ይሄ ‘ቁጥር’፣ ፈፅሞ እውነት ሊሆን አይችልም – “በአምስት ዓመት ከ10.6 ሚ. በላይ የሥራ እድል ፈጥሬያለሁ” – የከተማ ልማት ሚ/ር


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“በአምስት ዓመት ከ10.6 ሚ. በላይ የሥራ እድል ፈጥሬያለሁ” – የከተማ ልማት ሚ/ር

• ይሄ ‘ቁጥር’፣ ፈፅሞ እውነት ሊሆን አይችልም – ከውጭ አገር፣ 9 . ሚ ሰራተኞችን ካላመጣን በቀር ።

‘ቁጥሩ’፣ ከኢትዮጵያ ከተሞች አቅም በላይ ነው ። የመስራት አቅም ያለው ከተሜ፣ 9 ሚሊዮን አይደርስም

“እንግዲህ ነገሩን ከሥሩ እንጀምረው፡፡ addisadmassnews.com
የመንግስት ባለስልጣንና ተራ ሰራተኛው፣ የጎዳና ነጋዴውና ባለሱቁ አባወራ ከነረዳት ልጆቹ፣ ባለሃብትና ተቀጣሪዎች… አልፎ አልፎ የሚመጡ ጊዜያዊ የቀን ስራዎች ላይ የሚሰማሩ ሰዎችንም ጨምሮ፣… የኢትዮጵያ ከተሞች ጠቅላላ የሰራተኛ ቁጥር፣ 4.7 ሚሊዮን አካባቢ ነበር – በ2002 ዓ.ም።
ይሄ የስታትስቲክ ባለስልጣን መረጃ ነው። (STATISTICAL REPORT ON The 2010 URBAN EMPLOYMENT UNEMPLOYMENT SURVEY, Table 4.5 – ገፅ 73)
ከዚያ ወዲህ በነበሩ አምስት ዓመታት፣ የመንግስት ሰራተኞች ቁጥርና የኩባንያ ተቀጣሪዎች፣ በስድስት መቶ ሺ ያህል ጨምሯል። በዚህ ላይ፣ በከተማ ልማት ሚኒስቴር የተፈጠሩ፣ “ከ10.6 ሚሊዮን በላይ የስራ እድሎችን” ጨምሩበት።
ጠቅላላ የከተማ ሰራተኞች ቁጥር፤ 16 ሚሊዮን ይሆናል።
“እንዴት ነው ነገሩ?” ያሰኛል። የከተማ ልማት ሚኒስቴር፣ ምን ነካው? የኢትዮጵያ ከተሞች፣ ህፃን አዛውንቱ ጭምር ተደማምሮ፣ ጠቅላላ የሕዝቡ ቁጥር’ኮ፣ 16 ሚሊዮን ገደማ ነው።
ጨቅላ ህፃናትን፣ ታዳጊ ተማሪዎችንና በእድሜ የገፉ አዛውንትን… ትተን፣ ‘የመስራት አቅም ያለው’ የከተማ ነዋሪ ሲቆጠር ደግሞ፣ ስምንት ተኩል ሚሊዮን ብቻ ነው። ይሄም የስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ነው – (ባለፈው ጥቅምት ወር ይፋ የሆነው ባለ 325 ገፅ የጥናት ሪፖርት – STATISTICAL REPORT ON The 2015 URBAN EMPLOYMENT UNEMPLOYMENT SURVEY, Table 4.1 – ገፅ 57)።
የመስራት አቅም ካላቸው ከተሜዎች መካከልም፣ ሰባት ሚሊዮን ያህሉ፣ በዓመቱ ውስጥ ቢያንስ የተወሰነ ጊዜ፣ ስራ ላይ ተሰማርተዋል ይላል – ሪፖርቱ። ችግሩ እዚህ ላይ ነው። የከተማ ልማት ሚኒስቴርን ስሌት አምነን ካሰብነው፣ የሰራተኞች ቁጥር 16 ሚሊዮን መሙላት አለበት። ስለዚህ፣ ዘጠኝ ሚሊዮን ተጨማሪ ሰራተኛ ማምጣት ይኖርብናል – ከሆነ ቦታ፣ ከቅርብ ጎረቤት አገራትም ሆነ ከባህር ማዶ።
ለማሾፍ ለመቀለድ ፈልጌ አይደለም። በእርግጥ፣ ነገርዬው፣ መሳቂያ መቀለጃ ለመሆን ተመቻችቶ የተዘጋጀ ይመስላል። ግን፣ ጉዳዩ ከባድ ነው። ‘የስራ እድል’ ላይ እንዴት እንቀልዳለን? የእንጀራ፣ የኑሮ፣ የህይወት ጉዳይ ነዋ። ድህነትና ስራ አጥነት በበዛበት አገር ይቅርና፣ ሃብትና ብልፅግና በበዛበት አገርም፣ ‘የስራ እድል’ ላይ አይቀለድም።
