ስለምን ፈራን፤ እንፈራለን፣እናስፈራራለን፣እንፈራራለን ?


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ስለምን ፈራን፤ እንፈራለን፣እናስፈራራለን፣እንፈራራለን ? Girma Bekele
የሰው ልጅ ሞትን፣ እስራትን፣ ስቃይን፣ … የምፈራው የተፈጠረበትንና የምኖርበትን የህይወት ተልዕኮ አውቆ ፣ይህን ተልዕኮው ለማስፈጸም የሚያስችል ነባራዊ፣ ወቅታዊና ቀጣይ/የወደፊት ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ካረጋገጠ ይህ እንዳይበላሽበት፣ ተልዕኮው እንዳይሰናከልበት ሲል ሊሆን ይችላል፤ በእኔ እምነት ሊሆን ይገባል፡፡ በተጨማሪም ይህን ተልዕኮ ለመፈጸም ዛሬ ባይቻለው እንኳ ነገ እደርስበታለሁ የሚል ተስፋ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከዚህ እምነት በመነሳትም በአሁኑ ጊዜ የአገራችንን ሁኔታ የዜጎቿን ግንኙነት… በአጠቃላይም ፖለቲካው በዛሬው ትርጉሙ ወደጎን ቢተው እንኳ ያለው ኢኮኖሚያዊ እውነታና ማኅበራዊ ትስስር ይህን የሚፈቅድ ስለሆነ ወይም ተስፋው ስላለ ነው የምንፈራው ወይስ የህይወት የመኖራችን ትርጉም፣ የህይወት ተልዕኮኣችን ብዙናምርጥ መብላት፣ መጠጣት፣ በምርጥ ቤት ውስጥ ምርጥ ለብሶ፣ ከጎን ቆንጆ ሸጉጦ ውድ መኪና እየነዱ…. መኖር ነው፡፡ ይህ ከራስ አልፎ ስለአገርና ወገን ማሰብን፣ ሥነልቡናዊ- ልባዊና አዕምሮኣዊ ሁኔታዎችን መሟላት ካላካተተ እንደምን በማቴሪያላዊ ዓለም ሜካኒካል ህይወት ውጪ የመኖርን ትርጉም ያሟላል? ይህ የመኖርን ትርጉም ያሟላልን ? አዎ ያሟላል ብለን ብናስብ እንኳ ስንቱ ነው ምርጥ -ምርጡና መጠኑ/ብዛቱ ቀርቶ ህይወትን ለማስቀጠል መሰረታዊ ፍላጎቱ / ልብስ ፣ምግብና መጠለያ / አሟልቶ ለነገ ተስፋ ሰንቆ እየኖረ ያለውና መኖር እያጓጓው ፣የሚያጓጓው ህይወት እንዳይቀርበት፣ የነገ ተስፋው እንዳይደርቅበት በመስጋት ለፍርኃት የተጋለጠው ?ስለ ቀጣይ ትውልድ/ልጆቹና ታናሾቹ ለማሰብ አዕምሮው የተዘጋው ? እንደምንስ የምንፈራላት ቢበዛ ከ80 ኣመት የማታልፈው የምድር ቆይታችን እንደዚህ የምታሳሳን፣ አገርና ወገን የምታስረሳን ፣ከእምነታችንና አምላካችን የምታጣርሰን ?
አስራ አምስት ሚሊዬን ወገኑ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ እየሰማና እያየ ፣ወገኖቹ በላስቲክ ቤትና በየጎዳናው ወድቀው፣ የለበሱት በላያቸው ላይ ተበጣጥሶ እየተመለከተ፣ለመኖር ልቡ ከመደንደኑ በተጨማሪ ሰብዐዊነቱና ክብሩን ተነጥቆ በውርደት ለመኖር ከሌላው ወገኑ የበታች እንደሆነ እየተነገረው፣ በተግባር እየተገለጸለትና መሆኑን እንዲቀበል እየተገደደ፣…እንደምን ይህንን ለመሸከም ትከሻው ፈረጠመ ፣በፍርኃት ታስሮ የህይወት ተልዕኮውን ለመፈጸም ቀርቶ መሰረታዊ ፍላጎቱን ባላሟላበት ውርደትን ለመቀበል ወደደ ወይም ተገደደ ? እንደምንስ ፈጣሪ በአምሳሉ ሲፈጥረው የሰጠውን ክብርና ሞገስ በማቴሪያል ለመለወጥ አቅሙን ከየት አገኘ ? የመሰሉ ህይወት በግፍ ሲቀጠፍ፣ ወይም ለመቅጠፍ ፣ ወገኑ ለስቃይ ሲዳረግ ወይም ለመዳረግ እንደምን ጭካኔውንና ድፍረቱን ተላበሰ ?….፣ በጭቃ ውስጥ ተኝተን፣ መብታችንንና ክብራችንን ተነጥቀን እንደምን አንቀላፋን፣ እንደምን መብታችንንና ክብራችንን ለማስመለስ /ለማስጠበቅ/ለማስከበር…..ድፍረቱን አጣን ፣ ፈርተን አስፈራራን?…. የሚሉት ጥያቄዎች ዘወትር በአዕምሮዬ እየተመላለሱ ናቸውና እባካችሁ በገባችሁ መጠን መልስ የሚሆን ያላችሁ ወዳጆቼ እጃችሁን ብትዘረጉ አስቀድሜ አመሰግናለሁ፡፡
ለወዳጆቼ– ይህ አብሮኝ የኖረና ያለ ለራሴ የራሴን መልስ ሰጥቼ በዚያ መሰረት እየኖርኩበት ያለሁ መሆኔን እንጂ የተለየ ስሜት ውስጥ ሆኜ የጻፍኩት መስሏችሁ እንዳታስቡ፣ ይልቁንም ጥያቄዬ ከእኔ መልስ የተለየ ኃሣብና ግንዛቤ ቢኖር ተጨማሪ ለማግኘት የቀረበ ጥያቄ መሆኑን እንድትረዱልኝ አሳስባለሁ፡፡ በቸር ያገናኘን//