ለቡ ድሮ እና ዘንድሮ፥ (በእለፋቸው ሞሲሳ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የእድሜየን ሲሶ የኖርኩት ለቡ በምትባል በደቡብ አዲስአበባ በምትገኝኝ ቀበሌ ነው::….ድሮ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ነበር የምትባለው ….አሁን ለቁጥር ወግ በቅታ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምንትስ ቀበሌ ዜሮ አንድ ተብላለች:: ለቡ ድሮ ድሮ…ሁርቡ የሚባል የክረምት ጀግና ወንዝ እየተገማሸረ ነዋሪውን የሚያሸብርባት….ጎረምሶች የወንዙን ፉከራ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ እየዘለሉ ገብተው እወንዙ ዳር ሳር ሲግጥ ሳት ብሎት ገብቶ በ አለልቱ እግሮቹ የተተበተበ ወይፈን የሚታደጉባት …. የለቡ እና የማዶ ልጆች ክረምቱን ሙሉ እና በበጋው ቅዳሜ እና እሁድን ጠብቀው እግር ኩዋስ የሚጫወቱበት ሰፊ ሜዳ የያዘች….ጉርምስናን የተሻገሩት ህዳር ሃና እና ጥምቀትን እየጠበቁ ተሻግሮ ካሉት ገላን እና መኒሳ ቀበሌዎች ከሚመጡ ጎልማሶች ጋር የፈረስ ጉግስ ውድድር የሚያደርጉባት…. ከመሃል ከተማ ልጆች በክረምት ለበዓል የሚበራ ለራሳቸውም …የሚሸጥም ችቦ በነፃነት ለቅመው “ገጠር ሄደን መጣን!” ብለው ጉዋደኞቻቸውን የሚያስቀኑባት… በማገዶ ሽያጭ የሚተዳደሩ የጨርቆስ እና ቄራ አካባቢ እናቶች ከቀበሌው የሚገዙትን እንጨት እና ቅጠል ተሸክመው መሬት ለመንካት ስንዝር እስኪቀራቸው አጎንብሰው በአንዲት ጨፈቃ እርዳታ የሚጉዋዙበትን አንጀት የሚበላ ትዕይንት የምታይበት …በፀደይ ወቅት ለማየት የሚያሳሳ የጤፍ ቡቃያ የሚሰራው ማዕበል ነፍስን ወሰድ የሚያደርግባት…ነዋሪዎች እንደይዞታቸው መጠን አርሰው…ዘርተው…አጭደው ከጎተራ የሚያስገቡባት….የሚበቃቸው እህላቸውን ሽጠው….የማይበቃቸው ጎን ለጎን ከከብት አዛባ እና ከጭቃ የሚሰሩትን አክንባሎ “ቆሼ” እየተባለ ወደሚጠራው አየርጤና አካባቢ ያለ ገበያ ወስደው ሽጠው…. …. ከከብቶች ግጦሽ የተረፈ ስንበሌጥ እና ባለሚ (የሱ ሳር ሽታ እስካሁን ልቤን በሃሴት ይሰውራታል) አጭደው ቄራ ወስደው ሽጠው….ጋዝ …ሳሙና…እና መሰል ሸቀጦችን እንዳቅማቸው ሸምተው የሚገቡባት የገጠር ቀበሌ ነበረች:: በአብዛኛው ኦሮሞዎች የሆኑ ነዋሪዎችዋ ….ከወሎዬዎች…ጎንደሬዎች…አንድ እድር ገብተው….አንድ ፅዋ ጠጥተው….ከአንድ ማዕድ ቆርሰው…. በእሳት የተያያዘ ጎጆን አብረው አትርፈው ….በሰላም የሚኖሩባት የገጠር ቀበሌ ነበረች:: ይሄ የሕይወት ዑደት ባይሻሻል ሳይብስበት ….ሳይደፈርስ እየዞረ መጥቶአል… ለዘመናት! ይሄ እንደነገሩ የሳልኩት የለቡ ስእል መልካም ነው? የገጠር ኑሮ ሲያወሩት …ሲያነቡት…እንጂ ሲኖሩት አይመችም:: መብራት…ንፁህ ውሃ…ጤና….ትምህርት….እነዚህ ሁሉ ምስሉ ውስጥ ድራሻቸው የለም…. እነዚህ ነገሮች ለከተማ ነዋሪም የሚደርሱት ዕጣ በሚመስል ሁኔታ እንደሆነ እየቆየ አየሁ:: ነዋሪው ይህ ሁሉ ባይኖረው….አልፎ አልፎ ዓመት አዙሮ ለመግጠም እጅ አጥሮት አንድ በሬውን ቢሸጥ… ለድርድር የማያቀርበው አንድ ሀብት ግን አለው:: መሬት! ገበሬው “laffa kiyaa” ይላል:: እንደምንም መቀናጆ ገብቶ….