እሳትን በጋቢ “ማዳፈን”
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
Meski Ab Fits : የሃገራችን ሰሞንኛ ፖለቲካዊ ትኩሳት ንፁሃንን ለሞት፣ መንግስትን ለከፍተኛ ድንግርግሮሽ የዳረገ እንደሆነ የሚታይነው፡፡የፖለቲካው ግመት በዋናነት ከሁለቱ ሰፋፊ ክልሎች የሚነሳ ግን ደግሞ በክፉ ውጤቱ የኢትዮጵያን ህዝብ ከዳር እስከዳር እያሳዘነ እና እያሳሰበ ያለ ሁነት ነው፡፡በንፁሃን ሞት እና በወጣቶች ጅምላ እስር የታጀበው ጥፋት የማያስከፋው ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ የጥፋቱ መጠን እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖም መንግስት እንደሚያለባብሰው ቀላል አይደለም፡፡
መንግስት በአዲስ አበባ እና በአጎራባች ወረዳዎች መካከል የተቀናጀ ልማት ያመጣል እያለ በልማት ማማነቱ የሚዘምርለት እቅድ ህዝብን አሰከፍቶ ለአደባባይ እምቢተኝነት ያበቃ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ህዝቡ እቅዱ ከልማቱ ይልቅ ጥፋቱ ይበዛል ብሎ ነገሩ እንዲቀር የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው፡፡ በተመሳሳይ በአማራ ክልል በተለይ በጎንደር አካባቢ ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ማካለል እና ከቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ እየተጋጋመ ላለው ፖለቲካዊ ጥያቄ ህዝብ ጥቅሙን የሚያስከብርለት መፍትሄ ከመንግስት ይፈልጋል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ህዝቡ ከአንድ ወር ዘለግ ላለ ጊዜ ጥያቄውን በማሰማቱ ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን ከአፈሙዝ ጋር በአንድ እርምጃ ርቀት እየተያየም ሞትን ወደ አለመፍራት ምሬት የደረሰው የህዝብ አቋም በመንግስት ዘንድ የተሰጠው ትርጉም ሌላ ነው፡፡
ለኢህአዴግ ምሬት ያረገዘው የህዝብ ጥያቄ ከህዝቡ ከራሱ ፖለቲካዊ/ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የመነጨ ሳይሆን በጥፋት ሃይሎች የተቀነባበረ ህዝብን ለጥይት ከመማገድ ብርቱ ፍላጎት የተነሳ ነው፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የተነሱት ጥያቄዎች እውን ኢህአዴግ እንደሚያወራው ህዝቡን በምንም መልኩ አይጎዱትም? ህዝቡ እቅዶቹን በተመለከተ የራሱ ጥያቄ ከሌለውስ ለምን ብሎ ነው “ለጥፋት ሃይሎች ድብቅ አጀንዳ” ሲል በገዳዮች አፈሙዝ ትይዩ ደረቱን ሰጥቶ የሚቆመው? የኢትዮጵያ ህዝብስ የሚባሉትን የጥፋት ሃይሎች(ካሉ)አጀንዳ ተሸክሞ ወደ ሞት መንደር የሚያቀናው ምን አይነት ፖለቲካዊ የዋህነት ቢቆራኘው ነው? የጥፋት ሃይሎችስ ምን ያለ ምትሃት ቢኖራቸው ነው ይሄ ሁሉ ህዝብ ያለ ምንም አላማ (ኢህአዴግ እንደሚለው ለጥፋት አጀንዳ መሳካት)መተኪያ የሌላትን ነፍሱን በምህረት የለሹ አፈሙዝ ፊት እንዲያስቀምጥ ያደረጉት? ኢህአዴግ አመጣሁት እያለ ዘወትር የሚዘምርለት ልማት እንዴት ህዝብ የጥፋት ሃይሎችን ምክር እንዳይሰማ አላገዘም? የጥፋት ሃይሎች የሚለው አገላለፅስ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ማንነት ጋር እንዴት ይዛመዳል? ሰው የሆነ ፍጡር እንዴት የጥፋት አጀንዳ አንግቦ ለጥፋት ብቻ ይጓዛል ተብሎ ለሰሚ ይነገራል? የሃገር ልማት ፀር፣ የወጡበት ህዝብ ጠላት ሆኖ ፀረ-ህዝብ መሆንስ እንዴት ይቻላል?
