አመለጠ ማለት ነው። ግንቦት ሰባት ከተለያዩ ደርጅቶች ጋር እየተወየ እንደሆን እርሳቸውም አቶ ንአመን ዘለቀም በይፋ ገልጸዉልናል። እንግዲህ በዚህ ረገድ ቸር ወሬ ያሰማን።