በሰሞኑ የአደባባይ ውሎዎች ከህዝብ ለባለሥልጣናት/ካድሬዎች የተላለፉ‹‹ ምክሮች››


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በሰሞኑ የአደባባይ ውሎዎች ከህዝብ ለባለሥልጣናት/ካድሬዎች የተላለፉ‹‹ ምክሮች››
1. ‹‹ በአቅምሽ አልሚ››
‹‹ የአማራ ህዝብ ለብአዴን ከፍተና ባለስልጣናት/ ካድሬዎች ››

በአማራ ክልል ስለ አንደኛው ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸምና ስለሁለተኛው ዕቅድ ህዝብን ለማወያየት በተካሄደ ስብሰባ ላይ አንድ አዛውንት የካድሬዎችን የሰበካ/የጠመቃ ኃሳብ አድምጠው ካበቁ በኋላ አስተያየት ሲጠየቅ ተነስተው ንግግራቸውን በምሳሌያዊ አነጋገር እንዲህ በማለት ጀመሩ፡፡ ‹‹ አንድ ባልቴት ህልም አይተው ኖሮ ወደ ህልም ፈቺ/አዋቂ ዘንድ ሄደው ….. ትናንት ማታ ከጃንሆይ ጋር በአንድ ላይ ተቀምጠን እጅግ የሚጣፍጥ ምግብ ሳጎርሳቸው፣ ሲያጎርሱኝ ፣ ስንጎራረስ አደርን… ምን ይሆን ትርጉሙ›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ህልም ፈቺውም ‹‹ ባቅምሽ አታልምም ነበር፤ ምን እንድልሽ ትፈልጊያለሽ፣ለወደፊቱ በአቅምሽ አልሚ›› አሏት ካሉ በኋላ ንግግራቸውን በመቀጠል ‹‹… የእናንተ ዕቅድም እንደሴትዬዋ ህልም ነው፣ ያላቅማችሁ- አልማችሁ ትነሱና ቅንጣቱን ሳትፈጽሙ፣ እኛን ሰብስባችሁ ህልማችሁን እንድንፈታላችሁ፣ ውድቀታችሁን ለመደበቅ ትሰበስቡናላችሁ፡፡ ይልቁንስ ለእኛ የሚበጀው ለእናንተም የሚጠቅመው ልታደርጉ የምትችሉትን ብታቅዱ እንጂ ለፕሮፖጋንዳችሁ እኛ የማናየውንና ያልደረሰንንና የማይደርሰንን ፣ ደርሰን የማናየውን የተስፋ ዳቦ አትመግቡን፡፡ ለእኛ ስለወረዳችን /አካባቢያችን ያቀዳችሁትን ፣ልትፈጽሙ የምትችሉትን ነገ አይተን ስለምናመሰግናችሁ/ስለምንወቅሳችሁ ብትነግሩን ነው እንጂ ሌላው ምን ሊጠቅመን ?፡፡ እንግዲህ ስለወረዳችን/አካባቢያችን ብትጠይቁን የምንነግራችሁ ይደረግላችኋል ካላችሁት የደረሰን የለም ባንልም በጣም እጅግ በጣም ጥቂቱ ነውና አዲስ ዕቅድ ከምታወሩብን በሁለተኛው ዕቅድ ዘመናችሁ ዕድሜ ከሰጣችሁ በመጀመሪያው የገባችሁልን ቃል ከፈጸማችሁ ከበቂያችን በላይ ነው፡፡ ያለፈውን ሳትፈጽሙ ሌላ መጨመር ያው እንደ ባልቴቷ ህልም ነውና እባካችሁ በተራበ አንጀታችን አታድክሙን፡፡…. ስለምንስ የእኛዎቹ ከናንተ ጎን ተቀምጠው ስብሰባውን አልመሩም —የተናገሩትንና የሆነውን ስለሚያውቁ ነው›› ብለው እንዳበቁ ህዝቡ አጨብጭቦ ስብሰባውን ‹‹አብቅቶ›› ረግጦ ከተባለ‹‹ ፀረ-ልማት ›› ያስብላልና ወደየቤቱ ተበተነ፡፡ በማለት አንድ ወዳጃችን አጫወተን ፡፡ በእርግጥም ህልምም ቢሆን በአቅም/በልክ ሲሆን ነው፤ ከትግራይ እስከ ወላይታ ባቡር መንገድ አልሞ የአዲስ አበባን ቀላል የባቡር መንገድ ያለማጠናቀቅ፣ አስር የስኳር ፋብሪካ አልሞ አንዱንም አለማስጀመር፣ በምግብ እህል ራሳችንን ችለን ለውጪ ገበያ እናቀርባለን ብሎ ተነስቶ በአንድ የምርት ዘመን ችግር 10 ሚሊዮን ህዝብ አስርቦ አቁማዳ ይዞ ልመና መዞር፣…… ሁሉ ልክን አለማወቅ ከማለት ቢያንስ ህዝብን ከማታለል አያልፍም ፡፡ህዝብ ደግሞ አልታለልም ማለቱን ምሳሌው ያስረዳል፡፡

