–    ዛሬ በጠዋቱ አምሮብሽ ወዴት ነው?
–    ቀኑንም ረሳኸው?
–    ግንቦት 20 ነው እንዴ?
–    ጤነኛ ነህ?
–    የብሔር ብሔረሰቦችም ቀን አልፏል እኮ፡፡
–    አሁን አሁን ጤነኝነትህ እያጠራጠረኝ ነው፡፡
–    የምሬን እኮ ነው በጠዋቱ እንዲህ አምረሽ ወዴት ነው?
–    ወዴት የምሄድ ይመስልሃል?
–    የሴቶች ሊግ ስብሰባ አለብሽ?
–    እውነትም ለይቶልሃል፡፡
–    እኔ የማላውቀው ቀን በፓርላማ ተሰየመ እንዴ ታዲያ?
–    የምን ቀን?
–    እንዲህ ነጭ ከለበሽ የሰላም ቀን ነዋ የሚሆነው፡፡
–    እፀልይልሃለሁ ለማንኛውም፡፡
–    ምን ብለሽ?
–    ልብ ስጠው፡፡
–    የምፈልገውን ዓይነት ግን እንዳትረሺ፡፡
–    ምን ዓይነት ነው የምትፈልገው?
–    ልማታዊ ልብ፡፡
–    ምነው ኪራይ ሰብሳቢው ልብ ሰለቸህ?
–    ወሬማ ማን ብሎሽ?
–    እውነቴን ነው፡፡
–    ለማንኛውም ወዴት ነው የምትሄጂው?
–    ወደ አራት ኪሎ፡፡
–    ምን ልታደርጊ?
–    ልሳለም፡፡
–    ፓርላማውን ነው?
–    ምን ይላል ይኼ?
–    ጽሕፈት ቤታችንን ነው?
–    ኧረ የዓመቱ ነው፡፡
–    የዓመቱ ምን?
–    ገብርኤል፡፡
–    ለዚህ ነው እንደዚህ የዘነጥሽው?
–    ምን አለበት?
–    ምነው ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን እንደዚህ አልዘነጥሽ?
–    እየቀለድክ ነው?
–    አሁን እኔ በብሔር ብሔረሰቦች ስቀልድ ዓይተሽኝ ታውቂያለሽ?
–    መጽሐፉ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር እንደሚል አታውቅም?
–    የትኛው መጽሔት አዲስ ራዕይ?
–    የለም ዮሐንስ ራዕይ፡፡
–    ምን ልታደርጊ ነው የምትሄጂው?
–    ልሳል፡፡
–    እኮ ምንድን ነው የምትሳይው?
–    ጧፍ ነዋ፡፡
–    የምን ጧፍ አመጣሽ?
–    እና ምን ልሳል?
–    አምፖል ነዋ፡፡
–    ለምን ሲባል?
–    እኛ ግድብ የምንገነባው ሁሉም ቦታ መብራት እንዲበራ አይደል እንዴ?
–    ስለቴም እኮ እሱ ነው፡፡
–    ምንድን ነው የተሳልሽው?
–    እንዳይጠፋ ብዬ፡፡
–    ምኑ?
–    መብራቱ!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
–    ክቡር ሚኒስትር እንግዶች ይፈልጉዎታል፡፡
–    የምን እንግዳ?
–    ዳያስፖራዋች ናቸው፡፡
–    ተላላኪዎች ናቸው አትለኝም፡፡
–    የምን ተላላኪ?
–    የኒዮሊብራሎች ነዋ፡፡
–    ኧረ ክቡር ሚኒስትር እነዚህ አገር ወዳድ ዳያስፖራዎች ናቸው፡፡
–    ምን ፈልገው ነው?
–    እኛን ሊረዱን ፈልገው ነው፡፡
–    በምንድን ነው የሚረዱን?
–    ባለፈው ያወጣነውን ጨረታ ዓይተው ነው፡፡
–    የቱን ጨረታ?
–    ለሶፍትዌር ያወጣነውን ጨረታ፡፡
–    ታዲያ ጨረታውን ስጡን ሊሉን ነው የመጡት አትለኝም?
