ሠርገኛ መጣ … (ዝናዬ ታደሰ)


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከቅርብ ሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ነውጥ፤ ዕድሜው በመርዘሙ፣ በርከት ያሉ ከተማዎች ውስጥ በመካሄዱና እና አመጹም በይዘትና በመልክ ከቀደሙት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች የተለየ በመሆኑ ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ጆሮዎቻችንን አቅንተን እንድንከታተለው ተገደናል።

ስለሁኔታው እስካሁን እንደተወራው ከሆነ፣ በተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች ውስጥ በአሁኑ ወቅት የሚታየው አለመረጋጋት የአንድ አገር አቀፍ አመጽ አካል አይደለም። ከሁሉም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መካከል ደግሞ በተለይ “የኦሮሞዎች አመጽ” የተባለው አገር ውስጥ እንዲሁም ውጭ በሚገኙ የዜና አውታሮች (የወያኔዎቹም ጭምር) እና በፖለቲካ ድርጅቶች ልሳኖች ገኖ ይነገርለታል።

ለኦሮሞዎች አመጽ ምክንያት ሆኗል የሚባለው የአዲስ አበባ ክልል እንዲሰፋ የግድ ከኦሮሚያ ክልል ግዛት ተቆርሶ ስለሚወሰድ፣ ያ ደግሞ የአዲስ አበባ ክልል ዙሪያ ነዋሪዎች የሆኑ ኦሮሞዎች ገበሬዎችን ስለሚያፈናቅል ነገሩ ኦሮሞ የሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ማስቆጣቱ ነበር።

እንግዲህ ይህ በመሰረቱ የኦሮሚያ የግዛት ጥያቄ መሆኑና ከተማሪዎቹ በተጨማሪ ሌሎች ኦሮሞዎችም በአመጹ መሳተፋቸው አመጹን የኦሮሞዎች ነው ለመባል ያበቃው ይመስላል። ወያኔዎቹ ተቃውሞው ስላየለባቸው የአዲስ አበባን ክልል ለማስፋት ያወጡትን ዕቅድ እንደሳቡት ተነግሯል። እግረመንገዳቸውንም በርከት ያሉ ሰዎችን እንደገደሉ በተለያዩ የዜና ማዕከሎች ተዘክሯል።

ሆኖም፣ እንደሚሰማው ከሆነ የኦሮሚያ የግዛት ጥያቄ ከተመለሰም በሁዋላ አመጹ አለማባራቱ ለተመልካች ትንሽ ያደናግራል። ኦሮሞዎች ያልሆኑ ሁሉ በአመጹ እንዲካፈሉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በኦሮሞዎች ስም ጥሪዎች ቀርበዋል። ግን የቀጠለው የኦሮሞዎች አመጽ በምን ጉዳይ እንደሆነ በጣም ግልጽ አይደለም ፣ በተጨማሪም እስከ አሁን በሚካሄደው አመጽ ሟቾቹም ሆኑ በአጠቃላይ አማጺዎቹ ሁሉም ኦሮሞዎች እንደሆኑም የቀረበ ማስረጃ እስካሁን የለም።

ሌላው የ “ኦሮሞዎች አመጽ” እንድምታ ደግሞ አባባሉ አመጹን በኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት የሚመራ ማስመሰሉ ነው። የአንዳንድ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች መታሰር ደግሞ ይሀንኑ ግምት የበለጠ ያጠናክራል። ግን አመጹ የፖለቲካ አመራር የሚሠጠው ከሆነ አመራሩ ስልታዊነት ይጎድለዋል።

የኦሮሞዎች አመጽ ወያኔዎችን አስገድዶ እስከ አሁኑ ሰዓት ድረስ በግልጽ ላልተነገሩ ተጨማሪ የኦሮሞ ጥያቄዎች መልስ ለማሰጠት ከሆነ የቀረው በዙሪያቸው የሚኖረው ሕዝብ ሳይደግፋቸው ኦሮሞዎች ብቻቸውን ዓላማቸውን ማሳካት አይችሉም። ወያኔ ነጥሎ ይመታቸዋል።

