ከማህፀን ውጭ የሚፈጠር እርግዝና (Ectopic Pregnancy) (በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም ቱፈር)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ከማህፀን ውጭ የሚፈጠር እርግዝና (Ectopic Pregnancy)
(በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም ቱፈር)
ከማህፀን ውጭ የሚፈጠር እርግዝና በአብዛኛው የሚከሰተው እንቁላልን ከእንቁላል ማቀፊያ ወይም እንቁልጢ ወደ ማህፀን በሚወስደው ቱቦ (Fallopian tubes) ውስጥ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የማህፀን ውጭ እርግዝና በሆድ ውስጥ፤ በእንቁላል ማቀፊያ ከረጢት (እንቁልጢ) እና በማህፀን አንገት ላይም ሊከሰት ይችላል፡፡
ከማህፀን ውጭ ሚፈጠር እርግዝና በአፋጣኝ ሕክምና ካልተደረገለት ከፍተኛ ለሆነ እና ሕይወትን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል የደም መፍሰስን ያስከትላል፡፡
✔ ለሕመሙ ተጋላጭነት የሚዳርጉ ሁኔታዎች
• ከዚህ ቀደም የተከሰተ ከማህፀን ውጭ እርግዝና
• ኢንፌክሽን፡- በማህፀን ቱቦዎች ላይ የሚከሰት ኢንፌክሽን በአብዛኛው በአባላዘር በሽታዎች ምክንያት የሚመጡ ናቸው፡፡
• ተፈጥሮአዊ የማህፀን ቱቦ አቀማመጥ ወይንም በቀዶ ጥገና ጊዜ የሚደርስ የቱቦ ጉዳት
✔ የሕመሙ ምልክቶች
• በመጀመሪያ ሕመሙ ምንም ዓይነት ምልክት ላያሳይ ይችላል ወይንም ደግሞ ከማህፀን ውስጥ ካለ እርግዝና ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሊሆን ይችላል፡፡
ይህም፡-
• የወር አበባ አለማየት
• የጡት ሕመም
• ማቅለሽለሽ እና እርግዝና ምርመራ ላይ እርግዝና እንዳለ የሚጠቁም ውጤት ናቸው፡፡
✔ በቀጣይነት የሚከሰቱ ምልክቶች
• የሆድ ሕመም
• ቀላል የሆነ ደም በማህፀን መፍሰስ
• እርግዝናው በእንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦ ውስጥ ከተፈጠረ እና ቱቦው እንዲቀደድ ካደረገ ለከፍተኛ የደም መፍሰስ ስለሚያጋልጥም ራስን እስከመሳት ሊያደርስ ይችላል፡፡
• ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች በሚያጋጥምዎ ጊዜ ወደ ሕክምና ቦታ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ በሕክምና ቦታም ከማህፀን ውጭ ያለ እርግዝና መፈጠሩን ለማረጋገጥ የደም ምርመራዎችና የአልትራ ሳውንድ ምርመራ እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ፡፡
• አንዳንዴም እርግዝናውን በአልትራሳውንድ ለማየት የማይቻልበት ጊዜ ላይ ከሆነ በሐኪም ጥብቅ ክትትል እየተደረገ እና የደም ምርመራዎች እየተደረጉ በአልትራ ሳውንድ እስኪረጋገጥ ድረስ ይጠበቃል፡፡
• ከማህፀን ውጭ በተፈጠረ እርግዝና ምክንያት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ከተከሰተ ግን በአፋጣኝ የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊደረግ ይገባል፡፡
✔ ህመሙን እንዴት መከላከል ይቻላል?
• ከማህፀን ውጭ የሚከሰትን እርግዝና መከላከል ባይቻልም ተጋላጭነት የሚጨምሩ ሁኔታዎችን ማስወገድ ግን ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ለአንድ በመወሰን እንዲሁም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ኮንዶምን በመጠቀም ከአባላዘር በሽታዎች እራስን መከላከል ይቻላል፡፡
• ከዚህ ቀደም ከማህፀን ውጭ እርግዝና ካጋጠመዎ ከቀጣይ እርግዝና በፊት ሐኪምዎን ማማከር ከእርግዝና በኋላም ቢሆን ሐኪምዎ ጋር ክትትል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
• ወዲያውኑ የሚደረጉ የደም ምርመራዎችና የአልትራ ሳውንድ ምርመራ የእርግዝናውን ሁኔታ ስለሚያሳውቁ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ምርመራውን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