የኦሮሚያ ባለቤት ኦሮሞው ነው ይላል የክልሉ ሕግ መንግስት – ግርማ ካሳ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ብዙዎች የማናውቀውና ያላስተዋል አንድ ነገር አለ። ማስተር ፕላን ፣ ማስተር ፕላን የሚለው ጫጫታ ያለዉን መሰረታዊ ችግር እንዳንረዳ አድርጎናል። የትብብር ጥሪ እየቀረበ ነው። ትብብርን በጣም እደግፋለሁ። ግን የምንተባበረው ለምንድን ነው ? ያ በግልጽ መቀመጥ አለበት። ያ ባልሆነበት ሁኔታ ለመተባበር በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።
አንዳንዶች በአገዛዙ ላይ ጥላቻ ስላላቸው “ወያኔን ለማስወገድ ፍላጎት መኖሩ ብቻ” ለመተባበር በቂ ነው ይላሉ። ይሄ በጣም አደገኛ አካሄድ ነው። ደካማ አስተሳሰብም ነው። “ደርግ ይወገድ እንጂ ለምን ሰይጣን አይመጣም” ብለን ከተሞቻችንን ከፍተን ሕወሃትን አስገብተን የሆነውን መርሳት የለብንም።
ወያኔዎችን ስንቃወም ወያኔዎችን ተክቶ የሚመጣው ኃይል መልአክ ባይሆንም ፣ ቢያንስ ከወያኔዎች የባሰ እንደማይሆን አንድ አይነት ማረጋገጫ ማግኘት ያስፈለጋል።
አንድ ነገር አንርሳ አሁን “ኦሮሚያ” የምትባለው ክልል በሕወሃት እና በኦነግ በሕዝቡ ላይ የተጫነች ክልል ናት። ይህ የኦሮሚያ ክልል የራሷ የክልል ሕገ መንግስት አላት። በኦሮሚያ ክልል ሕግ መንግስት መሰረት የኦሮሚያ ባለቤት የ”ኦሮሞ ህዝብ ነው” (አንቀጽ 8) ።
የኦሮሞ ልሂቃን የሌላው ብሄር ብሄረሰብ አባላት ኦሮሚያ ዉስጥ መኖር ይችላሉ እያሉን ነው። ቻይናዎችም እየኖሩ ነው። ግን ሌላው ኢትዮጵያዊ በኦሮሚያ እንዴት ነው የሚታየው ? እርሱም የመሬቱ ባለቤት ነው ወይንስ እንደ ቻይናዎች እንደ alien ፣ እንደ እንግዳ ነው መኖር ይችላል የሚባለው ? ይሄን በግልጽ ሊመልሱልን ያስፈልጋል።
እንግዲህ ቀደም ባሉት ፖስቶችን እንደገለጽኩት መሰረታዊ የሆኑ የመብትና የሕልዉና ጥያቄዎች አሉ። የኦሮሞ ልሂቃን መመለስ ያለባቸው።
1. የኦሮሚያ መሬት የ”ኦሮሞ ብሄረሰብ” ሳይሆን የክልል ነዋሪዎች ሁሉ ነው በሚለው ይስማማሉ ወይ ? የኦሮሚያ ክልል ሕግ መንግስት አንቀጽ 8 የኦሮሚያ ባለቤት የኦሮሞ ህዝብ ነው ሳይሆነ የኦሮሚያ ነዋሪዎች ነው በሚለው ቢሻሻል ችግር ይኖራቸዋል ወይ ?
2. ገበሬው መሬት የመንግስት ነው እየተባለ በጉልበት መፈናቀል እየደረሰበት ነው። ጥቂቶች ሃብታም እየሆኑ ገበሬው ለማኝና ዘበኛ እየሆነ ነው። ብዙ ኦሮሞ ያልሆኑ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ነው እየተባለ (በአንቀጽ 8 መሰረት) ከሚኖሩበት ቦታ እየተፈናቀሉ ነው። የዘር ማጽዳት ወንጀል እየተፈጸመባቸው ነው። ዜጎች የሚኖሩበትን ቤትና የሚያርሱበትን እርሻ በባለቤትነት የመያዝ መብት ካላቸው ግን፣ ገበሬው ካልፈለገ ከመሬቱ አይፈናቀል፣ ልላው ኢትዮጵያዊም ኦሮሞ አይደለህግም ተብሎ አይፈናቀልም። የመሬት ፖሊሲው ከተቀየረ፣ በሁለቱም መንገድ ሲታዩ የነበሩ መፈናቅሎች ይቆማሉ። ገበሬው እንዳይፈናቀል ማድረግ እና የሌሎች ብሄረሰቦች ላይ ከአገራች ዉጡ የሚለው ጸያፍና ዘረኛ ተግባራትን ማስቆም ወቅቱ የሚጠይቃቸው አንገብጋቢ የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ናቸው። ይሄንን የኦሮሞ ልሂቃን ይስማማሉ ወይ ?
እንደ ኢሳት ያሉ ሜዲያዎች ህዝቡ መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ መልስ እንዲያገኝ ማድረግ አለባቸው። ዝም ብሎ ፕሮፖጋንዳ መርጨት አይደለም። ለምሳሌ ዶር በያን፣ ጃዋር ሞሃመድ፣ አቶ ሌንጮ ቀርበዋል። ለምን መጠየቅ ያለባቸውን አይጠይቋቸውም ? መሬት መሸጥ መለወጥ እንዲቻል ገበሬዉ የመሬቱ ባለቤት እንዲሆን በአጭሩ መሬት ላራሹን ይደግፋሉ ወይ ? የኦሮሚያ መሬት የኦሮሞ ብሄረሰብ ሳይሆን የክልሉ ነዋሪዎች ነው ብለው ያማናሉ ወይ ? በዚህ ጉዳይ ላይ አቅርበው በድጋሚ ቢጠይቋቸው መልካም ነው። እንደ አቶ ንአመን እና አቶ ኤርሚክያ ለገሰ ያሉም፣ በነዚህ ነጥቦች ዙሪያ የኦሮሞ ብሄረተኞች ያላቸውን አቋም ሳያውቁ ብዙ ስለትብብር ባያወሩ ጥሩ ነው። ቅድም እንዳልኩት መቅደም ያለበት መቅደም አለበት።