ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ህዝባዊ ቁጣው የኦሮሚያ ሳይሆን የኢትዮጵያ እንዲባል ጠየቁ::
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የሰብዐዊ መብት ተሟጋቹ፣ መምህሩ፣ የተለያዩ ፓርቲዎች መስራች እና አመራር እንዲሁም በተለያዩ መፅሔቶች አምደኛ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ህዝባዊ አመፁ እና ቁጣው የኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ተብሎ እንዲጠራ ጠይቀዋል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን የማህበራዊ ሚዲያዎችን ተጠቅመው “በሁለት ደረጃ የሚቀርቡ ጥያቄዎች አሉኝ፤–
አንድ፡– ግርግሩ የኦሮምያ ነው? ወይስ የኢትዮጵያ? ወይስ ኦሮምያ ከኢትዮጵያ ተለይቷል?
ሁለት፡– የኢትዮጵያ የመሬት ጉዳይ ኦሮሞዎችን ብቻ የሚመለከት ነው? ወይስ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ?” የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተው “አንደኛ፣ ግልጽ ከሆነው እውነት እንነሣ፤ ኦሮምያ ከኢትዮጵያ አልተለየም፤ ስለዚህም ግርግሩ የኢትዮጵያ ነው እንጂ የኦሮምያ አይደለም፤ ጥንቱኑ ለማጋጨት የተሰጠውን ስያሜ በስምነነቱ ከማጽደቅ በላይ ለታቀደው ዓላማ አመቺ መሣሪያ ማድረግ ነው፤ ይህ ደግሞ በቅድሚያ መሸነፍን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ከወያኔ በቀር ደጋፊ ያለው አይመስለኝም፤ ቁርጠኛ ትግል ቁርጠኛ ዓለማና ቁርጠኛ ስልት ያስፈልገዋል፤ ስለዚህም ቁርጠኛ መሪ ያስፈልገዋል፤ የሕመሙን መርዝ እየተጎነጩ ከሕመሙ ፈውስ ለማግኘት አይቻልም፤ ግርግሩ የኦሮሞ ከተባለ ሁለት ውጤቶች ይከተላሉ፤ አንዱ ውጤት ከኦሮሞ በቀር ሌላውን ሕዝብ አያገባውም ማለት ይሆናል፤ ሁለተኛው ውጤት የልየነቱ በላቤቶችና ተፋላሚዎች ኦሮሞዎችና ወያኔዎች ብቻ ናቸው ማለት ነው፤ ይህ ትልቅ አደጋ አለበት፡፡
አደጋው ወደሁለተኛው ጥያቄ ይመራናል፤ ገብቶኝ እንደሆነ የግርግሩ ምክንያት ሁለት ናቸው፤ አንዱ ከቤት-ንብረት መፈናቀል ነው፤ የዜግነት መብትና መገለጫ የሆነውን መሬት ማጣት ነው፤ ሁለቱም መሰረታዊ የሆኑ የኢትዮጵያዊነትን የዜግነት መብቶች ሚደፈጥጡ ናቸው፤ ልብ በሉ የኦሮሞን የዜግነት መብቶች ይደፈጥጣል አላልኩም፤ የኢትዮጵያውያንን ሁሉ መሠረታዊ መብቶች የሚደፈጥጥ ነው፤ ይህ የማያጠራጥር እውነት ነው፤ ይህንን ከተቀበልን ጉዳዩ የኦሮሞ ብቻ አይደለም፤ ግርግሩም የኦሮሞ ብቻ አይደለም፡፡
ትልቁ አደጋ ያሁንን ግርግር የኦሮምያ ብቻ ካደረግነው ወደፊት ያው ጉዳይ በሌሎች ጎሣዎች መሀከል ሊነሣ ነው፤ ሌሎች ግርግሮች ሊያስፈልጉ ነው፡፡
ጉዳዩ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሆነ ትግሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ነው” የሚል ምላሽ እና ማብራሪያን ሰጥተዋል፡፡ ጥያቄው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጣውም የመላው ህዝብ ተብሎ እንዲጠራም ጠይቀዋል፡፡