ማኅበረ ቅዱሳን ለቅዱስ ፓትርያርኩ መሠረተ ቢስ ደብዳቤ መልስ ሰጠ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ማኅበረ ቅዱሳን ለቅዱስ ፓትርያርኩ መሠረተ ቢስ ደብዳቤ መልስ ሰጠ
(ማኅቶት ዘተዋሕዶ)ማኅበረ ቅዱሳን ብፁዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ፓትያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጥር 16/2008 ዓ.ም ለሦስቱ ኮሌጆች ማኅበሩን አስመልክተው ለጻፉት መሠረት ቢስ ደብዳቤ መልስ ሰጠ።
ማኅበረ ቅዱሳን ለቅዱስ ፓትርያርኩ ጥር 24/2008 ዓ.ም በቁጥር ማቅሥአመ/239/02/ለ/08 በጻፈው ደብዳቤ ቅዱስነታቸው በቁጥር ል/ጽ/179/338/2008 ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅና ለቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የጻፉት ደብዳቤ ፍጹም እውነትነት በሌለው መረጃ ላይ ተመርኩዞ የተጻፈ ነው በማለት መልስ ሰጥቷል። በ12 ገጾች ለፓትርያርኩ በሰጠው መልስ ማኅበሩ በፓትርያርኩ ደብዳቤ የሰፈረው ሃሳብ እንደማይገልጠውና በተከሰሰበት ጉዳይም በግላባጭ እንኳ እንዲያውቅ አለመደረጉን አስረድቷል።
“የደብዳቤው ዓላማና ተልእኮም ምን እንደ ሆነ ለመገመት አስቸግሮናል” ያለው የማኅበረ ቅዱሳን ደብዳቤ ፓትርያርኩ በጻፉትና ለኮሌጆቹ ባስተላለፉት መመርያ ውስጥ ላነሧቸውና ማኅበሩን ለኰነኑባቸው ነጥቦች ዝርዝር መልስ ሰጥቷል። በፓትርያርኩና በማኅበሩ መካከል የተፈጠረውን ክፍተት እንደ ልጅነት ቀርቦ በመነጋገር ለመፍታት በማሰብ የውይይት ቀነ ቀጠሮ እንዲያዝለት ስድስት ያኽል ደብዳቤዎችን ጽፎላቸው ፓትርያርኩ ለደብዳቤዎቹና ማኅበሩ ብዥታዎችን በውይይት ለማጥፋት ላደረገው ጥረት ትኩረት የነፈጉት ሆኖ ሳለ በደብዳቤያቸው ማኅበሩ አልታዘዝም ባይ እንደ ሆነ አድርገው ማቅረባቸው የሚያሳዝን መሆኑን አመልክቷል። ማኅበሩን ለማነጋገር ጊዜ ያጠራቸው ፓትርያርክ የማኅበሩን ከሳሾች በየጊዜው ተቀብለው መረጃ ቢስ ውንጀላቸውን ለመስማት ጊዜ መስጠታቸው የፓትርያርኩን ፍትሃዊነት እጅጉን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑንም ተቅሷል።
ፓትርያርኩ ለመንፈሳዊ ኮሌጆቹ በደብዳቤ ባስተላለፉት መመርያ “ጥቅሙና ጉዳቱ በሚገባ ሳይጠና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር የሚያስከትለው የሃይማኖትና የሥርዓት ተፋልሶ ሳይፈተሽ በአንድ ወቅት ራሱ አርቅቆና አዘጋጅቶ በቀረበው ደምብ በቅዱስ ሲኖዶስ የተፈቀደልኝ ሕጋዊ ማኅበር ነኝ ይላል” በማለት ያሰፈሩት ሃሳብ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔና አሠራር የተቃረነ እንደ ሆነ የገለጠው ማኅበረ ቅዱሳን ፓትርያርኩ እንደ ጻፉት ሳይሆን “በ1992 ዓ.ም በቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በኩል በዝርዝር የሚያጠኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩት ኮሚቴ ታይቶና ተመርምሮ የጸደቀነት ደንብ፣ እንዲሁም በ1994 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ደረጃ ቀርቦ የታየ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩት የተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትና የሕግ ባለ ሙያዎች የተሳተፉበት ከ6 ወራት በላይ የፈጀ ጥናት የተደረገበት” መተዳደርያ ደንብ እንዳለው አስረድቷል። በ2004 ዓ.ም የማኅበሩን የአገልግሎት አድማስ መስፋትና በወቅቱ ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ ኃላፊዎች ጋር የነበረውን አለመግባባት ከግምት ውስጥ በማስገባት የበለጠ ሊያሠራው የሚችል ደንብ እንዲኖረው በማሰብ ቅዱስ ሲኖዶስ ራሳቸው ፓትርያርኩ ጭምር በተገኙበት ደንቡን የሚያሰሻሽል ኮሚቴ መሠየሙን የጠቆመው የማኅበሩ ደብዳቤ አጥኚ ኮሚቴው አጠናቅቆ ያቀረበውን ደንብ በየትኛውም አሠራር በሌለው መልኩ አልቀበልም በማለት የደንቡን መሻሻል ሆን ብለው ፓትርያርኩ ራሳቸው እንዳዘገዩት አስረድቷል።
የቤተ ክርስቲያኒቷን እምነት፣ ሥርዓትና ቀኖና ለመበረዝ የሚተጉ ተሐድሶ መናፍቃን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ማኅበሩን የሚከሱባቸው ነጥቦች በፓትርያርኩ ደብዳቤ ውስጥ በአጭር በአጭሩ ተጠቅሰው ማየቱ እንዳሳዘነው ማኅበረ ቅዱሳን በደብዳቤው የገለጠ ሲሆን አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችም የተሐድሶዎች ሃሳብ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ውስጥ መጠቀስ ሁለት አንድምታዎች ሊኖሩት እንደሚችል ያስረዳሉ። አስተያየት ሰጪዎቹ ወይ የፓትርያርኩን ደብዳቤ ጽፈው ያስፈረሟቸው የተሐድሶ መናፍቃን አባላት ወይም ፓትርያርኩ ራሳቸው የተሐድሶ መናፍቃንን ሐሳብ ይጋሩ ይሆናል ብለዋል።
(ዜና ዝግጅት ፦በስምዐ ኮነ)
ማኅበረ ቅዱሳን ለቅዱስ ፓትርያርኩ ደብዳቤ የሰጠውን ምላሽ ሙሉ ሃሳብ ለመረዳት ከዚህ በታች ያያዝነውን ሙሉውን ደብዳቤ ይመልከቱ።
Source : http://orthodoxt.zetewahedo.org/2016/02/blog-post_98.html?spref
Posted by ማኅቶት ዘተዋሕዶ