ኤፍሬም ታምሩ ሮሃ ባንድ- እንደገና እጹብ ድንቅ ልዕልና!!!
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
Written by ደረጀ ምንላርግህ On AddisAdmass
ስለ አልበሙ ትንሽ እስኪ እናውራ” እነሆ የ “ኤፍሬም ታምሩ እና ሮሃ ባንድ እንደገና – The Reunion” የሙዚቃ አልበም ማጣጣም ከጀመርን ቀናቶች ተቆጠሩ፡፡ ዘመን ያልሻረው፣ እንደውም ከሚታመነውና ከሚጠበቀው በላይ በድንቅ የአዘፋፈን ክህሎቱና ድምጸ ውበቱ እጅግ በልጽጎና ተውቦ የመጣው ኤፍሬም ታምሩ፣ እንዲሁ ዘመን ከማይሽራቸው የሮሃ ባንድ ሙዚቃ አቀናባሪዎች ጋር በድጋሚ ተዋህዶ፤ እነኛን ታሪካዊ ተፍለቅላቂ ዜማዎቹን፣ እንደ ጥጥ ፀዓዳ በሆነው ድምጸ አዘፋፈኑ ሸጋ አድርጎ አሳስቶ፣ አባዝቶ፣ አዳምጦና ፈትሎ ሲያበቃ ውብ አድርጎ ለብሷቸው ነው የመጣው፡፡ በእውነት ዜማን ሽክ!! ማድረግ፣ በዜማም ሽክ!! ማለት እንዲህ ነው። ብራቮ ኤፍሬም!!!
አጠቃላይ ሙዚቃው ህይወት እንዳለው ተክል ይተነፍሳል- የኤፍሬም ድምጽና ሁሉም አጃቢ የሙዚቃ መሳሪያዎች አግባብ ባለው ተፈጥሯዊ ቦታቸው ላይ በደንብ እንዲሰሙ ሆነው ተሰድረዋል- እርስ በርሳቸው ሳይሻሙና ሳይረባበሹ፡፡ ሮሃ ባንዶችም በግሩም የሙዚቃው አሬንጅመንት ድንቁን ኤፍሬም ታምሩን በሚዘፍንበትና ድምጹንም በሚቀረጽበት ወቅት፣ በምቹ ፍራሽ ላይ በምቾት እንደሚንፈላሰስ ሁሉ እንደልቡ እንዲመቸው አድርገውታል፡፡ የእውነተኛ ሙዚቃ አቀናባሪ ምንነትና ተግባርም ይሄው ነውና- ዘፋኙን ሙሽራ ማድረግ!!- ማለትም በሙዚቃው ውስጥ ዘፋኙ በደንብ ጎልቶና ተውቦ እንዲወጣ ማድረግ፡፡ በሰርግ ጊዜም እኮ ሙሽራዋ ናት ከሚዜዎቿ ይልቅ በሁሉም መልክ አምራና ጎልታ መታየት ያለባት፡፡ አስተውላችሁም ከሆነ፣ ሙሽራዋ ሚዜዎቿን ስትመርጥም እኮ፣ በተቻለ መጠን ብቻ ሳይሆን በሁሉም መጠን፣ በተክለ ሰውነት ውበት ከእሷ የሚያንሱትን ሴቶች ነው የምትመርጠው- Consciouslyም ሆነ Unconsciously፡፡ ከእሷ ያነሱትን ስትመርጥ Unconsciously (በደመ ነፍስ)፣ እሷን የምትበልጣትን በጣም ቆንጆ ጓደኛዋን ስትተዋት ግን consciously (እያወቀችና ሆነ ብላ!!) ነው፡፡ የእውነቴን እኮ ነው!! አይመስላችሁም?!፡፡ እንደውም ሳስበው፣ በተለይ ሴት ሙሽራ በውበት ከእሷ ያነሱ ሴቶችን ለሚዜነት ፈልጋ ፈልጋ ካጣች እንኳን፣ ሰርጓ ይቀራል እንጂ የምትሞክረው አይመስለኝም (ቂቂቂ. . .)፡፡ አብሮ አደግ ጓደኛዋ የሆነች እንኳን ብትሆን፣ ከእሷ የላቀች ቆንጆ ከሆነች፣ ምክንያት ይፈለግላታል እንጂ፣ ሚዜዋ ሆና ከጎኗ እንድትቆምማ አታደርገውም፡፡ ለምን ቢባል? ሰርጉ ላይ የሚገኙት የታዳሚ ሰዎች ዓይን ሁሉ እሷ ሙሽራዋ ላይ ማረፍ ሲገባው፣ የራሱ የጋሽ ባልም ዓይን ሳይቀር ወደ ቆንጅዬዋ ሚዜ ስለሚሳብና ስለሚሔድ ነዋ። ልብ አርጉ ጎበዝ!! ዓይን አይከለከልም። እንደውም እዚች ላይ የበውቄን (በዕውቀቱ ስዩምን) ሸግዬ ጨዋታ ላስታውሳችሁማ!! ወሬያችንን ታግዘናለች፡፡