ይልቅስ፣ በከባድ የኑሮ ጉዳይ ላይ፣ የከተማ ልማት ሚኒስቴር፣ እንዲህ አይነት ‘መቀለጃ’ ቁጥሮችንና መረጃዎችን፣ ማሰራጨቱ ያናድዳል። ግን፣ ከጊዜያዊ ንዴትም ያልፋል። በጣም ያሳስባል። ይሄ ስህተት፣ የመጀመሪያው አይደለማ። በየአመቱ እየተደጋገመ የመጣ ስህተት ነው – ለዚያውም እየባሰበትና እየገዘፈ የመጣ ስህተት።
ባለፉት አመታትም፣ የከተማ ልማት ሚኒስቴር፣ በየጊዜው ‘የስራ እድል ፈጠርኩ’ እያለ ተመሳሳይ መግለጫዎችን ሲያሰራጭ፣ “ኧረ ይሄ ነገር ይታረም፤ ይስተካከል” የሚሉ ትችቶችና ምክሮች ተሰንዝረዋል፤ ተፅፈዋል። ግን፣ አልታረመም።
ከአመት አመት እንዴት እየጨመረ እንደመጣ ተመልከቱ።
በ2003 ዓ.ም ነው የጀመረው – 650ሺ የስራ እድሎችን ፈጥሬያለሁ በማለት የዓመቱ መጨረሻ ላይ መግለጫ አወጣ። በሚቀጥለው አመት ደግሞ፣ በእጥፍ የሚበልጥ ሌላ ቁጥር ይዞ ከች አለ – 1.3 ሚሊዮን ተጨማሪ የስራ እድሎች እንደተፈጠሩ ገለፀ።
አካሄዱ ወዴት ወዴት እንደሚሆን መገመት ትችላላችሁ። ዓመት ጠብቆ፣ በ2005 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ባሰራጨው መግለጫ፣ ሁለት ሚሊዮን አዳዲስ የስራ እድሎችን ጨምሬያለሁ በማለት አበሰረ። ከዚያም፣ ሌላ 2.7 ሚሊዮን። አምና ደግሞ ተመነጠቀ። በአራት ሚሊዮን አዳዲስ የስራ እድሎች፤ የኢትዮጵያ ከተሞች እንደተንበሻበሹ ተገለፀ።
እንግዲህ፣ እነዚህን ቁጥሮች በመደመር ነው፣ በአምስት ዓመታት ውስጥ፣ ከ10.6 ሚሊዮን በላይ የስራ እድሎችን ፈጥሬያለሁ በማለት፣ በተደጋጋሚ ሲናገር የከረመው።
አስገራሚው ነገር፣… ሌላው ቢቀር፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ አንዳንድ የፓርላማ አባላት፣ የሚሰነዝሩበትን ትችት ሰምቶ ትንሽ ለመታረም አይሞክርም? ‘አብዛኞቹ የስራ እድሎች፣ ከጥቂት ሳምንታት በላይ የማይዘልቁ ናቸው። እነዚህንም እየቆጠረ፣ እንደ ስኬት፣ ሪፖርት ማቅረብ ተገቢ አይደለም’ በማለት ተችተውታል።
ለነገሩ፣ የከተማ ልማት ሚኒስቴር ራሱ፣ በቁጥር ከሚገልፃቸው የሥራ እድሎች መካከል፣ ግማሽ ያህሉ፣ ‘ጊዜያዊ’ እንደሆኑ፣… አንዳንዴ ያምናል፤ ይህንንም ይናገራል። እና፣ አንዳንዴ ይህንን መረጃ ስለሚናገር፣ ‘አንዳንዴ’ ስህተቱን ለማረም ይሞክራል ማለት ነው? ‘አንዳንዴ’ ብቻ መሆኑ ራሱ፣ ትልቅ ችግር ነው።
ግን፣ አንዳንዴ ብቻ ሳይሆን፣ ሁልጊዜ ይህንን መረጃ ቢናገር እንኳ፣ ስህተቱን አረመ ማለት አይደለም። ከአስር ሚሊዮን የስራ እድል መካከል፣ ግማሽ ያህል፣ ለሳምንታት የማያዛልቅ ‘ጊዜያዊ ስራ’ ስለሆነ፤ አንቁጠረው እንበል። ግን፣ ሌላኛው ግማሽስ? ከአምስት ሚሊዮን በላይ፣ የእውነት የሚያዛልቅ የሥራ እድል ተፈጥሯል ማለት ነው? ይሄኛውንም አባባል፣ ‘ትንሽ ይሻላል’ ብለን እንቀበለው እንደሆነ እንጂ፣ ከእውነታው የራቀ ነው።
ለምን?
አሃ፤ ጊዜያዊ ስራዎች ጭምር ተቆጥረው፣ ባለፉት አመታት የተከፈቱ የከተማ የስራ እድሎች፣ ከ2.3 ሚሊዮን እንደማይበልጡ፣ የስታትስቲክስ ባለስልጣን ሪፖርቶችን በማገናዘብ መረዳት ይቻላል።