እነዚህ ፀረ-ልማት፣ፀረ-ህዝብ አለያም የጥፋት ሃይሎች እየተባሉ በኢህአዴግ መንደር የሚብጠለጠሉ አካላት ከኢህአዴግ ጋር የአመለካከት ልዩነት ያላቸው፣ ከሰላማዊ እስከ ትጥቅ ትግል የደረሰ መንገድ ተጠቅመው ኢህአዴግን ለመቀየር የሚታገሉትን ተቃዋሚዎች ለማለት እንደሆነ ኢህአዴግን የሚያውቅ ሁሉ የሚረዳው ነው፡፡ ግር የሚለው ነገር ግን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ “የጥፋት ሃይሎችን” ተከትሎ “የልማት አባት” ነው ሲባል የኖረውን የኢህአዴግን መንግስት ሊንድ ተነሳ የሚለው አሰልች ፕሮፖጋንዳ ከራሱ ልማታዊ ነኝ ከሚለው መንግስት መወሳቱ ነው፡፡
ኢህአዴግ አብዛኛውን ጊዜ ህዝብ በራሱ ህሊና አስቦ፣ ጥቅም ጉዳቱን መዝኖ የመንግስትን አካሄድ ተቃወመ ሲል አያጋጥምም፡፡ ይልቅ ህዝብ የኢህአዴግን መንግስት ሲጠይቅ እና ሲቃወም በጥፋት ሃይሎች ተገፍቶ ነው ማለትን ይመርጣል፡፡ ‘ህዝብ በራሱ አስቦ፣ የሚጠቅመውን ለይቶ፣ልማቱን የሚያስቀጥልለትን የመምረጥ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጠ’ የሚባለው ኢህአዴግ እንደምንም አድርጎ ተመረጥኩ በሚልበት የምርጫ ውጤት ላይ ብቻ ነው፡፡ የምርጫ ውጤቱ ትክክለኛ የህዝብ ውሳኔ የሚሆነው ኢህአዴግን መልሶ በመንበሩ የሚያስቀምጥ ከሆነ ነው፡፡ ይህ ኢህአዴግ እስከዛሬ ያዘገመበት ፖለተካዊ ዘይቤ ቢሆንም ሁልጊዜ ይሰራል ማለት ግን አይደለም፡፡ በተለይ ህዝብን በሆነ አካል እየተነዳ አደገኛ የፖለቲካ ስህተት የሚሰራ የዋህ አድርጎ ማቅረብ ጉዳት እንጅ ጥቅም የለውም፡፡ ከዚህ ይልቅ የህዝብን ትክክለኛ የቅሬታ ምንጭ መርምሮ ወደ ትክክለኛው የመፍትሄ መንገድ መጓዙ ራስን ከማታለል ያድናል፤ ከአጉል አወዳደቅም ይታደጋል፡፡ በተረፈ መንግስት የተያያዘው የጥፋት ሃይሎች እኩይተግባር በቁጥጥር ስር ዋለ የሚለው አውጋዥ እና በፉከራ የተሞላ ፕሮፖጋንዳን ዋና ያደረገ አካሄድ ጋላቢ እሳትን በጋቢ ለማዳፈን እንደመሞከር ያለ አደገኛ መንገድ ነዉ፡፡
የሃገራችንን ፖለቲካዊ ትኩሳት ያናረው ወቅታዊው የህዝብ ጥያቄ ከተለመደው የመንግስት አውጋዥ ፕሮፖጋንዳ አለፍ ያለ ብስለትን የሚጠይቅ ፖለቲካዊ ውሳኔ ይሻል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመንግስት በኩል በድሮ በሬ ማረስን መተው አማራጭ የለውም፡፡ በድሮ በሬ ማረስን ለመተው ትክክለኛውን የህዝብ ጥያቄ ከማድበስበስ ይልቅ በቅሬታውን ትክክለኛ ምንጭ ላይ ለመነጋገር የመድፈርን ብልህነት መልመድ ግድ ነው፡፡ሰሞኑን በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የተነሱት የህዝብ ጥያቄዎች የሃገሪቱን የመሬት ፖሊሲ፣ በተግባር አሃዳዊ መንግስትን የሚያስንቀውን የይስሙላ ፌደራሊዝም፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን የሃገርን ጥቅም የማስከበር አቅም፣ የዘር ፖለቲካን ብቻ ሙጥኝ የማለትን ትርፍ ኪሳራ ወዘተ መፈተሸን ይጠይቃል፡፡