‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› ለአቶ ጥላሁን እንደሻው — ( እዮብ አለም)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› ለአቶ ጥላሁን እንደሻው–
ዛሬም መሸፋፈንና ማላከክ እንደዕውቀት? ጃንዋሪ 3/2015 በዚሁ ገጽ ላይ በዋነኛነት መድረክ ከሰማያዊ ጋር በትብብር ለመስራት የጀመረውን ግንኙነት በሚመለከት ከጅምሩ የገጠመውን ደንቃራና በቀጣይም ሊያጋጥመው የሚችለውን ፈተና በሚመለከት ከመድረክ አባላት/ውስጥ አዋቂ ምንጮች የተገኘው መረጃና ሂደቱን በመሰረት በማድረግ የቀረበውን ጽሁፍ በሚመለከት ‹‹ የተቃዋሚዎች ትብብር የሚያንገበግባቸው የሽፍንፍን ኢህአዴጎች መፍጨርጨር ሲጋለጥ ›› በሚል ርዕስ የሰጡትን መልስ በጥሞና ተመልክተነዋል፡፡
ለእርስዎ አረዳድ የምንሰጠው ቦታ እንዳለ ሆኖ በመጀመሪያ ርዕሱና ይዘቱ አይገናኝም ፤ ርዕሱ ስለሽፍንፍን ኢህአዴጎች ሆኖ ይዘቱ በተጠቀሰው ጽሁፍ የተገለጹትን መረጃዎችና በሂደቱ በተጨባጭ በአደባባይ የታዩትን እውነታዎች በጠረጠሯቸው ግን ባልጠቀሷቸው ሽፍንፍን ኢህአዴጎች መቀናበራቸውን፣ ይህም የትብብር ጥረቱን ለማደናቀፍ መሆኑን በመረጃና የሂደቱን ትክክለኛነት በማሳየት ከመሞገት ይልቅ በጽሁፉ የተነሱትን ግለሰቦችና ድርጅቶች እንኳ ሳያነሳ አንድ ግለሰብን ለመከላከል ብቻ መጻፉን ያመለክታል፡፡ ዋናውና የመከራከሪያ ማዕከላዊ ኃሳቡን ትቶ ወይም በ‹‹ሾላ በድፍኑ›› አልፎ ጉዳዩን የፕ/ር በየነና የባለቅሬታ አባላት አድርጎ ለማሳነስ መሞከር ከግምት ይጥላል፡፡
የእኛ ጽሁፍ ዓላማ የመድረክ/ሰማያዊ የተለመደው ዓይነት የይስሙላ ግንኙነት በአገራዊ ትግላችን ላይ የሚያስከትለው ችግር ከወዲሁ ታውቆ ተገቢው እርምት እንዲወሰድ የሚያሳስብ ስለመሆኑ ንጹህና ጤናማ /ሚዛናዊ አዕምሮ ያለው በቀላሉ ሊገነዘብ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ጽሁፉዎን ያነበቡ የእናንተው ደጋፊዎችም ትዝብት ማሳደራቸውን መረዳት ተችሏል፡፡ ከመግቢያዎ ላይ የጽሁፉን ዋና ጭብጥና በመረጃነት የተነሱትን ተዛማጅ ጉዳዮች በትክክል ከመግለጽዎ ውጪ ስለነዚህ ኃሳቦችም ሆነ በማሳያነት በቀረቡት አምስት ነጥቦች ላይ አንድም አስተያየት ሳይሰጡ ለፕ/ር በየነ መወድስ በማቅረብ ታማኝነትዎን ለማረጋገጥ ያደረጉት ጥረት ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡ አይጠበቅብዎትም፣ ከግምት ጥሎዎታል፡፡ በአጠቃላይ ስለጽሁፍዎ በጥቅሉ ይህን ያህል ካልን በኋላ ነጥብ በነጥብ እንመልከት፡፡
1ኛ/ እርስዎ በበኩልዎ የመድረክና ሰማያዊ መልካም ግንኙነት እንደሚቀጥልና ሌሎች ሀቀኞችንም አስተባብረው ለትግል እንደሚያበቁ እምነት ባሳደሩበት ከቀናት በኋላ ፕ/ር በየነ ከሰማያዊ ጋር የተጀመረው ግንኙነት ‹‹በጋራ ሰልፍ ከመጥራት ያለፈ ያለመሆኑን ገልጸው መጻፋቸውን›› በዚህም የኦፌኮ አባላት ቀድሞ የፕ/ሩ ደጋፊ ናቸው የሚባሉትን የተሻረውን ደብዳቤ ያረቀቁትን ጨምሮ በፕ/ሩና በእናንተ ላይ ተስፋ የቆረጡበትን እውነታ እንዴት ያዩታል፣ወይስ ይህም የኢህአዴግ ወሬ ነው ? እርስዎ እንዳሉት ሆኖ የኢህአዴግ ወሬ ቢሆን ምንኛ ታድለን ነበር፡፡