–    እሱማ ስጡን ሊሉን ነው የመጡት፡፡
–    እኔ መቼ አጣሁት?
–    ግን በነፃ ሊሠሩልን ይፈልጋሉ፡፡
–    ምን በነፃ?
–    አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    እባክህ በጐን ሌላ ነገር ፈልገው ሊቀበሉን ነው፡፡
–    ክቡር ሚኒስትር፣ እስካሁን በጐን የጠየቁን ነገር ስለሌለ ብንሰማቸው ጥሩ ነው፡፡
–    ለመሆኑ አሁን አሉ?
–    አዎን ቢሮ እየጠበቁኝ ነው፡፡
–    እስቲ አስገባቸው፡፡
–    እሺ፡፡
[ዳያስፖራዎቹ ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገቡ]
–    እናመሰግናለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ስለምኑ?
–    ሊያናግሩን ፈቃደኛ ስለሆኑ፡፡
–    ዳያስፖራውን መስማት ሥራችን ነው፡፡
–    ዛሬ የመጣነው ለምን እንደሆነ ያውቃሉ?
–    አላውቅም ለምንድን ነው?
–    መሥሪያ ቤታችሁ እንዲሠራለት የሚፈልገውን ሶፍትዌር ለመሥራት ነው፡፡
–    እሺ፡፡
–    ሶፍትዌሩን እኛ ብንሠራው ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡
–    ምን ዓይነት ጠቀሜታ?
–    ገንዘብ ይዘን እንመጣለን፡፡
–    እሺ፡፡
–    የቴክኖሎጂ ሽግግር እናደርጋለን፡፡
–    ሌላስ?
–    ሶፍትዌሩ የሚሠራው በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በመሆኑ የዕውቀትም ሽግግር እናደርጋለን፡፡
–    ጥሩ፡፡
–    አገሪቷ ለሶፍትዌሩ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ እናስቀራለን፡፡
–    ለመሆኑ ሶፍትዌሩን ሠርታችሁታል?
–    ይኸው ክቡር ሚኒስትር ይዘነው መጥተናል፡፡
–    በቃ ምላሻችንን እናስታውቃችኋለን፡፡
–    እናመሰግናለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
–    ክቡር ሚኒስትር ሶፍትዌሩን ተመለከቱ አይደል?
–    ዓይቼዋለሁ፡፡
–    ስለዚህ በዚሁ መሠረት ይሥሩልን አይደለ?
–    ለምን ሲባል?
–    ምን ችግር አለው?
–    ኪራይ ሰብሳቢ ሶፍትዌር ነዋ የሠሩት፡፡
–    ክቡር ሚኒስትር እኛ የምንፈልገውን ዓይነት ሶፍትዌር እኮ ነው የሠሩልን፡፡
–    እኛ ያቋቋምነው ድርጅት ለምን አይሠራውም?
–    መጀመሪያ ዕድል የሰጠነውማ ለእሱ ነበር፡፡
–    እና ምን ሆነ?
–    የሠራቸው ሶፍትዌሮች የሚሠሩ አይደሉም፡፡
–    ለምን?
–    ድርጅቱ እኮ መዋጥ ከሚችለው በላይ ነው እንዲያላምጥ እያደረግነው ያለነው፡፡
–    ቢሆንም ዕድል ይሰጠው፡፡
–    እስከ መቼ? እስከ ምፅአት ቀን?
–    መካከለኛ ገቢ ያለን አገር እስክንሆን ድረስ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወዳጃቸው ሚኒስትር ጋ ደውለው ሻይ ለመጠጣት ተቀጣጠሩ]
–    የሰሞኑን የባንኮቹን ውህደት እንዴት ዓየኸው?
–    በዓይኔ ነዋ ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    እኛም ብናስብበት ጥሩ ይመስለኛል፡፡
–    ምኑን?
–    መቀላቀሉን፡፡
–    አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    የሁለታችንን መሥሪያ ቤት መቀላቀል ነዋ፡፡
–    ለምን?
–    ለሥራው ቅልጥፍና ነዋ፡፡
–    ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡
–    የምን ጥንቃቄ?
