ህግ እና ደንብ የጣሰው ማነው? -Eyasped Tesfaye – ከሰማያዊ ፓርቲ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ህግ እና ደንብ የጣሰው ማነው?
———–
ሞልቶ ሲንተረከክ እንሸሽገው ቢባል በየት በኩል; ሰብቶ ደልቦ እራፊ ሰውነቱን አልሸፍን ሲል አደባባይ ወጥቶ በሰው አይን መመታቱ አይቀሬ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አልፅፍም ብዬ ነበር….ለማን ነው የምፅፈው; ማንስ ምን አግብቶት ነው የምንፅፍለት; እያልኩ፡፡ ደግሞ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሀል አይነት ‹‹የጅራፎች›› ድምፅ ሲበራከት ልፃፍ ይሆንን ስል……..እንፃፍ ካልንም ደግሞ የቱን አንስቶ የቱን መተው ይቻላል; ያለውን ሀቅ በሙሉ ልፃፈው ወይስ ቁርጭኝ ቁርጭኙን ብቻ; በእውነት ብዙ አስቢያለሁ፡፡ የትናንቱን የወንድሜን የአርአያን ፅሁፍ እስካነብ ድረስ ግን ባልፅፍ ይሻላል ብዬ ነበር አሁን ግን አንድም ነገር ሳያስቀሩ ከመፃፍ የተሻለ አማራጭ የለም ብዬ አምኛለሁ፡፡

Eyasped Tesfaye's photo.

እነ ‹‹ቃር አያውቅሽ›› ዳር ተቀምጠው በሰው ቁስል ላይ ጨው ሲነሰንሱ ዝም ብሎ ማየትም በስጋም በነፍስም ያስጠይቃልና እነሆ እውነቱ፡-

መግቢያ

አንድ፡-

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች የመጀመሪያውና ከባዱ ፈተና ሲመሰረቱ የሚገጥማቸው ነገር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተቆራርጦ የቀረበው የአንዳርጋቸው ፅጌ ንግግር ላይ አንዳርጋቸው የሚናገረው አንድ ቁም ነገር አለ ‹‹ድርጅቶች ሲመሰረቱ ቢያንስ ሁለት መቶ እና ሶስት መቶ ሺህ ፊርማ እንዲሰበስቡ መገደድ አለባቸው›› የሚል፡፡ እውነት ነው እንዲህ አይነት ሰፊ መሰረት ቢኖር እጅጉን መልካም ነበር፡፡ አሁን ባለው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህገ ደንብ መሰረት አንድ የፖለቲካ ድርጅት ለመመስረት 1500(አንድ ሺህ አምስት መቶ) አባላትን አሰባስቦ ማስፈረም ግድ ይላል፡፡ አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶችም ይህንን መስፈርት ለማሟላት ስለሚከብዳቸው መነሻቸው ላይ አባል የሚያደጉት የተገኘውን በሙሉ ነው፡፡ የትምህርት ደረጃው፣ የፖለቲካ ንቃተ ህሊናው፣ በሚኖርበት ማህበረሰብ መካከል ያለው ተቀባይነት ወዘተረፈም ከግምት ውስጥ ሳይገቡ በድርጅቱ ተቋማት ውስጥ (ምክርቤት፣ ኦዲት፣ ማእከላዊ ኮሚቴ፣ ዲሲፒሊን ኮሚቴ፣ ስራእስፈፃሚ፣ ፖሊት ቢሮ ወዘተረፈ) ቦታ እንዲይዙ ይደረጋል፡፡ እንግዲህ ድርጅቱ ከተመሰረተ እና በህግም እውቅና ከተሰጠው በኋላ በእውቀትም በልምድም እጅጉን የተሻሉ ሰዎች ወደ ድርጅቱ መጉረፍ ይጀምራሉ፡፡ ችግሩ የሚመጣው እዚህ ጋር ነው፡፡ ጥቂቶች አስተዋዮች ከእኔ የተሻለ አለ እኔ ለዚህ ቦታ አልመጥንም በማለት ከእነርሱ ለተሻለው ቦታቸውን ሲለቁ አብዛኞቹ ግን በአጋጣሚ ያገኙትን ቦታ ላለመልቀቅ ወደ ተንኮል እና ሸር ይገባሉ፡፡ ከኋላ መጥተህ እዩኝ እዩኝ ምንደነው የሚለው ይበረክታል፡፡ አሉባልታ እና ሴራ ቦታውን ይይዛሉ፡፡