እንግዲህ አስቡት። በ2002 ዓ.ም፣ የነበረው ሁሉም አይነት የስራ እድል፣ 4.7 ሚሊዮን ገደማ ነው።
በ2007 ዓ.ምስ?
ሁሉንም አይነት ስራ በማካተት፣ አንድም ሳንተው፣ ብልጭ ብለው ድርግም የሚሉ ጊዜያዊ ስራዎችም ጭምር ተደማምረው፣ የከተማ የስራ እድሎቹ 7 ሚሊዮን ገደማ እንደደረሱ አዲሱ ሪፖርት ይገልፃል (STATISTICAL REPORT ON The 2015 URBAN EMPLOYMENT UNEMPLOYMENT SURVEY, Table 5.1 – ገፅ 83)።
ስለዚህ፣ በአምስት አመታት የተፈጠሩ፣ ሁሉም አይነት የስራ እድሎች፣ ከ2.3 ሚሊዮን አይበልጡም ማለት ነው።
ብልጭ ድርግም የሚሉ ስራዎችን ትተን፤ መደበኛ ስራዎችንና… ቢያንስ ቢያንስ እስከ ዓመት መንፈቅ ድረስ የሚዘልቁ ጊዜያዊ ስራዎችን ከቆጠርንስ?
በ2002 ዓ.ም፣ 4.2 ሚሊዮን “ደህና” የከተማ የሥራ እድሎች ነበሩ። በ2007 ዓ.ም ደግሞ፣ እንዲህ አይነት የስራ እድሎች፣ ወደ ስድስት ሚሊዮን ጨምረዋል። ባለፉት አምስት አመታት የተፈጠሩት “ደህና” የከተማ የስራ እድሎች፣ 1.8 ሚሊዮን ገደማ ብቻ ናቸው ማለት ነው።።
እነዚህ አዳዲስ የስራ እድሎችም ቢሆኑ፣ በከተማ ልማት ሚኒስቴር (ወይም በአነስተኛና ጥቃቅን ልማት ኤጀንሲ) አማካኝነት የተፈጠሩ ናቸው ማለት አይደለም። ከላይ የተጠቀሱትን፣ የስታትስቲክ ባለስልጣን የ2002 እና የ2007 ሪፖርቶችን በማነፃፀር፤ በምን በምን መስኮች ተጨማሪ አዳዲስ የስራ እድሎች እንደተፈጠሩ፣ አንዳንዶቹን ለመጠቃቀስ ልሞክር።
40 ሺዎቹ ተጨማሪ አዳዲስ የስራ እድሎች፣ የቤት ሰራተኝነት ናቸው። 180 ሺ ያህሉ፣ ያለ ክፍያ የሚከናወን የቤተሰብ አባላት ስራ ነው – ለምሳሌ የባለ ሱቅ ልጆች፣ ደንበኞችን በማስተናገድ ያግዛሉ። ሌላስ?
80 ሺዎቹ አዳዲስ ሰራተኞች፣ በባንክና በኢንሹራንስ ድርጅት የተቀጠሩ ናቸው። 80 ሺ በሲቪል ሰርቪስ፣ 400ሺ ደግሞ በመንግስት የንግድ ድርጅቶች ተቀጥረዋል። ነባርና አዳዲስ የግል ኩባንያዎችም እንዲሁ፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ጨምረዋል። በአጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው አዲስ የስራ እድል፣ በእነዚህ መስኮች የተሸፈነ ነው። የከተማ ልማት ሚኒስቴር ወይም የአነስተኛና ጥቃቅን ኤጀንሲ፤ በእነዚህ መስኮች ውስጥ ድርሻ የላቸውም።
ለመሆኑ፣ ስንት ቀረ? ገና በማንና በየትኛው መስክ እንደተፈጠሩ በዝርዝር ያልገለፅናቸው፣ 800 ሺ የሥራ እድሎች አሉ። በማን የተፈጠሩ ይሆኑ?
እንግዲህ፤ እዚህ ድረስ ጉዳዩን በመተንተን ካቃለልኩላቸው ዘንዳ፣ የከተማ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም የአነስተኛና ጥቃቅን ልማት ኤጀንሲ፤ ከዚህችው ‘ቀሪ’ ውስጥ፣ (ከስምንት መቶ ሺ የሥራ እድል ፈጠራ ውስጥ)፣ ድርሻቸው ምን ያህል እንደሆነ ለማጣራትና ለመግለፅ መሞከር ይችላሉ።
እስከዚያው ግን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት፣ እጅግ በዛ ቢባል፣ ከ800ሺ በላይ የሥራ እድል እንዳልፈጠሩ፣ በማመን ቢጀምሩ መልካም ይሆናል።

Addis Admass