የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሥራ አስፈጻሚዎችና የወጣት ሊግ አመራሮች ፍርድ ቤት ቀረቡ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በኦሮሚያ ተፈጥሮ ለነበረው ረብሻ ምክንያት ናቸው ተብለው የታሰሩ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሥራ አስፈጻሚዎችና የወጣት ሊግ አመራሮችን ጨምሮ በተፈጠረው ድርጊት ተጠርጥረው በፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) የታሰሩት፣ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸዋል፡፡
የኦፌኮ ተቀዳሚ ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሰባት አመራሮችና ከ500 በላይ የሚሆኑ በተለያዩ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሚገኙ አባላቶቹ እንደታሰሩበት የገለጸው ኦፌኮ፣ አንድ ተጠርጣሪ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በዋለ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ ቢሆንም፣ እስካሁን አባላቱ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ለሪፖርተር ገልጾ ነበር፡፡
ነገር ግን ከ48 ሰዓታት ቢሆን በተጠረጠሩበት ወንጀል በቁጥጥር ሥር የሚገኙት ሁሉም ታሳሪዎች፣ በክልል በሚገኙና አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ ፍርድ ቤቶች መቅረባቸውን ሪፖርተር ከፍርድ ቤቶች ያገኘው መረጃ አረጋግጧል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት እስረኞቹን ይዞ በመቅረብ እንዳስረዳው፣ ግለሰቦቹ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ለተፈጠሩት ረብሻዎችና በረብሻው ምክንያት ለጠፋው የሰው ሕይወትም ሆነ ለወደመው ንብረት ምክንያቶቹ እነሱ መሆናቸውን፣ ከሌሎች ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመሆን ሁከት እንዲፈጠር ማድረጋቸውን በማስረዳት፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው መርማሪ ቡድኑ ያለምንም ምክንያት ስማቸውን እያጠፋ መሆኑን፣ ሕዝቡ ያነሳው ጥያቄ ስላልተመለሰለት በራሱ ጊዜ ብሶት ፈንቅሎት የወሰደው ዕርምጃ እንጂ እነሱ ምንም ያደረጉት ነገር እንደሌለ በመግለጽ፣ ከእስር እንዲፈቱ ወይም ዋስትና ተጠብቆላቸው እንዲለቀቁ መጠየቃቸው ታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ በመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