[ክቡር ሚኒስትሩ የአለቃቸው ልጅ ልታገባ መሆኑን ሰምተው፣ በራሳቸው ተነሳሽነት ሠርጉን የሚያስፈጽም ኮሚቴ ሊያዋቅሩ ተዘጋጅተዋል፡፡ አማካሪያቸውም በአፋጣኝ ወደ ቢሯቸው እንዲመጣ አደረጉት]
–    ምነው በአፋጣኝ ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
–    አንገብጋቢ ጉዳይ መጥቶ ነው፡፡
–    የምን አንገብጋቢ ጉዳይ?
–    ትልቅ አዲስ አገራዊ ፕሮጀክት ከፊታችን ተደቅኗል፡፡
–    አዲስ አገራዊ ፕሮጀክት?
–    አዎን አዲስ አገራዊ ፕሮጀክት፡፡
–    ግድብ ነው ክቡር ሚኒስትር?
–    የጀመርነውን ሳንጨርስ ሌላ ግድብ አማረህ?
–    ታዲያ የባቡር ፕሮጀክት ነው?
–    እሱንማ አጠናቀቅን፡፡
–    የስኳር ፕሮጀክት ነው?
–    የስኳር ፕሮጀክት ነበረን ለካ?
–    የማዳበሪያ ፕሮጀክት ነው ክቡር ሚኒስትር?
–    አንተ በዚህ ከቀጠልክ  የሞቱ ዘመዶቼን ልታስታውሰኝ ትችላለህ፡፡
–    የምን ፕሮጀክት ነው ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
–    ትልቅ ልማታዊ ሠርግ ከፊታችን ተደቅኗል፡፡
–    ልጅዎት ልታገባ ነው እንዴ?
–    እኔ የልጄን ሠርግ እንደ ትልቅ ፕሮጀክት የምቆጥረው ይመስልሃል?
–    ታዲያ የማን ሠርግ ነው?
–    የአለቃዬ፡፡
–    አለቃዎት ሊያገቡ ነው?
–    የለም ልጃቸው ልታገባ ነው፡፡
–    ግን ክቡር ሚኒስትር …
–    የምን ግን ነው?
–    ሠርጉ እኮ የቤተሰቡ የግል ጉዳይ ነው፡፡
–    ጤነኛ ነህ ግን አንተ?
–    እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
–    ከዚህ የበለጠ የአገር ጉዳይ አለ?
–    ኧረ የለም፡፡
–    ከተማችን ውስጥ ተደግሶ የማያውቅ ድል ያለ ሠርግ ነው የምንደግሰው፡፡
–    አለቃዎት ያውቃሉ ግን?
–    ሰርፕራይዝ ነው፡፡
–    አይ ፈርቼ ነው እኮ፡፡
–    ምንድን ነው የፈራኸው?
–    ሰርፕራይዙ እርስዎን ራስዎትን ሰርፕራይዝ እንዳያደርግዎት፡፡
–    ስለእሱ አታስብ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ፡፡
–    ስለዚህ ምን ይደረግ?
–    ኮሚቴ መቋቋም አለበት፡፡
–    ምን የሚሉት?
–    በራስ ተነሳሽነት ሠርጉን የሚያስፈጽም ኮሚቴ፡፡
–    እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    እዚህ ላይ ትኩረት እንዲሰጣቸው የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡
–    ምንድን ናቸው ክቡር ሚኒስትር?
–    በመጀመሪያ ይህ ፕሮጀክት ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው፡፡
–    እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ሲቀጥል ይህን ፕሮጀክት እንደ ማሳያ መጠቀም ስለምንፈልግ ከፍተኛ ርብርብ እንዲደረግበት እፈልጋለሁ፡፡
–    ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ስለዚህ ፕሮጀክቱን ከግብ ለማድረስ ሁላችንም ቀን ተሌት ደከመን ሰለቸን ሳንል መሥራት አለብን፡፡
–    ነጥቦቹን ይዣቼዋለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ከዚህ ባለፈ ማድረግ ያለብን ነገሮች አሉ፡፡
–    ምን ክቡር ሚኒስትር?
–    በዋናው ኮሚቴ ሥር ሦስት ንዑስ ኮሚቴዎች መዋቀር አለባቸው፡፡
–    ምን ዓይነት ኮሚቴዎች?
–    የመጀመሪያው የከብት አፈላላጊ ኮሚቴ ነው፡፡
–    ሁለተኛውስ?
–    የከብት ግዢ ኮሚቴ ነው፡፡
–    የመጨረሻው ምንድን ነው?
–    ሦስተኛው የከብት አራጅ ኮሚቴ ነው፡፡
–    እነዚህ ኮሚቴዎች ያስፈልጋሉ ግን?