ጨዋታዋ እንዲህ ናት፡- አንዱ ባል እኮ ነው፣ ሁሌም ከሚስቱ ጋር አብረው ሲሔዱ መንገድ ላይ ቆንጆ ሴት ባየ ቁጥር፣ ወይም ከሴቶች አካለ ውበት ነገራቸው አንዱን ቆንጆ ነገራቸውን ባየ ቁጥር፣ ዓይኑን እዚያ ላይ ተክሎ እየተመሰጠ ሲያስቸግራት ጊዜ፣ ሚስት ሆዬ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠችውና ዳግመኛ ላያደርግ ተስማማ። ታዲያ ምን ይደረጋል፣ ይሄን የቃል ስምምነቱን ከገባ ከቀናት በኋላ፣ እንደዚሁ አንድ ቀን ከሚስቱ ጋር አብረው ዎክ በማድረግ ላይ ሳሉ፣ ከፊት ለፊታቸው አንድ ዘልዬ ካልወጣሁ?! ዓይነት የሚል፣ እኔ ነኝ!! ያለ ቆንጆ የሴት ጡት መጣበታ፡፡ እናም፣ ይሄ ወንድማችን ባል ሆዬ ለሚስቱ የገባውን ቃል ጣሰና፣ ዓይኑን እዚያ ቆንጆ ጡት ላይ ተክሎት ቀራኣ፡፡ ይሄን ነገሩን ያየችው ሚስቱም- ‹‹አንተ?!›› ብላ በጥፊ ስታጮለው፣ ደግነቱ ይቺው ጦስ የሆነችበት ባለ ጡት፣ ደረቱ ላይ ‹‹እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ!!›› የሚል ጽሑፍ የታተመበት ቲሸርት ለብሳ ነበርና፣ ይሄ ወንድማችንም ፈጠን አለና- ‹‹እህ?! እርግጥ ነው በትዳር ውስጥ ሆኖ የሌላን ሴት ጡት ማየት ተገቢ ባይሆንም፣ የእናት ሀገራችን ኢትዮጵያን ጽሑፍ ከቲሸርት ላይ ማንበብ አይቻልም እንዴ?!›› ብሎ መለሰላታ፡፡ የዋዛ ነው እንዴ?!፡፡ የእውነት!! ይሄን የመሰለ መውጫ ላያጣ፣ ሚስቱን በመፍራት ያን የመሰለ ጡት!! ሳያነበው ባላዩ ሙድ ቢያልፈው ኖሮ፣ እኔ ራሴ አለቀውም ነበር (ቂቂቂ…)። እንዴ?! ምን ነካችሁ?! ‹‹ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ አንድ የሚጠላ አንድ የሚወደድ›› ነው እኮ ነገሩ፡፡
አሁን ጉዳያችን ወደሆነውና ወደጀመርነው ቁምነገር እንመለስ፡፡ . . . እናም፣ ሮሃ ባንዶች ኤፍሬም ታምሩን በሙዚቃው ላይ ሙሽራ አድርገውታል ብዬ ስለጀመርኩት የንጽጽር ሀሳበ ጉዳይ ስመለስ፣ ሮሃዎች ከኤፍሬም ታምሩ ድምፀ አጨዋወት ጋር ሲነጻጸሩ፣ እንደ የሰርግ ሚዜዎቹ ሁሉ በሙዚቃ አጨዋወታቸው ከኤፍሬም ድምጽ አነስ ብለው ታይተዋል ለማለት ሳይሆን፣ የተለየ የሙዚቃ ችሎታቸውን ለማሳየት ሲሉ፣ ጎልቶ መውጣት ያለበትን የድምጻዊውን ኤፍሬም ታምሩን ውብ ፍሰተ-አዘፋፈን ድምጽ በመሻማት ሳይሆን ሙሽራ ሆኖ እንዲጎላ በማድረግ በደንብ አጅበውታል!!- ሚዜው ሆነውታል ለማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ ጎበዝ፣ እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ነገር ቢኖር፣ ከማንኛቸውም የሙዚቃ መሳሪያዎች ድምጽ ሁሉ የላቀው ዕንቁና ብርቅዬ የሚባለው ድምጽ የዘፋኙ ድምጽ መሆኑን ነው- The most precious music sound is the human (singer) voice!!