ትብብር ለማግኘት ደግሞ ለአመጹ አመራር የሚሰጥ አካል ካለ የግድ ከመነሻው የኦሮሞዎችን አመጽ የረጅም ጊዜ ግብ (እውነትም ይሁን ሃሰት) ማሳወቅ ይኖርበታል። የኦሮሞ ሕዝብ ከዳር እስከዳር እስረኞችን ለማስፈታት መነቃነቁ መልካም ሳለ፣ ለሕዝባዊ አመጽ ይህ የአጭር ጊዜ ግብ ነው የሚሆነው።

በአሁኑ ድብብቆሽ ኦሮሞዎች ያልሆኑ ሰዎች “የኦሮሞዎች ፍላጎት ምንጊዜም እንደ ኤርትራ መገንጠል ነውና እኛን ምን አግብቶን ለኦሮሚያ ነፃነት እንሞታለን? ለኦሮሚያ ነፃነት ኦሮሞዎች ይሙቱ ” ብለው የሚሆነውን ሁሉ ከዳር ሆነው ቢያዩ አያስገርምም።

እንደሚታወቀው የኦሮሞ ነፃነት ትግል ፀረ አማራ እና ፀረ ኢትዮጵያ ነው። ግን የኦሮሞ ድርጅቶች ፀረ አማራ እና ፀረ ኢትዮጵያ ሆነው ወያኔን ለማሸነፍ የግድ ማግኘት የሚያስፈልጋቸውን የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ማግኘት አይችሉም።

ቀድሞ ኢሕአፓ እና ተሐህት ለኤርትራ ነፃነት እንዳገለገሉት፣ (ለምሳሌ) ግንቦት ሰባት እና የኦጋዴኑ ነፃነት ድርጅት ለኦሮሚያ ነፃነት ያገለግሉናል ብለው የኦሮሞ ድርጅቶች ቢያስቡ እንኳን ሁለቱም ድርጅቶች ከኤርትርያ ውጭ ሕይወት የላቸውምና፣ የኢሳያስ አፈወርቂ በዕድሜ መግፋት ብቻውን ለዘለቄታው በኤርትርያ መንግስት ትብብር ላይ ብዙ መተማመን እንደማይችሉ ሊጠቁማቸው ይገባል።

ከዚህ በተጨማሪ ግንቦት ሰባቶች ከኦነግ ጋራ በፍቅር የመተባበር ስሜታቸው ልባዊ እንደሆነ ጊዜ የመሰከረለት ነገር ቢሆንም፣ ለኦሮሚያ ነፃነት ሲሉ ደማቸውን እንዲያፈሱ፣ አጥንታቸውንም እንዲከሰክሱ ኢትዮጵያውያንን አስተባብረው ለእርድ ማቅረብ መቻላቸው እጅግ ያጠራጥራል።

ደግሞም የኤርትራ ነፃነት በላብ አደሩ ዓለም አቀፋዊነት እና በብሔሮች ጭቆና እና በብሔር ነፃነት ሽፍንፍን፣ የኤርትራ ነፃነት የሌሎችም ነፃነት እንደሚሆን ተብሎ ለመሃል አገሩ ሰው በመቅረቡ ምክንያት ነገሩ ብዙዎችን ለማወናበድ በቅቷል። ግንቦት ሰባት ግን እንዲህ ያለ ጥልቅ ርዕዮተዓለማዊ ሽፋን የለውም።

በሌላ በኩል ሕወሀት እና እልፍ አዕላፍ የትግሬ ተጋዳዮች በኤርትራ በረሃዎች ለኤርትራ ነፃነት መስዋዕት ቢሆኑ የ”አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል” ጉዳይ ሁኖባቸው ነበር። የኦጋዴን ሶማሊዎች ለራሳቸው ነፃነት ጦርነት ተዋግተው፣ ለኦሮሚያም ነፃነት ተዋግተው፣ አቅማቸው ፈቅዶ ቢችሉትም እንኳን ከኦሮሞዎች ጋራ ላላቸው ቅርብ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ትስስር ሲሉ የሚያደርጉት ነገር አይሆንም። ለትግል አጋርነት የሚያበቃ ታሪክ እና ባህል አይጋሩምና ነው።

