የሪፖርተር ጋዜጣ ዜና እና የዞን ዘጠኙ ጦማሪ በፍቃዱ ዘሃይሉ ስለ ሰማያዊ ፓርቲ እና ስለተባረሩት ኣባሎቹ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የሪፖርተር ጋዜጣ ዜና እና የዞን ዘጠኙ ጦማሪ በፍቃዱ ዘሃይሉ ስለ ሰማያዊ ፓርቲ እና ስለተባረሩት ኣባሎቹ …………..
ሪፖርተር ጋዜጣ :- ሰማያዊ ፓርቲ ቀደም ብለው በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከፓርቲው ማግለላቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ያስታወቁትን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊውን አቶ ዮናታን ተስፋዬን ጨምሮ፣ አራት አባሎቹን ማሰናበቱን አስታወቀ፡፡
ፓርቲው ከጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አቶ ዮናታን ተስፋዬን፣ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑትን አቶ እያስፔድ ተስፋዬን፣ አቶ ጋሻዬነህ ላቀና አቶ ዮናስ ከድርን የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ ተላልፈው በመገኘታቸው፣ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከፓርቲው እንዲወገዱ ማድረጉን ገልጿል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የብሔራዊ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ኃላፊ ሃና ዋለልኝ ፊርማ የተላለፈው ውሳኔ እንደሚያስረዳው፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 42(5) ሥር ከባድ የሥነ ሥርዓት ቅጣት ስለሚያስከትሉ ጥፋቶች ተደንግጓል፡፡ የፓርቲውን ዓላማ፣ ፕሮግራምና ፖሊሲ መፃረር አይቻልም፡፡ በመሆኑም የተጠቀሱት አባላት ደንቡን በመተላለፋቸው ቅጣቱ እንደተላለፈባቸው አስታውቋል፡፡
አቶ ዮናታን በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የታሪክና የጎሳ ጥላቻ ያላቸው ቅስቀሳዎችን በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና የተለያዩ የአገሪቱን ቀደምት መንግሥታት ታሪኮች ያጎደፈ፣ ለጥላቻ የሚያነሳሳ፣ በሕዝብ መካከል የባህል መከባበር እንዳይኖር የጥላቻ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ፓርቲው በውሳኔው አስታውቋል፡፡ ሌሎቹም የተሰናበቱት አባላት ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸማቸውን በማብራራት ከፓርቲው መሰናበታቸውን ገልጿል፡፡
ከታች የምታዩት ዜና ከሪፖርተር ላይ የተቀነጨበ ነው – ሰማያዊ ፓርቲ ዮናታንን ያባረረበትን ምክንያት ይዘረዝራል። Eyaspedም ተባሯል። ሌሎች ሁለት ሰዎችም ተባረዋል።
፩ኛ) ዮናታን ከመባረሩ በፊት ራሱን ከፓርቲው አሰናብቷል፤
፪ኛ) ታስሯል።
ዮናታን ራሱን ካሰናበተ በኋላ፣ መንግሥት ሲያፍነው ከመንግሥት ዕኩል ሥም ሰጥቶ መወንጀሉ ሰማያዊን ምን ያክል ያስኬደዋል? (የሞራል ጥያቄ ነው) በዚህ ዓይነት እኮ መንግሥት ዮናታን ላይ የሰማያዊን መግለጫ አምጥቶ ሊከሰው ይችላል። ዮናታን (እና እያስጴድ፣ እና ሌሎችም…) ሰማያዊ ከተመሠረተበት አቋም የማፈንገጥ አዝማሚያ አሳይተዋል። ሆኖም፣ የሰማያዊ ፕሮግራም የማይጠየቅ ቅዱስ ቃል አይደለም። ሰማያዊ ፓርቲ የገዛ ልጆቹን በሐሳብ ረትቶ ውስጡ ማቆየት ካልቻለ አዳዲሶችን እንዴት ማምጣት ይችላል? “ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” እንዲል የክርስቲያኖች መጽሐፍ።
የዮናታንን የመጨረሻ አቋም ፌስቡክ ላይ ሳነብ ነበር። ዮናታን ከጠባብ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ሌሎችንም (የተገለሉትን ወይም እንደተገለሉ የሚሰማቸውን) አካታች ወደሆነው ሰፊ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ለመሸጋገር እየተፍጨረጨረ ነበር። ሙሉ ለሙሉ አልተሳካለት ይሆናል። ነገር ግን በቀና ልቦና አንድ አቋም እንደቀኖና ሳይይዝ ትክክለኛ መንገድ ለማግኘት እየተፍጨረጨረ እንደነበር እወራረድለታለሁ።
ሰማያዊ ፓርቲ አባሎቹም ይሁኑ ሌሎች የሚያነሱበትን እንከን መርምሮ ከጥያቄዎቹ በላይ ሆኖ መገኘት ሲገባው፣ በኔ እይታ የወሰደው እርምጃ የሚያሳንሰውን ነው። የወሰደው እርምጃ በሥነ ስርዓት ደንቡ ተገቢ ሊሆን ይችላል። የሥነ ስርዓት ደንቦች የሐሳብ ብዝኃነቶች የሚገድቡ ከሆኑ ግን ፍትሓዊ ርትዓዊ አይደሉም። ዮናታን በሰማያዊ የተወነጀለው ሐሳቡን በመግለፁ ነው። መንግሥትም ዜጎቹን የሚከሰው በተመሳሳይ አጀንዳ አለባብሶ ነው።
ሰማያዊ ፓርቲ የአሁኖቹ መሪዎች ሲተቹ ቅሬታ የሌለበትን ያክል የቀድሞ መሪዎችም ሲተቹ፣ ቢያንስ እንደነፃነት መቀበል ነበረበት። እንደእውነቱ ሁላችንም እየከፈልን ያለነው የቀድሞ አባቶቻችንን ዕዳ ነው። ጣጠኛ አገር አስረከቡን እንጂ ጣጣዋ ያለቀ አገር አላስረከቡንም። መግባበት በሌለበት የቀድሞ ታሪክ ላይ የፓርቲ አባላት ቢሳሳቱ እንኳን የመታረም ዕድል ነበር የሚያስፈልጋቸው፤ «የቀድሞ ወዳጅክን በምን ቀበርከው ቢሉ በሻሽ፣ የኋለኛው እንዳይሸሽ» አይደለም ከነተረቱ?!