–    ስማ ይህ ፕሮጀክት ፍጹም ከሙስና የፀዳ መሆን አለበት፡፡
–    ለዚህ ነው ኮሚቴዎቹ የበዙት?
–    ነገርኩህ እኮ፣ እያንዳንዱ የሥራ ሒደት ግልጽ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት፡፡
–    ስለዚህ ኮሚቴዎቹ እንዴት ይዋቀሩ?
–    የምታዋቅርበትን መንገድ አሁን እነግርሃለሁ፡፡
–    ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    በኮሚቴዎቹ የብሔር ስብጥር የተመጣጠነ መሆን አለበት፡፡
–    ጥሩ ነጥብ ነው ያነሱት፡፡
–    ሲቀጥል አባላቶቹ መመረጥ ያለባቸው ከፎረሞቹ ነው፡፡
–    ከየትኞቹ ፎረሞች?
–    ከሴቶች ፎረም፡፡
–    እሺ፡፡
–    ከወጣቶች ፎረም፡፡
–    ሌላስ?
–    ከነጋዴዎች ፎረም፡፡
–    የደላሎች ፎረምስ ይግቡበት?
–    ምን ነክቶሃል?
–    ምነው ክቡር ሚኒስትር?
–    ደላሎችን ለማጥፋት ቆርጠን በተነሳንበት ወቅት ጭራሽ ኮሚቴ ውስጥ ደላላ ልታስገባልኝ?
–    አይ ክቡር ሚኒስትር የከብት ገበያው እኮ በደላላ ነው የሚመራው ብዬ ነው፡፡
–    ቢሆንስ ታዲያ?
–    እነሱን ካልያዝን ይህን ፕሮጀክት በድል መወጣት አንችልም ብዬ ነው፡፡
–    ለነገሩ ልክ ብለሃል፡፡
–    አዲሱን አባባል አልሰሙም እንዴ?
–    ምን የሚለውን?
–    ለማንኛውም ድል፣ ያስፈልጋል ደላላ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ሌላ ሚኒስትር ጋ ስልክ ደወሉ]
–    እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
–    ይኸው በአዲሱ ፕሮጀክት ተወጥረናል፡፡
–    የምን አዲስ ፕሮጀክት መጣ?
–    አገራዊ ፋይዳ ያለው ታላቁ ፕሮጀክት ነዋ፡፡
–    ስለግድቡ ነው የሚያወሩት?
–    ሰው ሁሉ ከግድቡ ሌላ የሚያውቀው ነገር የለም እንዴ?
–    ታዲያ ስለየቱ ፕሮጀክት ነው የሚያወሩት?
–    ስለ አለቃችን ልጅ ሠርግ ፕሮጀክት ነዋ፡፡
–    እርስዎ እኮ አስተዋሽ ነዎት፡፡
–    ለዚህ አይደል እንዴ እኔ የማስፈልገው፡፡
–    ምን እየታሰበ ነው ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
–    አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ በውስጡ ሦስት ንዑስ ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡
–    ታዲያ እኔ ምን ልርዳዎት?
–    ኮሚቴው የሚንቀሳቀስበት በጀት ያስፈልገዋል፡፡
–    ታዲያ ተጨማሪ በጀት በፓርላማ እናስፈቅድ?
–    እሱ አንድ አማራጭ ነው፡፡
–    ካልሆነ ከሠራተኞች ደመወዝ ተቆራጭ ማድረግ ይቻላል፡፡
–    ይኼንንም እንደ ሌላ አማራጭ ማየት እንችላለን፡፡
–    ከዚህ ባለፈ ደግሞ ቦንድ መሸጥ እንችላለን፡፡
–    የአገር ውስጥ ወይስ የውጭ?
–    ግዢው የሚፈጸመው በውጭ ምንዛሪ ከሆነ የዩሮ ቦንድ ሽያጭ ማድረግ እንችላለን፡፡
–    ይሄ የተሻለ ሐሳብ ሳይሆን አልቀረም፡፡
–    ስለዚህ ዩሮ ቦንድ ይሁን?
–    በቃ ዩሮ ቦንድ!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
–    ሦስቱም ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፡፡
–    በጣም ጥሩ፡፡
–    የኮሚቴዎቹ ሰብሳቢዎችም እዚህ ስላሉ ቢያናግሯቸው ጥሩ ነው፡፡
–    አስገባቸው፡፡
[የኮሚቴዎቹ ሰብሳቢዎች የክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገቡ፡፡ ከከብት አፈላላጊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋር ውይይታቸ    ውን ቀጠሉ]
–    በመጀመሪያ ክቡር ሚኒስትር የዚህ ኮሚቴ ሰብሳቢ አድርገው ስለሾሙኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
–    ሹመት ቀላል ነገር አይደለም፣ ኃላፊነትም አለበት፡፡
–    አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ዋናው ሥራህ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
–    እሱን ከእርስዎ ለመቀበል ነው የመጣሁት፡፡
–    ያው የኮሚቴው ስም እንደሚገልጸው፣ ዋናው ሥራህ ከብት ማፈላለግ ነው፡፡
–    መፍትሔ የማፈላለግ ሥራ ነው ያሉኝ?
