አገሬን ረሀብ ገረፋት፤ ሰው ተፈጥሮን እያዛባት (ተፈራ ድንበሩ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በሽታ ባገር ገብቶ
ከብቱን ሁሉ ፈጅቶ
ዓሣማ ብቻ ቀርቶ
እዩ እስቲ አራዊቱን
ያገር ቡቃያውን
ጨፈጨፈ እሸት እሸቱን።

ሰብል በተምች ተመትቶ
አራሙቻው ተስፋፍቶ
እርሻውን ወርሶ ከፍቶ
ምርቱን ሁሉ በልቶ በልቶ
ያረም መድሐኒት ካገር ጠፍቶ
ከእስያ የመጣው ተብይቶ
ይህ የሰው ተባይ ዘር አጥፍቶ
ባላገሩን አደህይቶ
ከቤት አስወጣው አንከራቶ።

ከብት ሸጦ ቀለብ ገዝቶ
የሚያበላው መኖ አጥቶ
እንሰሳቱ ወድቆ ቀርቶ
የሞተውን ላውሬ ትቶ
ግራ ተጋብቶ
ካገር ወጣ ሰው ቤቱን ከፍቶ።

የድሮማ ቤቱ ትኋን የወረሰው
ሁሉ ተጠራርጎ ከወለል ጣሪው
ዶሮውም አልቋል ቅንቅንም የለው።

ዝንተዓለም ከኖረበት
የጓሮና የደጅ አትክልት
በያይነቱ አዝርዕት
እሽት ከሚበላበት
ሽንኮርም ሆነ ሽንኩርት
ተክሎ ከሚያመርትበት
ቤት ንብረቱ ሲፈርስበት
በሕግ አምላክ ለማለት
የሚሰማው አጥቶት
አንደበቱ ተይዞበት
ለእባብና ጊንጥ ሠራዊት
አገር ቀየውን ለቆለት
እንደሰዶም ገሞራ መቅሰፍት
ፊቱን ላያዞርበት
ረሀብ እና ግርፋት
ኃላም ሞትን በመፍራት
ብ..ን.. አለ ከኖረበት
የሚሆነው ጠፍቶት።

ባላገር ሄዶ በስደት
አገሩ እንግዳ ሆኖበት
ከሚታየው ሁሉ ቤት
ድንጋይ ድንጋዩ እሠገነት
አንዱም ማ’ዘን የለበት።
እንደ ሰናኦር መርገምት
ግምብ አጥር ከልሎት
ሁሉም በርበሩን ዘግቶት
መተያየት መደማመጥ አቅቶት
በየሥርቻው አይጥና ድመት
የታሠረ ውሻ ጩኸት
እንዲህ ያለ ክስተት
በየጎጡ ታክቶት
የሚያረካው አጣበት
አንጀት የሚያርስለት።

ሆድ ቁርጠት
ራስ ምታት
የጎን ውጋት
ትኩሣት፣
ቁርጥማት
ፋታ ማጣት
መፈጠርን መጥላት።
እንጀራ ማሽተት
ዳቦ ለመድሐኒት
ለአዋይም መጥፋት
ወተት ወተት ከወዴት?
ሥጋማ መቀናጣት።
ካልሲየም፣ ኒያሲን
ቫይታሚንና ፕሮቲን
መና ከሰማይ መለመን።
የተገኘውን ሆድ አስገብቶ
ውሀ መሳይ ሁሉ ሞልቶ
ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጭ እንደስልቻ ተቀብትቶ
የሆድ ዕቃው መሥራት ረስቶ፤
ምግብ ከሆድ ተጣልቶ።

አካል ሲቀል እንደሣር
ናላ ሲዞር
ምላስ ሲታሠር
ከላይ ቱር..!
ከታች ቱር..!
የአንጀት ቁስል ሲነዝር
ሆድ ሞር ሞር
ዐይን ብር ብር
ወገን ካለ የሚል ዝር።

አንዱ ጠግቦ ሲንደላቀቅ
ያጣው በጣእር ሲጨነቅ
መተንፈሻው ሲቅ ሲቅ
ቆዳ ካንጀት ሲጣበቅ
ነፍስ ከሥጋ ሲተናነቅ
መላከ-ሞት አንዣቦ ሲጠባበቅ
ሞት በፀጋ ሲናፍቅ
ግራ ገብቶት ያይን ኳስ
ግራና ቀኝ ሲላወስ
ሲታሠር ምላስ
እንኳን ሊጎርስ
አፍ ተስኖት መንቀሳቀስ
አካል ሆኖ አቅለቢስ
ሲሟገቱ ሥጋና ነፍስ
እኔ እብስ እኔ እብስ፤
ሕፃን ተጣብቆ ከጡት
ምንም ምን ላይወጣለት
ወይ ድምፅ አይሰማ ከናት
እሷም አሽልቧት
ያላንዳች ስንብት
ሁሉቱም ወድቀው መሬት
ተመልሰው ሊኖሩባት፤
ዝንታለም ሊተኙባት።