–    አንዳንድ ጋዜጦች እኮ ቀልደውብናል፡፡
–    ምን ብለው?
–    የባንኮቹ ቅልቅል የፈረስና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንን እንደመቀላቀል ነው ብለው፡፡
–    ሁለቱም ፌዴሬሽኖች ሩጫ ላይ ያተኮሩ ስለሆኑ ቢቀላቀሉ ምን ችግር አለው?
–    ያው ልክ እንደ ውኃና ዘይት የማይቀላቀሉ ነገሮች ስላሉ ብዬ ነው፡፡
–    በፊት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አንድ አልነበረም እንዴ?
–    እሱማ ነበረ፡፡
–    ስለዚህ ውኃና ዘይት ይቀላቀላሉ ማለት ነው፡፡
–    ለማንኛውም የእኛን ቅልቅል እናስብበት፡፡
–    በል እሺ እኔም ልሂድ፡፡
–    የት ነው የሚሄዱት?
–    ቅልቅል!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቅልቅሉ ከሹፌራቸው ጋ እየሄዱ ነው]
–    ይኼን ማስታወቂያ ዓየኸው?
–    የቱን የቢራውን ነው?
–    ካለሱ የሚታይህ ነገር የለም ማለት ነው?
–    አይ በየቦታው ተለጥፏል ብዬ ነው፡፡
–    ይኼም እኮ በየቦታው ተለጥፏል፡፡
–    የቱ ማስታወቂያ ነው ክቡር ሚኒስትር?
–    ያ ፊት ለፊት ስልክ እንጨቱ ላይ የተሰቀለው፡፡
–    ሄሎ ደላላ የሚለው፡፡
–    አዎን፡፡
–    ለነገሩ እኔም በየቦታው ዓይቼዋለሁ፡፡
–    ለመሆኑ ምንድን ነው የሚሠራው?
–    ድለላ ነዋ፡፡
–    ምን?
–    ድለላ፡፡
–    እኛ ደላሎችን ለማጥፋት ተነስተናል ጭራሽ በስልክ መጡ?
–    ክቡር ሚኒስትር ግን ይህ ተግባራችሁ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አይሆንባችሁም?
–    ለምን ይሆንብናል?
–    በርካታ ሰው ሥር አጥ ይሆናላ፡፡
–    ለምን?
–    ደላላ ያልሆነ ሰው የለማ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው ጋ ደወሉ]
–    ስማ ባለፈው አንድ ዳይሬክቶሬት እንዲቋቋም ነግሬህ ነበር አይደል?
–    የትኛው ነበር ክቡር ሚኒስትር?
–    የጋኔን አስወጪ ዳይሬክቶሬት ነዋ፡፡
–    የምን ጋኔን?
–    የሙስና ጋኔን፣ የኪራይ ሰብሳቢ ጋኔን፣ የኒዮሊብራል ጋኔንና እንዲሁም ሌሎችም፡፡
–    አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
–    ለዚህ ዳይሬክቶሬት አንድ የስልክ መስመር ከቴሌ መውሰድ አለብን፡፡
–    የምን የስልክ መስመር?
–    አጭር የስልክ መስመር ከቴሌ ይውጣለት፡፡
–    ምን ያደርግለታል?
–    ሰዎች ጋኔኖችን ሲያዩ ሪፖርት የሚያደረጉበት፡፡
–    እ…
–    እኔን ያስጨነቀኝ ቁጥሩ ስንት ይሁን የሚለው ነው?
–    ሁሉም የሚጀምሩት በ8 ቁጥር ነው፡፡
–    ግን አራት ዲጂት መሆን አለበታ?
–    ሦስቱ ዲጂትማ ይታወቃል፡፡
–    እንዴት ይታወቃል?
–    የጋኔን ቁጥር እኮ 666 ነው፡፡
–    ስለዚህ 8 – 666 እንበለው እያልከኝ ነው?
–    እህሳ ባይሆን ስሙን ምን እንበለው?
–    የምን ስም?
–    አይ ሄሎ ደላላ፣ ሄሎ ካሽ እንደሚባለው የዚህን ቁጥር ስም ምን እንበለው?
–    ሄሎ ጋኔን!