–    ከብት የማፈላለግ ሥራ፡፡
–    ከየት ልጀምር ከካራ፣ ከሰበታ ወይስ ከቡራዩ?
–    እንዲህ አቅልለህ አትየው፡፡
–    እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
–    ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ ከሆነ ከአውሮፓም ሆነ ከእስያ አማርጠን ዓይተን ነው ከብቶቹን የምንገዛው፡፡
–    ደስ ይለኛል ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ስለዚህ ከብቶቹ ልማታችን በግልጽ የሚናገሩ መሆን አለባቸው፡፡
–    እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    በዛ ላይ አረንጓዴ ኢኮኖሚን የሚያመላክቱ መሆን አለባቸው፡፡
–    አረንጓዴ ከብት አለ እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
–    ከፈለግህ አረንጓዴ ቀለም ቀባቸው፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከከብት ገዢ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋር መወያየት ጀመሩ]
–    የአንተ ዋነኛ ሥራ በአፈላላጊ ኮሚቴው ሪኮመንዴሽን መሠረት የከብት ግዢውን መፈጸም ነው፡፡
–    ምንም ችግር የለውም ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ስለዚህ የግዥ ሥርዓቱ ግልጽና ከሙስና የፀዳ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡
–    ስለዚህ ግልጽ ጨረታ እናውጣ ማለት ነው?
–    ግልጽ ይሁን ውስን የሚለው በኋላ የሚታይ ጉዳይ ይሆናል፡፡
–    ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ወይስ ለውጭ ኩባንያዎች ይሰጥ?
–    እሱ ከውጭ ምንዛሪ ጋር የሚያያዝ ስለሆነ በኋላ እንወስናለን፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከከብት አራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጋር መወያየት ጀመሩ]
–    ሚኒስትር ጋ ስትመጣ እንኳን ፕሮቶኮልህን አትጠብቅም?
–    ክቡር ሚኒስትር ያው ከተማ ውስጥ ብዙ የእርድ ሥራዋች ስለነበሩብኝ ነው፡፡
–    የምን እርድ?
–    እርድ እኮ በየቦታው ነው ያለው፤ ነጋዴው ያርዳል፣ ባለሥልጣኑ ያርዳል፣ ካድሬው ያርዳል፣ ብቻ ብዙ እርድ አለ፡፡
–    ለማንኛውም ይህ የእርድ ኮሚቴ ዓለም ላይ አለ የተባለውን የእርድ ቴክኖሎጂ መጠቀም አለበት፡፡
–    በደስታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    እዚህ ላይ የዕውቀት ሽግግር መኖሩን ማረጋገጥ አለብን፡፡
–    ልክ ብለዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
–    አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    እነዚህ ኮሚቴዎች ውስጥ ራሴ መግባት እፈልጋለሁ፡፡
–    ስለዚህ ኮሚቴዎቹ ለእርስዎ ሪፖርት ያድርጉዋ፡፡
–    ከዚያም ባለፈ ሥራዎቹ ላይ መሳተፍ እፈልጋለሁ፡፡
–    ለምን?
–    በቃ ፕሮጀክቱ እንዲደናቀፍ ስለማልፈልግ፣ ራሴው መግባት አለብኝ፡፡
–    ስለዚህ ምን ላድርግልዎት?
–    ለእኔና ለከብት አፈላላጊው የፕሌን ትኬት ግዛልን፡፡
–    ወዴት ሊሄዱ?
–    ወደ አውሮፓና እስያ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአውሮፓ ሆነው ለሚስታቸው ደወሉ]
–    ምን ዓይነት ፕሮጀክት ገጥሞህ ነው እንዲህ የዘጋኸኝ?
–    ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ይዤ ነው፡፡
–    እኮ ምን?
–    በስልክ አይወራም፡፡
–    ለማንኛውም ባልሽ የት ሄዶ ጠፋ ብሎ ብዙ ሰው ጠየቀኝ፡፡
–    ብዙ ሰው ደግሞ የት አግኝተሽ ነው?
–    ሠርጉ ላይ ነዋ፡፡
–    የማን ሠርግ?
–    የአለቃህ ልጅ፡፡
–    አለፈ እንዴ?