ለምሳሌ ያለፈው ጠቅላላ ጉባኤ ከመደረጉ በፊት በሚቀጥለው የስራ ዘመን የምክር ቤት አባል ለመሆን ለሚፈልጉ አባላት ማስታወቂያ ወጥቶ መስፈርቱን የሚያሟላ አባል በሙሉ ተወዳድሮ የምክርቤት አባል የመሆን መብት ይሰጣቸው ብለን ሀሳብ ስናቀርብ አሁን ካሉት የምክር ቤት አባላት እና አሁን ያለው ምክርቤት በራሱ ከሚመርጣቸው ጥቂት ሰዎች ውጭ ሌላ ሰው ለምክርቤት አባልነት መወዳደር አይችልም የሚል ተቃውሞ ነው ከምክርቤቱ የገጠመን፡፡ የመጀመሪያው ሶስት አመት የስራ ዘመን አልቆ ሁለተኛው ሲጀምር የቀድሞው ምክር ቤት አባላት እና ምክርቤቱ በራሱ በጎ ፈቃድ የጨመራቸው ጥቂት ሰዎች ናቸውና የተወዳደሩት ባለፈው የስራ ዘመን የነበረው ምክርቤት ራሱ 99በመቶ ሳይቀየር ሳይለወጥ ቀጥሏል፡፡ ብዙ በእውቀትም በልምድም የተሻሉ ሰዎች አሁንም ዳር ይዘው ከመመልከት ውጭ አማራጭ የላቸውም፡፡ አሮጊት ሴት በመቀነቷ ቋጥራ እንዳስቀመጠችው ሳንቲም የማይጨምር የማይቀንስ ነገር………. በነገራችን ላይ ሰማያዊ ውስጥ ጎልተው የወጡ ወጣቶች ብርሀኑ ተ/ያሬድ፣ ዮናታን ተስፋዬ፣ ኢሩሳሌም ተስፋው፣ ጋሻው መርሻ፣ እስክንድር፣ መአዛ መሀመድ በአንድም በሌላም መንገድ ወደ መድረኩ እንዲወጡ ያስቻላቸው ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚውን ክፍት እና አሳታፊ በማድረግ እና በሌሎች መንገዶች……..

ሁለት፡-

የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላው ፈተና ደንብና ፕሮግራም ላይ ማስተካከያ ማድረግ ነው፡፡ በተለይም ምርጫ ቦርድ ደንብና ፕሮግራም እንዳይሻሻሉ ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ከደንብ ማስተካከያ በኋላ አንድነት ፓርቲ የገባበትን ፈተና ልብ ይሏል፡፡ ካለፈው ጠቅላላ ጉባኤ በፊትም ደንብና ፕሮግራም በማሻሻል ሀሳብ ዙሪያ የምርጫ ቦርድ ነገር የራሱን ጥላ አጥልቷል፡፡ መሻሻል እና መለወጥን መፍራት በራሱ በድርጅት ውስጥ የሚያጋጥም የድርጅት ተፈጥሯዊ ባህርይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ ወንድሜ አርአያ ደንቡን ሳያውቁ አባል የሆኑ ሲል ትናንት የሰጣት አስተያየት አስቃኛለች፡፡ ደንቡን ብቻ ሳይሆን ደንቡን የቀረፁ ሰዎች የቀረፁበትን መቅድመ እሳቤ (presupposition) ሳይቀር በጊዜ ሂደት ውስጥ ለመገንዘብ በቅተናልና፡፡ ለምሳሌ በምርጫ ቦርድ ህገ ደንብ መሰረት ከሌሎች አቻ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የሚደረጉ ከውህደት በመለስ ያሉ ግንኙነቶች በስራ አስፈፃሚው በኩል መፈፀም ይችላሉ ቢልም የሰማያዊ መተዳደሪያ ደንብ ግን ማንኛውም አይነት ግንኙነቶች በጠቅላላ ጉባኤ እንዲወሰኑ ያደርጋል፡፡ ይህ ለምን ሆነ; ከአንድነት የመጡ የሰማያዊ መስራች አባላት ከደረሰባቸው የልብ ቁስለት የተነሳ ወደፊት ከአንድነት ጋር ሊደረጉ የሚችሉ ግንኙነቶች እንዳይኖሩ ከወዲሁ ለመቁረጥ ነበር፡፡