እንግዳ ተቀብለሽ
አስተናግደሽ
አፈር ሆነሽ
አብቅለሽ
ውሀ ሆነሽ
ተጠጥተሽ
ማዕድ ሆነሽ
ተበልተሽ
ላም ሆነሽ
ታልበሽ
ጎመን ሆነሽ
ተከትፈሽ
ዶቦ ሆነሽ
ተቆራርሰሽ
ተካፍለውሽ
እናት ሆነሽ
አጥብተሽ
ተነክሶ ጡትሽ
አሳድገሽ
ሁሉን መግበሽ
አጥግበሽ
ተረግጦ መሶብሽ
አንቺው ተሸጥሽ?
አንቺው ተሰደድሽ?
አንቺው ተራብሽ?

ክብሩን እንዲያ ሲወደው
ልዕልናውን ሲመኘው
ተስፋ ጥሎበት ሲያምነው
ወገን ግን ሆዱን እያየው
አንጀት ማየት ያቅተው ?

በዚች ምድር ባለማችን
ካፈር ወጥተን ሁላችን
በየዘጠኙ ወራችን
ያላንድ ዕዳ ተወልደን
ስንመጣ በባዷችን
ተፈጥሮ እኩል ተሰጥቶን
መሸከሙ እናንተን
አቅቶኛል ሳትለን
የተሰጠንን ፀጋ ተካፍለን
ፈጣሪን አመስግነን
በፍቅር መኖር ሲገባን
የአንድ እናት ልጆች ሆነን
መለያየት ከየት አመጣን?
መጨካከን ከማን ወረስን?

እነቻርለስ ዳርዊን
ተሳስተው ይሆን?
ሰው ከእንሰሳ መጣ ያሉን?
እኛስ የምናየው ተቃራነውን
ሰው ዝንጀሮ ሲሆን?

የሰው ህሊና ተቀብሮ
እውነት በሐሰት ተሽሮ
አንዱ ሌላውን አባሮ
ሰው በሰው ሞት ከብሮ
ያገኘ በቁንጣን ተወጥሮ
ያጣው በወስፋት ተቆዝሮ
ምን ያስብላል ዘንድሮ
ሰው ተሻለ ዝንጀሮ?

ከውሻ-ድመት ትብብር
አስተውለን ብንማር
አሞራው እንኳ አብሮ ሲበር
አእዋፉ በወል ሲወር
የጉንዳን ቤተሰብ ሲገባ እድር
ንብ ተደራጅቶ ሲሠራ ማር
ቁራም ዶልቶ ከንሥር
ሐረግ መዞ ሐረግ ሲያሥር፤
በእኛ ግን ያለው አሣር
አንድነት ከማጠናከር
በልብ-ወለድ አቃቂር
ቀለማትን በመቁጠር
አንዱ ሌላ በማጥቆር
በየጎጡ ሲናቆር
እልፍኝ አፍርሶ ጎጆ መቆርቆር
ትርፉ የሚሆነው ረሀብ ቸነፈር።

መከራም ነግሦ ባገር
ምነው የሰው አለመማር?
ታዲያ ሰው ብዙ ሲመራመር
ምነው ሆነበት ምስጢር?
እንድሚሻል መተባበር?
ተፈጥሮን አድንቆ በፍቅር?

እኔ ብቻ የለውም ክብር፤
ወገንን አናሳፍር፤
ተያይዘን እንዘምር፤
ይዘርጋ እጃችን በፍቅር
እንዳይረግመን አገር
ሰው ሞቶ እንዳይቀበር
ለትንሣኤው እንምከር፤
እንሁን ዋልታ ማገር፤
ደዌ ነግሦብን እንዳይቀር
እንዲመነገል ከሥር።
ሳንለይ ቀለም- ዘር
በመከባበር
የተሰጠንን ከእግዜር
ተካፍለን እንኑር።

እናታችን ተርባ አትቅር
በእርቅ ተለውጦ መቃቃር
በሰላምና ጤና ዘለዓለም ትኑር።