እናም ይህ እውነት እንዳለ ሆኖ፤ በዚህ አልበም ላይ ግን፣ ኤፍሬም ታምሩ ከሰላሳ ዓመት በኋላ እነዚህን ውብ ዜማዎቹን ደግሞ መዝፈኑ ብቻ ሳይሆን፣ እንደውም በድንቅ ክህሎቱ የበለጠ አበልጽጎ እንደዚህ አሽሞንሙኖ መጫወት መቻሉ በጣም በጣም ገራሚው ነገር ነው፡፡
በተለይም ደግሞ እነኚህን የኤፍሬምን ዜማዎች በደንብ ለሚያውቃቸው አድማጭ፣ በዘፈኖቹ ላይ ድሮ የሰራቸውን አንዳንድ ከባድ የድምጽ ቅላጼዎችንና ከርቮችን ሊደግማቸው ይችላል ወይ?! እንዴትስ ሊወጣቸው ይችላል?! ተብለው የሚታሰቡትን ሁሉ፣ እንደውም የበለጠ አስውቦ እንደ ልቡ እየፈሰሰ ሊጫወታቸው በመቻሉ፣ ኤፍሬምን ከልብ የሆነ የእውነት አድናቆት ያስችረዋል፡፡ በርትቶ በመስራት መታደል ማለት እንደዚህ ነዉና!!!፡፡
በነገራችን ላይ፣ ይሄ በኤፍሬም ላይ የነበረው፤ ‹‹ዘፈኖቹን እንደ ድሮው አድርጎ ደግሞ ሊዘፍናቸው ይችላል ወይ?!›› የሚለው ጥርጣሬ የእኛ የአድማጮች ብቻ ሳይሆን፣ የራሳቸው የሮሃ ባንድ የሙዚቃ አባላትም ጭምር ስጋት ነበር- አልበሙ የወጣ ሰሞን ከኪቦርዲስቱና የሮሃ ባንድ አሬንጅመንት መሪ ከነበረው ከጋሽ ዳዊት ይፍሩና ከቤዚስስቱ ጆቫኒ ሪኮ አንደበት እንደሰማሁት፡፡
ጋሽ ዳዊት ይፍሩ እንዳለውም፣ ቅንብሩ አልቆ ኤፍሬም ታምሩ ለድምጽ ቀረጻው ስቱዲዮ ከመግባቱ በፊት፣ የባንዱ አባላት በሳምንት ሁለት ቀን እየተገናኙ ለስድስት ዓመታት ዘፈኖቹን ተለማምደዋቸዋል። በዚህ ሁሉ የልምምድ ጊዜያቸውም፣ የኤፍሬምን ዘፈኖች እየተፈራረቁ ይጫወቱላቸው የነበሩት- ድምጻዊ ዳዊት መለሰ (በአዘፋፈን ስታይሉ የኤፍሬምን ዘፈኖች ይጫወታቸዋል ተብሎ የማይታሰበው)፣ ማዲንጎ አፈወርቅና ሞገስ መብራቱ ነበሩ እንጂ ኤፍሬም ታምሩ በአንድም የልምምድ ወቅት አልነበረም። ይሄን ያደረጉበትን ምክንያት ጋሽ ዳዊት ሲናገርም- ‹‹በመጀመሪያ፣ ድሮውንም የሰራናቸው እነኚህ የኤፍሬም ዘፈኖች የሙዚቃ ቅንብር ደረጃቸውን የጠበቁ ስለነበሩ ለምን እንደገና እንነካካቸዋለን?፤ ሲቀጥልም፣ እኛስ አሁን ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ሙዚቃዎችን እንደ ድሮው ደግመን መጫወት እንችላለን ወይ?! የሚል ስጋትም ስለነበረብን፣ መጀመሪያ እስኪ እኛ ብቻ እየተገናኘን ሙዚቃዎቹን እንለማመዳቸውና እርግጠኛ ስንሆን ያኔ ኤፍሬም ድምጹን ይገባል ብለን ነበር የወሰነው፡፡ በኋላም፣ ሙዚቃዎቹን በደንብ ተለማምደናቸው ስንጨርስና፣ በእኛ በኩል ጠብቀነው ከነበረውም በላይ በጣም ቆንጆ ሲሆንልን፣ ቀጣዩ ስጋታችን የነበረው ደሞ ‹አሁን ኤፍሬም እነኚህን የድሮ ዜማዎቹን ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ እንደ ድሮው አድርጎ ሊዘፍናቸው ይችላል ወይ?!