ኦነግ እና የኦጋዴኑ ድርጅት አማራን እና ኢትዮጵያን (ምናልባት አሁን ትግሬዎችንም ይጨምር ይሆናል) አንድ ላይ ጨፍልቀው አንድ ትልቅ የጋራ ጠላት ስለጠፈጠፉ ጊዜያዊ የዓላማ አንድነት አላቸው። ኦነግ ጦር ስለሌለው እና የኦጋዴኑ ድርጅት አለው ስለሚባል ደግሞ የኦሮሚያ ነፃነት ቢሳካ በኦጋዴኖቹ ትከሻ ነው የሚሆነው። ዳሩ ግን ነገሩን እንደኦጋዴኖቹ ድርጅት ሆኖ ለተመለከተው፣ ሶማሊዎቹ ለኦሮሚያ ነፃነት መዋጋታቸው የኦጋዴኑን ድርጅት ኃይል ስልሚከፍል፣ እንዲሁም የኦሮሚያ ነፃነት ለኦጋዴን ነፃነት ቅድመ ሁኔታ ባለመሆኑ፣ ኦነግ ቢመኘውም የኦሮሞዎች አፍንጫ ሲመታ የሶማሊዎች ዓይን ማልቀሱ ያጠራጥራል።

ይሄ ሁሉ እንግዲህ ወያኔዎች በኦሮሞ ድርጅቶች ወይም በሌሎች ጦር ቢሰበቅባቸው የወያኔን የበላይነት ለማስረገጥ ሲሉ የኦሮሞንም ሆነ የሌላ ብሔርተኝነትን ከመውጋት ወደሁዋላ እንደማይሉ በመገመት ነው። የኦሮሞ ብሔርተኛ አክራሪዎች እንዲሁም ሌሎች አማራዎችን ሳር ጎጆ ውስጥ አጉረው ቢያጋዩዋቸው ወያኔዎች ለደስታቸው ወሰን አይኖረውም። ሆኖም የዛኑ ያክል የኦሮሞም ሆነ የሌላ ብሔርተኝነት አይሎ ከእጃቸው እንዲወጣም ወያኔዎች አይፈልጉም።

እነዚህንና ለሎችንም ምልክቶች ላጤነ “የኦሮሞዎች አመጽ” የፖለቲካ አመራር የሚሰጠው አካል አለው ለማለት አያስደፍርም። በብዙ መልኩ አመጹ ቅንብር ማጣቱም የአዲስ አበባ አካባቢ ነዋሪ ኦሮሞዎች አመጽ ለመባል ይበቃ እንደሆነ እንጂ ኦሮሞዎች በያሉበት የኦሮሚያ ክልል ግዛት ወደ አዲስ አበባ ክልል መቀላቀሉን ተቃውመው ከዳር እስከዳር ተንቀሳቀሱ ቢባል ማጋነን ይሆናል።

ግን አመጹ የኦሮሞዎች ብቻ ሆነም አልሆነም፣ የዜና አቅራቢዎቹ እንዲሁም ወያኔዎቹ የኦሮሞዎች ጉዳይ ብቻ ሆኖ እንዲታይ ጽኑ ፍላጎት ያላቸው ይመስላል። ወያኔዎቹ “የኢትዮጵያውያን አመጽ” ባይሆንላቸው ለምን እንደሚወዱ ግልጽ ነው። የዜና አቅራቢዎቹ፣ በተለይም ወያኔዎችን አይወዱም የሚባሉት በስህተት እንኳን አንዳንዴ ኦሮሞዎችን ኢትዮጵያውያን ሊያደርጓቸው አለመፈለጋቸው ግን ይደንቃል።