ጅጊ ጠርቶ…ያርሳታል:: ልጆቹ ለጋብቻ ሲደርሱም እየቆረሰ ያወርሳታል…በመሬት ጉዳይ የተነሳ ጠብም እንዲህ በቀላሉ የሚበርድ አይደለም:: እድሜ ልክ ጠላት የሚያደርግ ጉዳይ ነው:: ዘጠና አመተምህረትን አልፎ ነገር መጣ! አንዳንድ ፀጉረ ለውጥ ሰዎች ብቅ እያሉ ማሳው ውስጥ ጥቅል ሜትር ይዘው መንጎራደድ ጀመሩ…ገበሬው እና ልጆቹ “ምን ሊያደርጉ ነው?” በሚል ስሜት የሚሰራውን ሥራ በአርምሞ ያያል:: በአንድ የተረገመ በጋ የገበሬ ማህበሩ አስተዳዳሪዎች ከአስር ሺህ ብር ጀምሮ (ሀገር የሚያክል መሬት የነበራቸው ሰዎች ያገኙት ካሳ እስከ መቶ ሺህ እንደሚደርስ ሰምቻለሁ) እየወረወሩለት የእርሻ መሬቱን ነጥቀው ገበሬውን በ ጉዋሮው ወሰኑት! ያቺ ጥቂት ሺህ ብር እስክታልቅ ጠብቀውም ቀስ እያሉ ጉዋሮውንም ነጥቀው መቶ እና መቶ ሃምሳ ካሬ መሬት ከ ጥቂት ሺህ ብሮች ጋር ሰጡት:: አሁን …ማስተር ፕላን….የከተማ ልማት…መሬት የመንግስት ነው….ገለመሌ የሚሉ ነገሮችን እንተዋቸውና ለጊዜው…የገበሬውን ሕይወት ታይም ላይን እንይ:: ….ማሳውን ተነጥቆ በተሰጠችው ብር የቤቱን የሳር ክዳን በቆርቆሮ ቀየራት….ከፍ ያለ ገንዘብ ያገኘው ታክሲ ገዝቶ ለከተማ ጮሌ ሹፌር እና ረዳት ሰጣት…እራሱ የተወሰደበት ማሳ ላይ ለሚሰሩ ቤቶች የማቴርያል ስቶር በወር መቶ ሃምሳ ብር እየተከፈለው ተቀጠረ… ልጆቹ የማቴርያሎቹ ጫኚና አውራጅ ሆኑ…. (ይሄንን ሥራ ማንም አይነካባችሁም ….ተደራጁና የናንተ ነው ስራው የምትል መደለያ ነበረች…..እውነቴን ነው!)….ሚስቱና ሴት ልጆቹ እዛው አካባቢ የሚሰሩ ቤቶች…ህንፃዎች….መንገዶች ላይ ድንጋይ ተሸካሚ ሆኑ…. ቀስ እያለ…የቤቶቹ የህንፃዎቹ ሥራ አለቀ…. እና በብስጭት ተቃጥሎ ከመሞት የተረፈው….ህንፃዎቹ ላይ አሁንም ዘበኛ ሆኖ ኑሮውን ይገፋል…. ጉዋሮው (ሁለት ሺህ….ሶስት ሺህ እና ከዛ በላይ የሚሆን ስፋት ያለው) ተወስዳ መቶ ካሬ እና ማፍረሻ የተሰጠችውም ባዶ ቁራጭ መሬት ታቅፎ ምንም ሊያደርገው አይችልም….እየሸጠ ወደ ዓለም ገና…ወደ ሰበታ…ዱከም…. (እዛም ደርሰው እስኪያባርሩት ድግሞ…) እየተገፋ ነው….ጎረምሶቹ…የሚወርደው ሲሚንቶም አልቆ….ቦዝነው … የልጆች አባት ሆነው….ያለ እድሜያቸው አርጅተው………በቁጭት …..በሱስ….በፀጥታ እየሞቱ ነው:: ለቡ ምን ትመስላለች አሁን? እረ አምሮባታል! ፒያሳ ምስጋና ትጣ! ወዝዋ ጨፍ ብሎአል! ወላ ሾፒንግ ሞል….ኢንዱስትሪ መንደር…ካልዲስ ካፌ….ደረጃውን የጠበቀ መንገድ….የመንገድ መብራት…ቪላዎች….አፓርትመንቶች……..እንደውሀ የሚፈሱ መኪኖች …ወዘተ ወረዋታል…:: አንድ የቀራት ነገር የለም! እና ይሄው ነው! በመላ ሀገሪቱ በኦሮሞ ተማሪዎች የተቀጣጠለው አመፅ ይሄ ማብቃት አለበት! የሚል ነው:: ይሄ ማስተርፕላን በለቡ ….ሃናማርያም….ቱሉዲምቱ…ለገጣፎ የተጀመረው ሲስተሚክ የገበሬዎች መፈናቀል … በገዛ መሬቱ ላይ ባርያ የማድረግ ዘመቻ ማስቀጠያ መሳርያ ብቻ ነው! ተቃውሞውም ምንም ውስብስብ አጀንዳ የለውም! የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው! ይሄ ጥያቄም መኖርን ባረጋገጠ መልኩ እስካልተመለሰ ድረስ አመፁም እንደተቀጣጠለ ይቀጥላል!