› የሚለው ነበር፡፡ የሚገርመው ግን፣ ኤፍሬም ስቱዲዮ ገብቶ ከዘፈናቸው በኋላ ድምጹን ስንሰማው፣ ባሳየው የአዘፋፈን ብቃቱ ሁላችንም እጅግ እጅግ አድርገን ነበር የተደነቅነውና የተደሰትነው›› ብሏል፡፡
በነገራችን ላይ በዚህ አልበም ላይ ያለው የአድማጮች አድናቆት እንዳለ ሆኖ፣ በተቃራኒው ደግሞ፣ አንዳንድ ሰዎች የሙዚቃውን ቅንብር በተመለከተ ‹‹ያው የድሮው ዓይነት እኮ ነው፤ ምንም አልተለወጠም፤አልተሻሻለም›› ሲሉ ቅሬታቸውን እሰማለሁ፡፡ እዚህ ላይ፣ በሙዚቃው ውስጥ የተሻሻሉና የተጨመሩ የሙዚቃ መሳሪያ አጨዋወቶች በደንብ እንዳሉበት ሊስተዋል ቢገባም፣ የቅሬታቸው እውነተኛነት ግን እንዳለ ነው፡፡ ለእውነተኛነቱ መሰረት የሚሆነውም ምክንያት፣ በተለይ አሁን አሁን፣ አንድን የቆየ ዜማ በራሱ በድምጻዊውም ሆነ በሌላ ዘፋኝ እንደገና ተደግሞ ሲቀናበርም ሆነ Remix ተደርጎ ስንሰማ፣ በሌላ የሙዚቃ ስታይል- በተለይም በውጮቹ የሙዚቃ ስታይል በሆኑት ዓይነቶች(ለምሳሌ- በሬጌ፣ ራጋ፣ ዳንስሆል፣ ብሉዝ፣ ሮክ፣ ካንትሪ፣ ዲስኮ፣ ሀውስ ቢት፣ ወዘተ) ቅንብሩ እየተለወጠ ስለሚሰራ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ፣ በዚህ በምንገኝበት ዘመነ ግሎባላይዜሽን፣ እነኚህ የውጮቹ የሙዚቃ ስታይሎች የእኛ እስኪመስሉን ድረስ ለጆሯችን ቅርብ እየሆኑ በመምጣታቸውና በመለመዳቸው፣ ለህዝባችን የዘፈን ድምጫም ጆሮ ገብ ሙዚቃ እየሆኑ መምጣታቸው አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡
ወደ እዚህ የ “ኤፍሬም ታምሩ & ሮሃ ባንድ እንደገና” አልበም ድጋሚ የሙዚቃ ቅንብር (ReArrangement) ጉዳይ ስንመጣ ግን፣ ሮሃ ባንዶች እነኚህን ዘፈኖች በሌላ ዓይነት የሙዚቃ ስታይል ቀይረው የማቀናበር ብቁ ችሎታው እንዳላቸው ቅንጣት ታክል ባያጠራጥርም፤ ያንኑ የድሮውን ቅንብር ደግሞ ለመስራት የመረጡበት አብይ ምክንያት፣ የቅንብሩን ስታይል ከለወጡት እነኚህ የኤፍሬምን ታሪካዊ ዜማዎች የድሮውን ሸጋ ዜማዊ ፍሰታቸውን ሊረብሹት ስለሚችሉና አሻራውንም ሊቀይሩት ስለሚችሉ ነው፡፡ በተረፈ ግን፣ሌላ ድምጻዊ እነኚህን የኤፍሬምን ዘፈኖች እንደገና ደግሞ ቢዘፍናቸውና የድሮውን የሙዚቃ ቅንብር ስታይል ሙሉ በሙሉ ቀይሮ ቢያመጣው ጉዳት የለውም- የዋናው ምንጭ የኤፍሬም ታምሩ ስራ ቅርስነት እንዳለ ነውና፡፡