ለማንኛውም የጊዜውን የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚያብላሉ ሰዎች ይህ የተቃውሞ ጎርፍ ማዕበል ሆኖ የወያኔዎችን መንግስት እንዲፈነቅለው፣ እንደሚመስላቸው ይህና ያ መደረግ ይኖርባቸዋል እያሉ ሃሳባቸውን ያካፍላሉ። በተደጋጋሚ የህብረት እንዲሁም የድርጅት ጥሪዎች ይደረጋሉ። ሁለቱም የተለመዱ ግብዣዎች ቢሆኑም አሁን አመጹ ሳይታሰብ ቀደመና ከበፊቱ በተለየ “እንዴት ነውጡን መልክ እናሲዘው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት እየተሞከረ ይመስላል።

መቸም አመጹ እየተካሄደ እያለ “ቅንብርና አመራር እንድንሰጠው ህብረትን ፈጥረን ድርጅትን እስክንመሰርት ተዳፍኖ ይጠብቅ” ማለት አይቻልም። ተቃውሞው ወይ ይብስበታል ወይም ይከስማል፤ ምን እንደሚሆን ከወዲሁ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ግን ይህ አጋጣሚ ለወደፊት የሚጠቅም ትምህርት ይሰጣል። ይኸውም አመጽን መቀስቀስ፣ መምራትና ከግብ ማድረስ እንደሚቻል፤ ግን ያልቀሰቀሱትን፣ ዓላማውን ያላወቁለትን አመጽ ከዳር ማድረስ እንደማይቻል ነው።

ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ግብዣዎች መካከል ህብረት የስነልቦናዊ ክስተት በመሆኑ “እስኪ ህብረት እንፍጠር” ስለተባለ የሚሆን ነገር አይመስልም። ሆኖም በድል ዙሪያ ሰዎች እንደሚሰባሰቡ ደግሞ በግብር የታየ ነው። እና ህብረትን ለመፍጠር ከተፈለገ ትንሽም ቢሆን ድል ያስፈልጋል። ከዚያ በሁዋላ ድል ሌላ ድልን እየወለደ፣ የበለጠ ህብረትንም ይገነባል።

ድል ከተቀነባበረ ትግል ይገኛል። የተቀነባበረ ትግል ለማድረግ ደግሞ መደራጀትን ይጠይቃል። ከምናውቀው በመነሳት ደግሞ ከአብዮታዊ ታሪካችን የተወረሰው ዓይነት መደራጀት፣ ማደራጀት እና ማንቃት በዙ ተነግሮለታል። ሆኖም ለሁሉም ዓይነት ትግል ደግሞ አንድ የድርጅት መልስ ሊኖር አይችልም። አብዮት ለማስኬድ የሚፈጠር ድርጅት ከምንም ይሻል ይሆናል። ግን አንድ ትልቅ ደካማ ጎን አለው። ይኽውም እንዲህ ነው። በደርግ ዘመን በተቃዋሚነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች (ጀብሃ ሻእቢያ ወያኔ ኢሃአፓ ኢፒዲኤ ኢዲዩ እና የመሳሰሉት) ሁሉም ከኢትዮጵያ ውጭ የሚደግፉዋቸው መንግስቶች ባይኖሩዋቸው ኖሮ ህልውናቸው ወረቀት ላይ ይቀር ነበረ።

እንደዛም ሆኖ በአንድ ወቅት የታጋዮች ሁሉ ጌታ ሻአቢያ በኢትዮጵያ ሰራዊት እስከ መጨረሻ ጣቢያው እስከናቅፋ ድረስ ተገፍቶ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ደረጃ መድረሱ ይታወሳል። በጊዜው ለጦርነት ጫካ ገብተው የነበሩ ድርጅቶች ጥቃት ቢደርስባቸው ወደ ሱዳን ሸሽተው ማምለጥ ይችሉ ነበረ። መሪዎቻቸው እንደፈለጉት በየአገሩ መንቀሳቀስም ይችሉ ነበረ። ሁሉም ድርጅቶች ጠቃሚ እስከነበሩበት ጊዜ ድረስ ያላቋረጠ የስልጠና፣ የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲና የመሳሪያ ድጋፍ አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ብዙ ጠላቶች ነበሩት። ከሶቪየቶች እና ከጥቂት ደካማ አገሮች በስተቀረ ሌሎች ያገባናል ይሉ የነበሩ በምዕራቡ ኃያላን ዙሪያ የተሰባሰቡ መንግስታት በአንድ መልክ ወይም በሌላ መልክ ተቃዋሚዎችን አግዘዋል። ለድል አብቅተዋቸው የፖለቲካ ስልጣንንም አከፋፍለዋቸዋል። በመሰረቱ ጸረ ኢትዮጵያ ርብርቦሹ ዓለምአቀፋዊ ነበረ ማለት ይቻላል።

