ታላቅ የ4ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር ከጁሙዓ ታህሳስ 22 እስከ ሐሙስ ታህሳስ 28/2008 = ድምፃችን ይሰማ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ታላቅ የ4ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር ከጁሙዓ ታህሳስ 22 እስከ ሐሙስ ታህሳስ 28/2008 = ድምፃችን ይሰማ

‹‹ቃላችንን እንደጠበቅን ለ4 ዓመታት ጸንተናል፤ አልሃምዱሊላህ! መብታችንን በዘላቂነት ማስከበር እስክንችል ጸንተን እንቆያለን፤ ኢንሻአላህ!!››
‹‹እንቁዎቻችን ሆይ! አናንተን በእስር ቤት ኣስቀምጠን የምናንቀላፋ አንሆንም አንሻአላህ!››
ሰኞ ታህሳስ 18/2008

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ባለፉት አራት ዓመታት ከመንግስት በኩል የሚሰነዘርብንን ኢ-ሕገ መንግስታዊ የመብት ጥሰት በጽናት እና በሰላዊ መንገድ ስንታገል ቆይተናል፡፡ በሂደቱም በርካታ መስዋእትነቶችን የመክፈላችንን ያክል በርካታ ፍሬዎችንም አግኝተንበታል፡፡ በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ከፍተኛ ንቃት ተፈጥሯል፡፡ መብቱን የሚያውቅ እና ለመብቱ ለመታገል የማይፈራ ትውልድ መፍጠር ተችሏል፤ በአላህ ፈቃድ!

በእነዚህ የትግል ዓመታት መንግስት ከሰላማዊ መንገዳችን እንድንወጣ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም፣ የትግሉን ውል በማሳት ወደቀውስ ለመክተት ያልፈነቀለው ድንጋይ ባይኖርም አሁንም ድረስ ሰላማዊነታችንን ጠብቀን እና መሠረታዊ ጥያቄዎቻችንን ሳናስነካ በትግላችን ቀጥለናል፡፡ ይህ ከአላህ የሆነ ታላቅ ችሮታ ነው፤ አልሐምዱሊላህ! በመሆኑም ቆጥረን የማንጨርሰውን ውለታ ለዋለልን ጌታ ታላቅ ምስጋና ማድረስ ኢስላማዊ ኃላፊነታችን እንደመሆኑ መጠን የትግላችንን አራተኛ ዓመት በምንዘክርበት በዚህ ወቅት የአላህን ችሮታ በማውሳት ሽኩር የምናደርስባቸው መርሃ ግብሮች የሚኖሩን ይሆናል፡፡ በመሆኑም በዚህ ሳምንት ድልን የምንከጅለውም የምንመኘውም ከአላህ ብቻ ነውና በሀቅ ላይ እግራችንን የፀና ያደርግልን ዘንድ እርሱኑ እንማፀነዋለን። ሰደቃ በማውጣትና የተለያዩ የኸይር ስራ ዘመቻዎችን በማድረግ ወደአላህ እንቃረባለን፡፡

‹‹ፍጡራንን ያላመሰገነ አላህንም አያመሰግንም›› እንዲል ሐዲሱ በዚህ እልክ እስጨራሽ የትግል ሂደት ወቅት በውስጣችን እኛም ታሪክም የማይረሳቸው በርካታ ባለውለታዎችን አፍርተናል። ተወዳጅ ነፍሳቸውን ለዲናቸው አሳልፈው ከሰጡት አንስቶ የሰጠናቸውን አማና አንግበው ራሳቸው እንደሻማ ቀልጠው ያበሩልን፣ በበዳዩ እጅ ስር ወድቀው የሚሰቃዩት ውድ ኮሚቴዎቻችን እና ብርቅዬ ወጣት እና እዛውንት ምሁራኖቻችን፣ ጋዜጠኞቻችን ሁሉ ለትግሉ ትልቅ ውለታ ውለዋል። በመሆኑም በዚሁ የሳምንት ጊዜ ውስጥ ለእነዚህ የኢስላም ልጆች እና ለቤተሰቦቻቸው በትንሹ ክብራችንን፣ አብሮነታችንንና አጋርነታችንን ለማሳየት ቤተሰቦቻቸውን፣ እንዲሁም እነሱን ያፈሩልንን ተቋማት እና ብርቅዬ ዓሊሞቻችንን በመዘየር የምንገልጽ ይሆናል። ከቤታቸው የህዝብን ጥያቄን አንግበው ለወጡት የሰላም አምባሳደሮቻችን እና ከእነሱ ጋር አብረው ለታሰሩት የህዝብ ጥያቄዎች መፈታትም አራተኛ ዓመታችን ላይ በአላህ ቤት ሆነን ብሄራዊውን ጭቆና እንዲወገድ ዱዓ እናደርጋለን። ይህ የመርሃ ግብሩ ሁለተኛ ክፍል ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የሚኖረን መርሃ ግብር ደግሞ የወደፊት ትግላችንን የሚመለከት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን የትናንቱን ስናይ እና ለፈጣሪያችን ምስጋናን ስናስገባ በዚህ ፈጣሪያችን በመረጠልን መንገድ እየታገልን ዓላማችንን ለማሳካት ትናንት በወንድሞቻችን ፊት ቃል እንደገባን ሁሉ ዛሬም ደግመን ለፈጣሪያችን ቃላችንን ማደስ ይጠበቅብናል፡፡ ይህን የምናደርግባቸው መርሃ ግብሮች በዚሁ ጊዜ ውስጥ እንዲኖሩን ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሶስተኛው የሳምንቱ መርሀ ግብር ይሆናል።

የመርሃ ግብሮቹን ዝርዝር አፈጻጸም በተመለከተ ሁሉም ሙስሊም እንደየሁኔታው እና እንደየአቅሙ በግልም በጋራም እየሆነ መተግበር የሚችል መሆኑን ከዚሁ ጋር አያይዘን ለማስታወቅ እንወዳለን፡፡

‹‹እንቁዎቻችን ሆይ! አናንተን በእስር ቤት ኣስቀምጠን የምናንቀላፋ አንሆንም አንሻአላህ!››
ብሄራዊ ጭቆናን አንሽከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!