ሌላው ይህ አልበም በድጋሚ መሰራቱ አስፈላጊ የሆነበትን አብይ ቁምነገር ስንመለከት፣ ድሮውንም ቢሆን በ70ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ላይ፣ የድምጻዊያኖቻችንን ሁሉ ሙዚቃ የማቀናበሩን ተግባር በታሪካዊ ኃላፊነት ተረክበውትና በሚገባም ነግሰውበት የነበሩት ሮሃ ባንዶች፣ በዚያን ጊዜውም የሰሯቸው የሙዚቃ ቅንብሮቻቸው እሰካሁን ዘመን ድረስም ሆነ ወደፊት በሚኖረው ፕሮፌሽናል የሙዚቃ ልኬት ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸው ባያጠራጥርም፣ በዚያን ጊዜው ስራቸው ላይ እንከን የነበረው ጉዳይ ግን በዘመኑ የነበረው የድምጽ ቀረጻው የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ የመሆኑ ነገር ነበር፡፡ ያኔ፣ ከሠላሳ ዓመት በፊት ማለት ነው፣ በነበረው ዘመነ ቴክኖሎጂ፣ የዘፋኙና የሁሉም አጃቢ የሙዚቃ መሳሪያዎች ድምጽ ይቀረጽ ወይም ይወሰድ የነበረው በአንድ ላይ በአንድ የቀረጻ መስመር ብቻ በመሆኑና፣ ቀጥሎም ደግሞ ዋናው ቅጂ (ማስተር ፒሱ) በካሴት ሲባዛ፣ ሙዚቃው ሊሰማ ከሚገባው የድምጫ ጥራት ደረጃ ያነሰ ወይም የደከመ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ካሴቱ ውስጥ የተካተቱ አንዳንድ የሙዚቃ መሳሪያዎችም ታፍነው ምንም ሳይሰሙ የሚቀሩበት ሁኔታም የነበረ መሆኑ ጭምር ነው፡፡
ዘመን አሁን ላይ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ግን የድምጽ መቅረጫ መሳሪያዎች በጥራት አወሳሰድ እጅግ ከፍ ያሉ በመሆናቸው፤ እንዲሁም የዘፋኙንም ሆነ የእያንዳንዶቹን የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች ባንድ ላይ ሳይሆን ለየብቻ በሆነ መስመር ቀርጾ ስለሚወስድና፤እንዲሁም እያንዳንዶቹ የሙዚቃ መሳሪያዎች ከሌሎች ጋር ህብር ሆነው በምን ያህል ከፍታ መሰማት እንዳለባቸው ሳይንሳዊ ልኬተ-ደረጃውን ጠብቆ በባለሙያ ስለሚዋሐዱ (Music Mixing) የድሮዎችን ዘፈኖች ባሉበት ሁኔታም ቢሆን እንደገና ደግሞ መስራቱ አስፈላጊነቱን ምክንያታዊ ያደርገዋል፡፡
