የአዲስ አበባ ህዝብ ለምን ተቃውሞ አላሰማም (ኤርሚያስ ቶኩማ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የአዲስ አበባ ህዝብ ለምን ተቃውሞ አላሰማም
ይህ ጥያቄ ሰሞኑን በተደጋጋሚ እዚህ ፌስቡክ ላይ ሲመላለስ እያየሁ ነው የአዲስ አበባ ልጅ እንደመሆኔ ጉዳዩ ስቦኝ የተወሰኑትን ፅሁፎች አነበብኩኝ አንዳንዶቹ በጭፍን የአዲስ አበባን ህዝብ ሲያጥላሉ የተወሰኑት ደግሞ የአዲስ አበባ ህዝብ ለምን አልተነሳም ሲሉ ይጠይቃሉ መቼ የአዲስ አበባ ህዝብ እንደተኛና ኢህአዴግን ከመቃወም እንዳረፈ ሊገባኝ አልቻለም ይህ ህዝብ ነው ኢህአዴግ በትረ ሥልጣኑን ከጨበጠበት ቀን ጀምሮ ለኢህአዴግ የእግር እሳት ሆኖ የቆየው አዎ ይህ ህዝብ እስከ 1997 ድረስ በየአደባባዩ ከጥይት ጋር ሲታገል ነበር አሁንስ? መልስ አለኝ
“የአዲስ አበባ ህዝብ የሚባል አለ ወይ?
ይህ ነው ጥያቄው እውን በአሁኑ ሰአት የአዲስ አበባ ህዝብ የሚባል አለ ወይ? ለዚህ ጥያቄ መልስ ካገኘን በኦሮሚያ ንፁሃን ዜጎች በአደባባይ ሲገደሉ የአዲስ አበባ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ለምን ድምፁን እንዳላሰማ በደምሳሳውም ባይሆን መረዳት እንችላለን ብዬ አስባለሁ
በአንድ ወቅት የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለው አንድ ከክፍለ ሀገር የመጣ የክፍል ጓደኛዬ ቦሌን ካላስጎበኘኸኝ ብሎ ቦሌን ለማስጎብኘት ይዤው እሄዳለሁ ቦሌን እስከ ቺቺንያ ካስጎበኘሁት በዃላ ተገርሞ እንዲህ ሲል ጠየቀኝ “የቦሌና የሀያ ሁለት ልጆች ቤታቸው የት ነው?” ይህንን የጠየቀኝ የቦሌ ልጆችን አጥቶ በአንፃሩ ቦሌና ሐያ ሁለት የሕወሐት መሪዎች ቤተሰቦች መኖሪያ መሆኗን አይቶ ነው እውነት ነው ሀያ ሁለት የአዲስ አበባ ልጆች መሆኗ አቁሞ በሕወሐት ሰዎች ተወራ ትንሿ አድዋ እስከመባል ደርሳለች ሀያ ሁለት ላይ በአሁኑ ሰአት የአዲስ አበባ ልጅ መፈለግ ኦሮምኛ ተናጋሪ ባለሥልጣን አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ላይ የመፈለግን ያህል ከባድ ነው ሌላውም ሰፈር እንደዛው ነው አራት ኪሎ ፈርሶ በስፍራው የሚኖሩ የአዲስ አበባ ሕዝቦች የት እንደገቡ አይታወቅም በአንፃሩ አራት ኪሎና አካባቢዋ በማን እንደተወረረ ሀገር ቤት የሚገኝ ወዳጅ ዘመድ ጋር ደውሎ መጠየቅ በቂ ነው።
የአዲስ አበባ ህዝብ የሚያወራለት አጥቶ ነው እንጂ ከተማውን ተቀምቷል አብዛኛው ተሰዷል የተወሰነው በኢሣያስ አፈወርቂና በመለስ ዜናዊ ስምምነት ባድመ ተጠርቶ በሐሰት ጦርነት እንዲያልቅ ተደርጓል (በነገራችን ላይ ይህ ጦርነት ሆን ተብሎ የአዲስ አበባን ወጣት እና የተቀረውን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ለመፍጀት በመለስ ዜናዊና በኢሳያስ አፈወርቂ የተዘጋጀ እንደነበረ ከማስረጃ ጋር ወደፊት አቀርበዋለሁ)
አሁን የአዲስ አበባ ህዝብ ንግዱንና መሬቱን በህወሀቶች ተቀምቶ ከስደት እና ከሞት የተረፈው የየእለት ጉርሱን ለማግኘት በመሯሯጥ ላይ ይገኛል የአዲስ አበባ ህዝብ ከህወሀቶች በተጨማሪ ከሌላ ክልል በመጡ ሕዝቦች ተወሯል ለዛም መሰለኝ ዘፋኙ
“ተሰልቶ ነው እንጂ እንዳው በጠቅላላ
የአዲስ አበባማ ልጆች አንድ ሺህም አንሞላ”
ይህንን እውነት ማመን አለብን የአዲስ አበባ ወጣት የተሰደደው እንደእኔ በፌስቡክ ይጮሀል ሀገር ቤት ያለው የአዲስ አበባ ልጅ እነእስክንድር ነጋ፣ ዮናታን ተስፋዬ፣ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አመራሮች ታስረው እንኳን እየታገሉ ነው ሰማያዊ ፓርቲ የሚገኙ የአዲስ አበባ ወገኖቼም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ግን አነስን፣ ተሰደድን፣ ተገደልን ታሰርን ቁጥራችን ተመናምኖ አዲስ አበባ የሕወሐት ሰዎችና የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከየክፍለ ሀገሩ በመጡ ዜጎች ተዋጠች እነዚህ አዲስ አበባን የተቆጣጠሩ የሕወሐት ጥቅመኞች ህወሀትን ተቃውመው የኦሮሚያ ተማሪዎችን አግዘው ሰልፍ ይወጣሉ ብሎ የሚያስብ ካለ የሃገራችንን ፖለቲካ በቅጡ አልተረዳውም ማለት ነው።
ወንድሞቼ እኛ የአዲስ አበባ ልጆች አዲስ አበባን ተቀምተን ከአዲስ አበባ ወጥተናል የተቀሩት ግን እየታገሉ ነው ማንነታቸውን ደግሞ ማእከላዊ ሄዶ ማጣራት ይቻላል።
#ኤርሚያስ_ቶኩማ