ሚዲያ ፣ ሽብርና እስልምና – ዳሩል አርቀም


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሚዲያ ፣ ሽብርና እስልምና

በቅርብ ዓመታት ሚዲያዎችን እና የፖለቲካ መድረኮችን ከተቆጣጠሩ ቃላት መካከል አክራሪነት እና ሽብርተኝነት ዋነኞቹ ናቸው ቢባል ከእውነታው መራቅ አይሆንም። ከሶስተኛው የፈረንጆቹ ዕልፍ ዓመት መባቻ ጀምሮ የህዝብን ጆሮ ካደነቆሩ ግልብ ጽንሰ ሐሳቦች መካከል ቀዳሚዎቹም ናቸው። የሽብርተኝነት አጀንዳ ሲነሳ አክራሪነት እና ጽንፈኝነት የሚሉ ቅጥሎችም በማጀቢያነት ሳይወሱ አይታለፉም። የኋለኞቹ ሁለት ጽንሰ ሐሳቦች ደግሞ የሚነገሩት በእምነት ዓውድ ውስጥ እንዲወድቁ ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ሁሉም የሚያስተውለው ነው። ብዙሃኑ ፖለቲከኞች እና የሚዲያ ሰዎች ደግሞ ቃላቱን ከእስልምና ጋር ለማስተሳሰር ሲጥሩ ማየት የበርካቶችቻችንን ትዝብት ማትረፉ አልቀረም።

ሽብር እና የሽብርተኝነት ጉዳይ ከሙስሊሞች ጋር ተላኮ እጅግ በተደጋጋሚ ከመተረኩ የተነሳ ሽብርን ከኃይማኖተኝነት ለዚያውም ከስመ ይልቅ የተግባር (ኃይማኖተኛ) ሙስሊምነት ጋር ማቆራኘት በተራው ህዝብ ዘንድም ተንሰራፍቶ የሚገኝ ስህተት ነው። ስህተት መሆኑን ደግሞ አብዛኛው ይገነዘባል ፤ ለዚህም ‘’የትኛውም እምነት ሽብርን አይሰብክም’’ ሲል የውስጡን አውጥቶ ይናገራል። ይሁን እንጅ ከመጠን በላይ ደጋግሞ የሰማው የሽብር ‘’ስብኪያ’’ ላይ ላዩን ያሳመነው በሚመስል መልኩ እንደሰማው ከማውራትም አይቆጠብም። ዛሬ ዛሬ በግል ህይዎቱም ሆነ በማህበራዊ መስተጋብሩ ለእስልምና መርሆዎች ያደረን ሙስሊም በአክራሪነት ፈርጆ ከሽብር ጋር ማስተሳሰር ለብዙኃኑ ቀላል ጉዳይ ሆኗል። በዚህም በሽብር ተዋጊዎች (‘’ጸረ ሽብር ኃይላት’’) የተደሰኮረውን የፍረጃ ስልት በመንተራስ አንዱን እምነት ከሽብር ጋር አጋብቶት ያርፋል።

ግን እውነታው ሽብር ከየትኛውም እምነትም ሆነ ዘር ወይም አካባቢ ጋር የማይቆራኝ ዕሳቤያዊ ጭራቅ መሆኑ ነው። ይሁን እንጅ ብዙኃኑ ዘንድ እንደ ፋሽን የተንሰራፋው ግንዛቤ ኃይማኖተኝነትን በአክራሪነት ፣ መንፈሳዊነትን ደግሞ በጽንፈኝነት የመሰየም ተለምዶ ነው። በተለይ እስልምናን እና ሙስሊምነትን ከሽብር ጋር የሚያስተሳስረው አንዳችም የስምም ሆነ የተግባር ዝምድና ያለመኖሩ ሊታወቅ የሚገባው ሐቅ ነው።

እስልምናን በማጠልሸት ክፉ ማስመሰል ፤ ምዕመናኑንም በእኩይ ፈርጆ ከሰብዓዊነት ባህሪ በሚያስወጣ መልኩ የ’’ማሰይጠን’’ ጭፈራ በየሚዲያው ይስተጋባል። እስልምና ግን ከነውበቱ ፣ የሰብዓዊነት እና ሰላማዊነት ብርኃኑን ለዘላለም እየፈነጠቀ ይኖራል። ቁም ነገሩ እስልምናን እና ሽብርን ምዕራባውያን እና አጋፋሪዎቻቸው ከሚሰብኩት ፍሪከርስኪ ባለፈ የሸረሪት ድር እንኳ ያህል ጥንካሬ ያለው ማስተሳሰሪያ አይገኝለትም። የ’’ጸረ ሽብር’’ ትግሉም ዕሳቤያዊ እና ቁሳዊ የበላይነትን ለማስጠበቅ ብሎም ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚደረግ ግብግብ (ርዕዮተ ዓለማዊ ጦርነት) እንጅ ሌላ መነሾም ሆነ ዓላማ የለውም። በጥለ እስልምና ልበ-ህሊናቸው የከሰመው ቡሽና ብሌይር ከአወዛጋቢው የመስከረሙ 11 ፣ 2001 ጥቃት ማግስት ‘’በአሜሪካ ላይ ጥላቻን ያነገቡ እና ነጻነታችን የማይዋጥላቸው ‘’እኩያን/evils’’ ላይ ጦርነት እናውጃለን’’ ካሉ ማግስት ጀምሮ በሙስሊሙ ዓለም ላይ ሞት ይዘንባል። ታዲያ ይህ የመካከለኛው ምስራቅ ፣ ሰሜን አፍሪካ እና ሌሎች ሙስሊም አካባቢዎች ላይ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሞትን ያወጀ የእኩያን ዕኩይ ምግባር እንጅ የሰላም ፣ የፍትህ ፣ የእኩልነት እና ሰብዓዊ ክብርን የሚያስጠብቅ ሰናይ ተልዕኮ ሊሆን አይቻለውም።

ምንጭ፡- ዳሩል አርቀም መፅሔት