በአንጻሩ ወያኔ ጠላት የለውም። የወያኔ ተቃዋሚዎች ወዳጅ መንግስታት የሉዋቸውም። የኤርትርያ እና የተቃዋሚዎች መጣሁ ቀረሁ ከ”የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ”ነት አያልፍም። ስለዚህ በቀድሞው ስሌት አይነት አገር አቀፍ የሆነ አንድ ማዕከል የሚመራው ከከተማ ወደገጠር የትጥቅ ትግል የሚባለው ነገር አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ አይሰራም።

በተጨማሪም በአብዮት ዘመን ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም ለኢትዮጵያውያን ባይተዋር ነገር ስለነበር፣ ስለ አዲሱ ርዕዮት ቀድመው ያወቁ “ነቅተዋል” የተባሉ ሰዎች ተሰባስበው ሌሎችን ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም አስተምረውና አግባብተው ከጎናቸው ለማሰለፍ የሚያገለግላቸውን ትግሉ የጠየቀውን ከአመራር ወደ ጀሌ ተጋዳይ፣ ከላይ ወደ ታች የተዋቀረ ዓይነት ድርጅት መፍጠር ነበረባቸው።

የወቅቱ ትግል ግን ሌሎች ነቅተው እስኪደራጁ የሚያስጠብቃቸው ሳይሆን ቀድመው “ነቅተዋል” የሚባሉት ሰዎች እራሳቸው የሚታገሉት ዓይነት ትግል ነው። ለሕዝብ የሚያስተዋውቁት አዲስ ርዕዮተ ዓለምም የላቸውም፤ ኢትዮጵያዊነት “ዴሞክራሲያዊ ካልሆነ አትውደዱት” ተብሎ ከተማሪው እንቅስቃሴ ዘመን ጀምሮ አለማቋረጥ ቢራከስም፣ አሁንም ቢሆን አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ነገድና ኃይማኖት ሳይለይ የሚያስተባብር ጥልቅ ስሜት ነው።

ይልቅ ወያኔን ከኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ ለማውረድ ወቅቱ የሚጠይቀው ትግል እና አደረጃጀቱ የሚከተለውን ሊመስል ይችላል።

ወያኔ ከሌሎች መንግስቶች የተለየ አይደለም። ህዝብን የሚቆጣጠርበት የጠላቶቹንም እንቅስቃሴ የሚሰልልበት የኢኮኖሚና የወታደራዊ አውታሮቹን ከጥቃት የሚከላከልበት ዋና መሳሪያው የጸጥታ መዋቅሩ ነው። የስለላው መረብ በሰፊው ከዳር ወደ መካከል በረጅም ሰንሰለቶች የተገነባ ሲሆን የቀለበቶቹ ብዛት ለወያኔ ጥንካሬ የሆነውን ያክል ከሌላው ተፈጥሮው በበለጠ ለአደጋ የሚያጋልጠውም ችግሩ ይኽው ነው። ይህ ማለት ከብዙ ትናንሽ ነገሮች የተገነባ አካል ብዙ የሚሰናከሉ ክፍሎች ይኖሩታል።