ደንብን በተመለከተ ግን ትልቁ ችግር ደንብን አለመረዳት ሳይሆን ደንብን ለሚፈልጉት ሴራ እና ተንኮል እየጠመዘዙ መጠቀም ነው፡፡ በተለይም ደንብን እንዲተረጉም ስልጣን የሚሰጠው አካል (ምክርቤት አሊያም ኦዲት) ደንቡን እንደፈለገ ላሻው ጉዳይ የመጠምዘዝ መብት ስለሚኖረው በድርጅቱ ውስጥ ያሻውን የሚያደርግ ከሐሌ ኩሉ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው፡፡
ፍሬ ነገር

አንድ፡-

ፕሮግራም እና ደንብ ሲጣስ በቀና ልቦና ዘብ መቆም፣ መከራከር፣ መሞገት ይበል የሚያሰኝ በጎ ነገር፡፡ ከጀርባ ሌላ አጀንዳ አዝሎ ግን ፕሮግራምን እና ደንብን መጠቀሚያ ማድረግ እጅጉን አሳፋሪ ምግባር ነው፡፡ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው፡፡ አሁን የተከሰተው ነገር እነ ዮናታንን አባረናል በሚል የሚያበቃም አይደለም፡፡ ሊቀመንበሩም ተባረዋል ሲባል በቅርቡ እንሰማ ይሆናል፡፡ ከ 4 ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን ባለፉት 3 አመታት ውስጥ ከድርጅቱ 160 ሺህ ብር ዘርፈዋል በሚል ክስ ጉዳዩ ወደ ‹‹ዲሲፕሊን›› መመራቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ልብ አድርጉ 160 ሺህ ብር በሶስት አመት ውስጥ ለ5 ሆኖ ‹መዝረፍ› ማለት በወር 888 ብር ይዘርፉ ነበር እንደማለት ነው፡፡ አሁን በሞያቸው እጅግ የተከበሩ ሰዎች እና በሞያቸው ቢሰሩ ብዙ ሺህ ብር በቀን የሚያገኙ ኢንጅነሮችን በወር ስምንት መቶ ሰማኒያ ስምንት ብር (888 ብር) ትዘርፉ ነበር ብሎ መክሰስ አያሳፍርም; ክሱን ያቀናበሩትን ሰዎች የማሰብ አቅምን ግምት ውስጥ የሚከት አሳፋሪ ተግባር፡፡ ዮናታን ከመታሰሩ አንድ ሳምንት በፊት በተደረገው የምክር ቤት ስብሰባ እነ ይልቃልን 160 ሺህ ብር ዘርፈዋል ያሏቸው ‹‹የአጣሪ ኮሚሽኖች›› አሁን በሰው ዘንድ እንደሚያስገምታቸው ሲያውቁ ይግባኝ ማለት ስለማይችል ጉዳዩን እንመረምራለን ይበሉ እንጂ ዮናታንን 78 ሺህ ብር ዘርፈሃል ብለው ሊከሱት ሽር ጉድ እያሉ ነበር፡፡ በተገኘው መንገድ ሁሉ ይልቃልን ከጨዋታ ውጭ ማድረግ አለብን ብለው የተነሱ ሰዎች ይልቃልን ይደግፋሉ ብለው ባሰቧቸው ሰዎች ላይ በሙሉ የማያዳግም የማጥፋት እርምጃ ለመውሰድ ጎንበስ ቀና እያሉ ነው፡፡ ይልቃልን በሚደግፉ ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ለይልቃል ጥሩ ስም ሊያተርፍለት ይችላል ብለው ያሰቡትን ሰራ በሙሉ ከማሰናከል ወደኋላ አይሉም፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በሰማያዊ ፓርቲ ፅህፈት ቤት ውስጥ መራራ እና ይልቃል ከሀገር ቤት እንዲሁም ከዲሲ በስካይፕ የተደረገው ስብሰባ ሲዘጋጅ ለህዝቡ ሊሰጠው የሚችለውን ትዕምርታዊ (ሲምቦሊካል) መልዕክት ታላቅነት የሚታወቅ ቢሆንም እነዚህ ግለሰቦች (በተለይም አንዳሻው) ግን የመብራት ቆጣሪ ገንጥለው በመሄድ ፕሮግራሙን ለማሰቀረት ያደረጉት ጥረት ያልኩትን የሚያጠናክርልኝ ነው፡፡ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ የሚሰራ ጄነሬተር ፍለጋ እንዴት እንደተሯሯጥን የነበረ ያወቀዋል፡፡