በነገራችን ላይ፣ በአንድ ካሴት ወይም ሲዲ ውስጥ ያሉት አጠቃላይ ዘፈኖች የሙዚቃ ቅንብር ስራው ተጠናቆ ካለቀ በኋላ ቀጥሎ ስለሚመጣው ወሳኙና አስፈላጊው ሙዚቃዊ ስራ ወደሆነው- ሙዚቃውን የማዋሐድ ተግባር (Music Mixing) ምንነት ቀለል ባለ መልኩ ለመረዳት የወጥ አሰራር ሙያን ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡ ወጥ በባለሙያ ሴት ሲሰራ ጣት የሚያስቆረጥም ይሆን ዘንድ ሽንኩርቱ፣ ዘይቱ፣ ውኃው፣ በርበሬው፣ በአጠቃላይ ቁሌቱ፣ የጨው መጠኑ በደንብ ሆኖ እንደሚመጠን ሁሉ፤ በሙዚቃም እንዲሁ በዘፈኑ ውስጥ የተካተቱት የዘፋኙ ድምጽ፣ ድራሙ (ቤዝ ድራም፣ ኪክ ወይም ስኔር ድራም፣ ሲይምባል፣ ሃይሃት፣ ክራሽ፣ ወዘተ የድራም ክፍሎች)፣ ጊታሩ (በትንሹ ቤዝ ጊታር፣ ሊድ ጊታር)፣ ሳክስፎኑ፣ ፒያኖው፣ ኪ-ቦርዱ፣ ወዘተ የተካተቱትን የሙዚቃ መሳሪያዎች ለጆሮ ጥዑም ድምጫ እንዲኖራቸው አድርጎ መመጠን ማለት ነው፤ ራሱን የቻለው የMusic Mixing ተግባር፡፡ የዚህን የሙዚቃ ተግባር ሚና የበለጠ ልብ ለማለት ካስፈለገም፣ ለምሳሌ የተሰራውን ወጥ ስንመገብ፣ ሙያ የሌላት “ሴት” ከሆነች የሰራችው ‹‹ውይ?! ጨው በዝቶበታል!! ወይም አንሷል!!፣ በርበሬው በዝቷል!! ወዘተ›› እንደምንልና እንደማንበላውም ሁሉ፣ በሙዚቃም እንዲሁ የሙዚቃ ዕውቀቱ ከሌለን፣ ቤዝ ላይኑ ወይም ብራስ ሴክሽኑ እንዲህ ሆኗል፣ ይሄኛው የሙዚቃ መሳሪያ እንደዚህ ዓይነት ድምጽ አያወጣም ወይም የድምጽ ምጣኔው በዝቷል!! አንሷል!! ማለት ባንችልም፣ ‹‹ውይ?! ኧረ ይሄ ሙዚቃ ይጮሃል!! ምናለ ባታደነቁሩን?! እስኪ ወዲያ ዝጉት!! አታንጫጩብን!! ….›› ዓይነት ስንል እንሰማለን። ስለዚህም ሙዚቃው ሙያውን የጠበቀ ህብር ውህደት (ሚውዚክ ሚክሲንግ)፣ ቀጥሎም ሚውዚክ ማስተሪንግ አልተሰራለትም ማለት ነው፡፡
እዚሁ ላይ በነካ እጄ፣ ስለ “ሚውዚክ ማስተሪንግ” ሚና ደግሞ ቀለል ባለ መልኩ ለመግለጽ፣ በተለያዬ ቅኝትና ሬንጅ ውስጥ ተሰርተው አልበሙ ዉስጥ የተካተቱት የሁሉም ዘፈኖች (trucks) ድምጸት አሰማም፣ አንደኛው ዘፈን ቀጥሎ ከሚመጣውና ከሌሎች ዘፈኖች ጋር ሲሰማ ከፍ ወይም ዝቅ ያለ እንዳይሆን እኩል ማስተካከል (ሌብል ማድረግ)፣ እንዲሁም ልክ ቆንጆ ምጥን ወጥ ተሰርቶ ካለቀ በኋላ፣ የበለጠ ጣዕምናውን ለመጨመር ቅመም በላዩ እንደሚነሰነስ ወይም