2. ‹‹ህዝብ ሲያለቅስ አብሮ ሳያለቅሱ ፣መምራት ቀርቶ አብሮ መኖር አይቻልም››
‹‹ የኦሮሞ ህዝብ ለኦህዴድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት/ካድሬዎች››

በሰሞኑ በኦሮሚያ በተከሰተው ሁኔታ ህዝቡን ለማረጋጋት ከፍተኛ ባለስልጣናት/ካድሬዎች በጠሩት ስብሰባ ላይ የካድሬዎችን ደረቅ ቅስቀሳ የሰሙ አንድ አዛውንት ‹‹ አሁን እናንተ የምትነግሩንና የሆነው አይገናኝም፣ እናንተ የምትሏቸውን ፀረ-ሰላምና ልማት፣ የጥፋት ኃይሎች እኛ አላየንም፣ የተቆጡትና የተቃወሙት በጥይት የተመቱት–የሞቱትና የቆሰሉት እኛው ያሳደግናቸው የምናውቃቸው ልጆች ናቸው፡፡እኛ የምንለውን በየቤታችን የምንነጋገረውን ከመስማት ውጪ እናንተ የምትሏቸውን አጥፊ ኃይሎች አያውቁም፡፡ ይህንን የአካባቢያችን ባለስልጣናትም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ታዲያ እናንተ ልጆቻችንን በጥፋት ኃይል ተልከው የምትሏቸው ማን ነግሯችሁ ነው፤ የእኛ ባለስልጣናት ከሆኑ ያሳዝናል፣ የእኛን ልጆች ሳያውቁ የሚያስዳድሩንና ልጆቻችንን በሀሰት የሚወነጅሉ ከሆነ፣ የእኛ ለቅሶ ለቅሶኣቸው ካልሆነና ከእኛ ጋር የማያለቅሱ ሆነው ለእናንተ ይህን ዓይነቱን ነገር ነግረዋችሁ ከሆነ እነርሱም ይስሙት፣ እናንተም እወቁት … በኦሮሞ ባህልና ወግ መሰረት ‹‹ህዝብ ሲያለቅስ አብሮ ሳያለቅሱ ፣መምራት ቀርቶ አብሮ መኖር አይቻልም›› እና በቀጣይ ባህልና ወጉን ሳታውቁ ወይም አውቃችሁ እየካዳችሁ ከማን ጋር እንዴት እየኖራችሁ ማንን ልትመሩ እንደሆነ አስቡበት›› የሚል ምክር አስተላልፈው ሲቀመጡ ህቡ በከፍተኛ ጭብጫባ ድጋፉን ገልጾላቸዋል ሲል ይሄው ወዳጃችን አጫውቶናል፡፡አዎን የማያውቁትን ህዝብ ወይም በቁስሉ ላይ እንጨት የሚሰዱበትን ህዝብ ማስተዳደር አይደለም አብሮ መኖርም ይከብዳልና ልብ ያለው ራሱን ከህዝብ ያዋህድ፣ የህዝብ ለቅሶ ለቅሶው ይሁን፣ የህዝብ እንባ አባሽ እንጂ አስለቃሽ ጋዝ አይሁን፡፡ በዚህ አጋጣሚ በዚህ ያለፉ ወንድሞቻችንና ህጻናት ነፍስ ይማርልን ፣ራሳቸውን ከህዝብ ጎን ላሰለፉ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት፣ ባለስልጣናት፣ የመንግስት ሠራተኞች- ሀኪሞች፣ መምህራን፣… አድናቆታችንና ተገቢው ክብር ይድረሳቸው እንላለን፡፡