2ኛ/እርስዎ ስለፕ/ሩ ያለዎትን ተጨባጭ ማስረጃ ተንተርሰው ‹‹…የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተባበረ የጋራ አቋም አምባገኑን ሥርዓት እንዲፋለሙ በማስተባበር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ የቆዩ በመሆናቸው ፣የኢህአዴግ ፕሮፖጋንዲስቶች ዒላማ ….›› መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህን ከፍተኛ ተግባር የፈጸሙት በአገራችን ውስጥ ወይስ ስለሌላ አገር ነው የሚያወሩት፣ ስለእኛው መድረክ ወይስ ከ1986 ጀምሮ የነበሩ ጥረቶችን ማክሸፋቸው ነው ‹‹ከፍተኛ አስተዋጽኦ››የተባለው ወይስ እኛ የማናውቀው እርስዎ ብቻ የሚያውቁት በርሳቸው አስተባባሪነት የተመዘገበ ድል/ውጤት አለ? ይገለጽልን፡፡
3ኛ/ እርስዎ ስለሌላው ማስተባበር ሲያነሱ በምርጫ 2007 ከተሳተፉት የመድረክ አባል ፓርቲዎች ብቸኛው አገርአቀፍ ፓርቲ የእናንተው ኢማዴ-ደኅ ፓርቲ ሆኖ ስንት ዕጩ አቀረበ ፣ ከሌሎቹ ሁለት ክልልና አንድ ዞን ከሚሸፍኑት የአንድ ብሄር /ብሄረሰብ ድርጅቶች ሲኣን፣ዐረና ኦፌኮ/ በስንት ያህል የበለጡ አባላት በዕጩነት አቀረበ፣የዚህ መልስ የማስተባበር ልምዳቸውን ያሳያልና መልስዎትን ይስጡን፡፡ ከዚህ ውጪ በአሁኑ ጊዜ ያለው ተጨባጭ እውነት የመድረክ/ሰማያዊ ግንኙነት በጋራ ሰልፍ ተገድቧል፣ ሰማያዊ ግንኙነቱን የሚቀጥል ከሆነ ሊሆን የሚችለው ከመድረክ አባል ድርጅቶች ጋር እንጂ እንደርስዎ እምነት አይደለም፣ እርስዎ የሚጽፉላቸው ደሞዝ ከፋይዎ አይደለም ከሰማያዊም ሆነ ሌሎች ጋር ግንኙነት ለማጠናከርና ትብብሩን ማስፋት መድረክን አባላትም ለትርጉም ያለው ግንኙነትና ተግባር ለማብቃት የመቻላቸው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል፡፡
አብረን እየሰራንም ‹‹እርሳቸው ›› ላይ ከደረስን የኢህአዴግ ፕሮፖጋንዲስቶች ከተባልን በተጨባጭ ማን ምን እንዳለና እንደተገበረ፣ ምን ውጤት ላይ እንደተደረሰ የሚለይበት ጊዜ ቅርብ ነውና ፍርዱን ለህዝብ እናቆየው፡፡፣ እስከ ታሪክና ትውልድ አይቆይምና፡፡ በመጨረሻም የኢሶዴ-ደኅ ፓርቲና የዐረና ውህደት ስንት ዓመታት ነው የሚፈጀው? ብዙ ጉዳዮች እየነቀስን ጥያቄ ማቅረብ ብንችልም ለዛሬው ለነዚህና ባለፈው ላነሳናቸው መልስ ካለዎት በጨዋ ደንብ ይዘው ከቀረቡ ለመወያየት/ለመከራከር ዝግጁ ነን፡፡ ለእኛ ማሳመኛ ከዚህ በላይ በርካታ ተጨባጭ መረጃዎችና ማስረጃዎች ቢኖሩንም የእርስዎን መልስ እንስማ – ምናልባትም ወደ ኅሊናችሁ መጥታችሁ ክህደቱንና ማላከኩን ትታችሁ መመለስን ያካትታልና ፤ ያለበለዚያ ጨዋታው አንድም ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ›› በተጨማሪም እርስዎም እንዳሉት ‹‹የተሸፋፈነ›› ይሆናልና በዝርዝር እንመለስበታለን፡፡