ቅቤ ጣል እንደሚደረግበት ሁሉ፣ በሙዚቃ አልበምም እንዲሁ መጨረሻ ላይ ጣዕመ ድባብ የሚያመጡትን የሙዚቃ ቅመሞች በዘፈኖቹ ላይ ነስነስ አድርጎ ማጠቃለል ማለት ነው፡፡ ይሄን ካልኩ በኋላ ግን፣ ሲያወሩት ቀላል ነው እንጂ፣ ይህ የሙዚቃ ሚክሲንግና ማስተሪንግ ሙያ ሙዚቃን ከማቀናበር ችሎታ በተጨማሪ ሌላ ዕውቀትና ልምድ የሚፈልግ ፕሮፌሽን ነው፡፡ ለዚህም ነው በሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ላይ እነኚህን ሁለት የአልበም ስራ ወሳኝ ተግባራት በተገቢው ደረጃ የሚሰሩት ሙዚቀኞች በጣት የሚቆጠሩ ሳይሆኑ ሁለት ብቻ የሆኑት፡፡ እነሱም፡- የኤክስፕረስ ባንዱ ጊታሪስት ክብረት ዘኪዎስና አበጋዙ ክብረወርቅ ሺወታ ናቸው፡፡ ይህን የኤፍሬምና ሮሃ ባንድ እንደገና ስራንም፣ የድምጽና ሙዚቃ ቀረጻውን እንዲህ ጽድትና ኩልል አድርጎ የቀረጸው ክብረት ዘኪዎስ በኤክስፕረስ ስቱዲዮ ውስጥ ሲሆን፤ ቀጥሎ ያለውን የሙዚቃውን ሚክሲንግና ማስተሪንግ እንዲህ ያለ ሸጋ ደርባባ እንዲሆን አድርጎ ያከናወነው ደግሞ አበጋዙ ክብረወርቅ ሺወታ ነው፡፡ ስለሆነም ስለዚህ አልበም ውጤታማነትና ስኬታማነት ስናወራ ከኤፍሬምና ሮሃ ባንድ ጎን ለጎን የእነኚህ የሁለቱንም ስኬታማ ሙዚቀኞች አስተዋጽኦ ማወቅና ልብ ማለት ያስፈልገናል፡፡
በመጨረሻም ሀሳቤን ሳጠቃልል፣ የኤፍሬም ታምሩና ሮሃ ባንድ እንደገና የሙዚቃ አልበም እነዚህን ከላይ ያወራናቸውንና ሌሎችን ፕሮፌሽናል የሙዚቃ ስራ ግብዓቶችን በደንብና በሚገባ ሁኔታ አሟልቶ የተሰራ በመሆኑ፤ እንዲሁም እነኚህ ታሪካዊ የኤፍሬም ዘፈኖች በዚያን ዘመን ላልነበሩ ላሁኑና መጪው ትውልዶችም መተላለፍ እንዲችሉ ሆኖ እንደገና መሰራቱ ጥቅሙ ለሙያው ባለቤቶች ብቻ አይደለም፣ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክም ቅርስ ሆኖ በተገቢው መንገድ እንዲቀመጥ መቻሉ ሀገራዊ ጥቅሙ እጅግ የጎላ ነው እላለሁ፡፡
እንግዲህ የሚያውቀውን የወረወረ ፈሪ አይባልም። ብልህ ሰው ደግሞ ከታናሹም ይማራልና፣ በዚህ በጻፍኩት ጉዳይ ላይ በዕውቀት ማነስ ምክንያት ብቀንስ እንጂ አልጨመርኩምና የማውቀውን አቀብያለሁ፡፡በሉ ይሄን የኤፍሬም ታምሩና ሮሃ ባንድ እንደገና አልበም ኦሪጅናል ሲዲ ገዝታችሁ በማዳመጥ፣ ያወራናቸውን የሙዚቃውን ቁም ነገሮች ልብ እያላችሁ ለጆሮ ሰላም በሆነው ስሜት ሀሴትን አድርጉ!!! ፍቅርና ሰላም አይለያችሁ፡፡