ያለፈው ወር ላይ በነበረን የብሄራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ‹‹አሁን በኦሮሚያ እየተደረገ ያለውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ መደገፍ ያስፈልገናል ከዚህም ባለፈ ግን ለሱዳን ሊሰጥ ያለውን መሬት በተመለከተ በአማራ ክልል ሰላማዊ ሰልፎች በማካሄድ ህዝቡን ማነሳሳት እና ትግሉ ከአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም አቅጣጫ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልገናል›› በሚል ላቀረብኩት ሀሳብ አቶ ጌታነህ ባልቻ እና አቶ ይድነቃቸው የሰጡት ምላሽ ‹‹ሀገሪቱን ወደ አለመረጋጋት እና ረብሻ መውሰድ ለሚፈልጉ ሀይሎች አላማ መማገድ አንፈልግም አሁን በኦሮሚያ ያስነሱት ነገር አለ በሌላም አካባቢ ያንኑ ነው ማድረግ የሚፈልጉት ለእነዚህ ሀይሎች መማገድ አንፈልግም፡፡ ማን ምን እንደሆነ እናወቃለን፡፡›› የሚል ነበረ፡፡ የዚህ ስብሰባ ቃለጉባኤ በድምፅም ሪከርድ የተደረገ በመሆኑ ይህንን ማለታቸውን እነሱም የሚክዱት አይመስለኝም፡፡ የሆነው ሆኖ እኛን (ዮናታን፣ እኔ፣ ዮናስ እና ጋሻነህን) በሌላ ፓርቲ አባልነት በይፋ ስለከሰሱን አይደንቀኝም ግን እንዲህ ባለ ወሳኝ የትግል ወቅት ስራ መስራት ለሌሎች ሀይሎች መማገድ የሚሆነው እንዴት ነው; ስራ አስፈፃሚው ምንም ስራ እየሰራ አይደልም ለዚህም ተጠያቂው ሊቀመንበሩ ነው የሚል ክስ ለማቅረብ ሲባል ሊሰሩ የሚችሉ ነገሮችን በሙሉ በማሰናከል ፓርቲውን አሳስሮ ማስቀመጥ ምን የሚሉት ነው;
የብሄራዊ ምክር ቤቱ የእነ ዮናታን ጉዳይ ወደ ዲሲፕሊን ይመራ ተብሎ ተወስኗል የተባለው ጥቅምት 14 ቢሆንም ሳንከሰስ ብዙ ጊዜ ከቆየ በኋላ ህዝባዊ ትግሉ ሲፋፋም፣ የተራራቁ ሀይሎች ሲቀራረቡ፣ በተለይም በኦፌኮ እና በሰማያዊ መካከል መልካም ግንኙነት ሲፈጠር ጠብቆ የክስ ቻርጅ የደረሰን ህዳር 27 ቀን ነበር፡፡ ይከሰሱ ከተባልን ከአንድ ወር ከ 15 ቀን በኋላ ማለት ነው፡፡ ተባረሩ የሚለው ብይን ደግሞ የመጣው የበለጠ ቁርጥ በሆነ ሰዓት፡፡ ይህንንም ይዞ ወደ ሚዲያ መሮጥ፡፡ ይህ ምን አይነት ስራ ነው; መከሰሳችንን አውቀን ሊወሰንብን የሚችለውንም ውሳኔ እያወቅን፣ ውሳኔውንም በሪፖርተር ይፋ ከሆነ በኋላ ሁሉ ዝምታን የመረጥነው ወቅታዊው ህዝባዊ ትግል ላይ ምንም አይነት ጥላ ላለማጥላት በሚል ነበር፡፡ አንዳንዶች አንደውም የእኛ መባረር አስቆጥቷቸው በማህበራዊ ሚድያ ብዙ ነገር ሲሉ እኛ ለማረጋጋት ስንሞክር ነበር፡፡ በተለይም የሪፖርተር ዜና እንደወጣ ፓርቲው ጉዳዩን ግልፅ ያድርግ የሚለው ጫና እስኪበረታ ድረስ ዝምታን መርጠን ነበር፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ግን የይልቃልን 160 ሺህብር ዘርፏል ተብሎ ክስ መመስረታችንን ነገረ ኢትዮጵያ ካልዘገበችልን በማለት አሁን በእስር ላይ የሚገኘውን ጌታቸው ሽፈራውን እንዲሁም በላይ ማናየን ደጅ ሲጠኑ እንደከረሙ የሚታወቅ ነው፡፡