በበለጠ ለማብራራት፣ ወያኔ ለአምስት ኢትዮጵያውያን አንድ ሰላይ አለው ይባላል። ከዛ ሌላ የየአካባቢውን ነዋሪ በዛው በአገሬው ሰው ነው የሚያሰልለው። ይህ ሁሉ ሁለት ስለት ያለው ቢላዋ እንደሆነ ግልጽ ነው። ወያኔ ሰላዮቹን እንደሌላው መንግስት ሁሉ በገንዘብ ቀጥሮ ነው የሚያሰራቸው። እነዚህ ሰላዮች በጣም ብዙዎቹ ደሞዛቸው ሃብታም አያደርጋቸውም። በጎረቤቶቻቸው ላይ እያሴሩ ለአለቆቻቸው የረባውንም ያልረባውንም ወሬ እያቀበሉ የሚኖሩ ቅጥረኞች ናቸው። ቅጥረኞች ደግሞ አይነተኛ ባህሪያቸው ከተከፈላቸው ምንም የማያደርጉት ነገር አለመኖሩ ነው።

በአጭሩ ወያኔ የገዛውን ቅጥረኛ የወያኔ ተቃዋሚ የሆነም ሊገዛው ይችላል። የገንዘቡ መጠን የግልጋሎቱንም መጠን እንዲሁም ጥራት ይወስናል። ዋናው ነጥብ ግን ቅጥረኛ ተአማኒነቱ ለገንዘብ መሆኑ ነው። በዚህ መልክ የወያኔን የፀጥታ መዋቅር ማደናገር፣ ከውስጥ መቦርቦርና ከጊዜ ብዛት መናድ ይቻላል።

ይህ ታላቅ ግኝት አይደለም፤ ስልቱ የኖረና የተፈተነ ነው። የምዕራቡ ኃያላን በየቦታው በሰፊው እየተገለገሉበት ይገኛሉ። በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ላይም ተጠቅመውበት ትንሽ ጊዜ ቢወስድባቸውም መንግስት አፍርሰውበታል። በንጉሱ ዘመንም ሆነ በሁዋላ የኤርትራ ወንበዴዎች እንዲሁም ሌሎች መሰል ቡድኖች በተንኮል በመንግስት ላይ ብዙ ጥፋት አድርሰዋል።

እና ሁሉም የሚያውቁት የነበረው ታላቁ የአደባባይ ምስጢር በየትም ይገኝ፣ መንግስት የሚባለው ሰው ሰራሽ ተቋም በእውነትም በተፈጥሮው የእምቧይ ካብ መሆኑን ነው። ይህ ማለት የመንግስት ሕልውና ከቀን ወደቀን የተጠበቀ የሚሆነውና እና ቀጣይነትም የሚያገኘው በርከት ያሉ መንግስታዊ ክንዋኔዎች ሁሉም በአንድ ጊዜ ያለመሰናክል ሲካሄዱ ነው።

ይህ ማለት ደግሞ ለምሳሌ ገቢ የሚያፈልቁ የንግድና የመሳሰሉ ተቋማት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጠላትን ክንድ እንዳያደነድኑ መንግስት የማያቋርጥ ክትትል ማድረግ ይኖርበታል። ይህ ብቻውን ቀላል ሃላፊነት አይደለም። በሌላ ጎን ደግሞ የየትኛውም መንግስት የጀርባ አጥንት የሚሆነው ወታደራዊ ተቀጥላው አለጥያቄ ትእዛዝ መቀበሉ ብቻ ሳይሆን ትእዛዙን ማስፈጸሙ በበኩሉ የምግብ፣ የማመላለሻ አገልግሎት፣ የነዳጅ፣ የመሳሪያ እና የመሳሰሉትን አቅርቦት ላይ የሚመረኮዝ እንደመሆኑ መንግስት ለመንጠላጠያ በጣም በርካታ ሲባጎዎችን መቀጣጠል ይኖርበታል።

ይሄ ሁሉ ሳያንስ በተለይ እንደወያኔ ላለ 80 ሚሊዮን ሕዝብ ጠላት አድርጎ ለሚኖር መንግስት ከሚሊዮኖች ሰላዮቹ የሚሰበስበው መረጃ አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጥ መቻል ደግሞ እጅግ አድካሚ፣ እፎይታ የማይሰጥ ሃላፊነት እንደሆነ መገመት አያዳግትም።