ከድርጅት ፖለቲካ ውጭ ያለው የህበረተሰብ ክፍል ማን ምን አለ ማነው እውነተኛ የሚለውን ጉዳይ በጥሞና ከመመርመር ይልቅ ‹‹እንደልማዳቸው ተጣሉ›› በሚል ተስፋ መቁረጥ ነው የሚቀናው በማለት ትከሻችንን አስፍተን ብዙ ነገር ችለን ተቀምጠናል፡፡ አፋችንንም ወደመ መሬት ቀብረን ምንም ነገር ከማለት ተቆጥበን ቆይተናል፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር በጋዜጣ ከወጣ በኋላ ዝም ማለት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናልና አስተዋዮች ያስተውሉት ዘንድ ሁሉን ነገር ግልፅ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አጊንቼዋለሁ፡፡
‹‹ሰማያዊን እናድን›› በሚል የብዕር ስም በፌስቡክ የሚፅፉት እነዚህ ግለሰቦች ለረጅም ጊዜ የተፈጠረ ያልተፈጠረውን ሁሉ ሲፅፉ በራሳቸው ስም በይፋ እስኪፅፉ ድረስ ጠበቅናቸው እንጂ መልስ የሰጠ አልነበረም፡፡ ፀሀፊዎቹ እነማን አንደሆኑ ሳናውቃቸው ቀርተን ሳይሆን ጉዳዩን ንቆ በመተው ነበር፡፡