ከላይ እንደምሳሌ በጠቀስኩዋቸው ሶስት ተቋማት ውስጥ ብቻ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የተጋለጡ ሊሰናከሉ፣ ሊደናቀፉ የሚችሉ አካላት ይገኛሉ። ከመደጋገም ብዛት የወያኔን መንግስት አሽመድምደው፣ ከሌሎች ነገሮች ጋር ተደምረውም የሚንዱት ናቸው። ሌላው ቀርቶ ጊዜና ቦታ እየተመረጠ በርከት ያሉ የወያኔ ተሽከርካሪዎች ጎማዎቻችው ሁሉ በየወሩ በየከተማው ቢተረተሩባቸው በዚያ ሳቢያ በእነዚያ ቀናት ሊፈጠር ከሚችለው የስራ መጓተት ሌላ፣ በተለይም ለወያኔዎቹ ለራሳችው ወያኔ ድንጉጥና ደካማ እንደሆነ የሚመሰክር፣ ለኢትዮጵያውያንም ታላቅ የስነልቦና ድል፣ ገፋ ላለ ነገርም የልብ ልብ የሚስጥ አጀማመር ይሆናል።

ይህንን ለማድረግ ድርጅት ያስፈልጋል። አዋጅ አያስፈልግም። ወደ ጎረቤት ሀገር ሄዶ መሸፈትንም አይጠይቅም። ጥቂት ሰዎች በታላቅ ጥንቃቄና ጥበብ በትንሹ ጀምረውት እያደረ ሊጎለብት የሚችል የወያኔን አከርካሪ የሚሰብር ትግል ነው።

“እንዳለፈው ጊዜ ይሄ መንግስት ይፍረስ እንጂ የባሰ አይመጣም ብለን ከወያኔዎች የከፋ ነገር የሚያስከትልብንን ስህተት እንዳንሰራ” የሚለው መሸበር በመሰረቱ በመረጃ የተደገፈ ፍርሃት አይደለም። ከዚህ አስተያየት ጀርባ ደርግን ያፈረሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የሚል የተሳሳተ ግምትም ያስተጋባል።

ደርግን የኢትዮጵያ ሕዝብ አፈረሰው ማለት የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦርነቱ ጊዜ በወያኔዎች እና በሻእቢያ ሲመራ ነበር፣ እንዲሁም በሽግግሩ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ ተወክሎ ነበር እንደማለት ይቆጠራል። ያ ደግሞ ትክክል አይደለም። በኢሰፓ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ሲፈርስ ኢትዮጵያውያን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ቢተባበሩም፣ ደርግን ያፈረሱት በመሰረቱ ምዕራባውያን ኃያላን ናቸው። እነርሱ ደግሞ በየትኛውም ጊዜ የኢትዮጵያን መንግስት አፍርሰው በምን እንደሚተኩት ግራ ተጋብተው እንዳልነበረ በሎንዶኑ ስብሰባ ግልጽ ነበር። እና ከላይ የተጠቀሰው ሽብር የአሸናፊዎች ጭንቀት አይደለም።

ግን፣ እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያን ጸረ ወያኔ አመጽ ወያኔዎችን ከማፍረሱ በፊት ፈረንጆቹ እጃቸውን ማስግባታቸው አይቀርም። የኢትዮጵያውያን ጭንቀት መሆን ያለበት በድርድሩ ጠረቤዛ ዙሪያ የሚወክላቸው ኃይል ወንበር ማግኘቱና፣ ምኞታቸውና ፍላጎታቸውን የሚያቋጥር ወያኔዎችን የሚተካ መንግስት መቋቋሙ መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ፈረንጆቹ “እንደወያኔ ያለ ጸረ ኢትዮጵያ መንግስት እንደገና የምትሾሙብን ቢሆን ወዲያውኑ እናፈርሰዋለን” የሚል መልዕክት ከኢትዮጵያውያን ጸረ ወያኔ አመጽ እንዲደርሳቸው መሆን ይኖርበታል።

ድል ለኢትዮጵያውያን!
ዝናዬ ታደሰ