ሁለት፡-

ደንብን እና መርህን ያልተከተለ አሰራር ምንድነው;
ጥቅምት 14 በተካሄደው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ እነዮናታን ይከሰሱ ተብሎ ሲወሰን 13/12 በሆነ የድምፅ ልዩነት ነው፡፡ በስብሰባው ላይ የድምፅ ብልጫ እንዲኖር ድምፁን የሰጠው እንዳሻው እምሻው የምክር ቤት አባል አይደለም፡፡ በፈጠረው የድምፅ ልዩነት ብቻ ሳይሆን ድምፅ መስጠት የሌለበት ሰው በስብሰባው ተገኝቶ ድምፅ በመስጠቱ ብቻ ስብሰባው ህገወጥ (invalid) ነው፡፡እንዳሻው በዚያ ስብሰባ ላይ እነዚህ ልጆች ፕሮግራሙን በቀይ እስኪቢርቶ ሰርዘውታልና መባረር አለባቸው በማለት ሲከራከርም ነበር፡፡ /በነገራችን ላይ እንዳሻው ከዚያ ስብሰባ (ጥቅምት 14) በኋላ በሌላ የምክርቤት ስብሰባ አልተሰበሰበም፡፡/ የክስ ቻርጁ እንደደረሰን ለዲሲፕሊን ኮሚቴ ምክርቤቱ አልከሰሰንም ብለን የእንዳሻውን ጉዳይ ጠቅሰን መልሰን ነበር፡፡ በዲስፕሊን ኮሚቴዋ ሰብሳቢ ሀና ዋለልኝ በኩል በደብዳቤ የተሰጠን መልስ ግን ከሳሻችሁ ምክርቤቱ ሳይሆን አቶ ይድነቃቸው በግላቸው ነው የሚል ነው፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ግን በደረሰን የክስ ቻርጅ ላይ ከሳሽ፡- የሰማያዊ ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ነው የሚለው፡፡ ይህንን ከፅሁፉ ጋር ባያያዝኩት የፎቶ ማስረጃ ላይ በግልፅ የሚታይ ነው፡፡

እንግዲህ እኛ በማስረጃ አስደግፈን አልተከሰስንም ስንል ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ደግሞ ኮሚቴ ደግሞ ይግባኝ ጠይቁ ይለናል፡፡ ባልተከሰስንበት ጉዳይ እንዴት ነው ይግባኝ የምንጠይቀው; ማነው እዚህ ጋር ደንብ የጣሰው;

ጉዳዩ እዚህ ላይ ብቻም አያቆምም የዲሲፕሊን ኮሚቴ አራት ሆነው ከተሰበሰቡ በኋላ ከአራቱ አንዱ ቃለጉባኤ ቀይራችሁ አምጥታችኋል የተነጋገርነው እንደዚህ አልነበረም ስለዚህ አልፈርምም ባለበት ሁኔታ (ይህ ማለት የዚህ ግለሰብ ድምፅ በተቃውሞ፣ በድጋፍ፣ አሊያም በተአቅቦ አልተመዘገበም ማለት ነው) ኮረም ሳይሞላ በተላለፈ ብይን ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ይግባኝ ጠይቁ እያለን ነው፡፡ ማነው ደንብ የጣሰው ታዲያ;
በሰማያዊ ደንብ መሰረት የሰማያዊ ፓርቲ የፅህፈት ቤት ሀላፊ በሊቀመንበሩ እና በምክርቤት ሰብሳቢው በጋራ አቅራቢነት የሚመረጥ ሆኖ ሳለ የሰማያዊ ሊቀመንበር አሁን ያለው የሰማያዊ የፅህፈት ቤት ሀላፊ እንዲቀየርለት በይፋ በደብዳቤ ከጠየቀ ከ3 ወር በላይ ቢሆነውም አቶ እንዳሻው ግን በጉልበታቸው ቢሮውንም አለቅም ማህተምም አልመልስም ብለው ቁጭ ካለ በርካታ ወራት ሆነው፡፡ ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ይህንን ህገወጥ ድርጊት ከማስቆም ይልቅ ከዚህ ህገወጥ ድርጊት ጋር ተባብሮ መቆምን መርጧል፡፡(በነገራችን ላይ የዶ/ር መራራን እና የይልቃልን ስብሰባ ለማደናቀፍ የመብራት ቆጣሪ ያበላሸው ይኸው ግለሰብ ነው) እንግዲህ ደንብን ማስከበር የሚገባው አካል ደንብን ጥሶ ከተገኘ ምን ማድረግ ይቻላል?

Eyasped Tesfaye's photo.
Eyasped Tesfaye's photo.
Eyasped Tesfaye's photo.