ተቃዋሚዎች ራሳቸውን የሚመለከቱበትን መስታዎት ይስበሩት
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ተቃዋሚዎች ራሳቸውን የሚመለከቱበትን መስታዎት ይስበሩት ( Jomanex Kassaye )==================================================
ብዙዎች ይሀ አገዛዝ እየገደለን፣ እያሰደደን፣ እያሰረን፣ አካላችንን እያጎደለ፣ እየዘረፈን፣ መብታችንን ነጥቆ በጭለማ እያኖረ የሚገዛን ከጥንካሬው ሳይሆን ከተቃዋሚ ድክመት ነው በሚለው ይስማማሉ፡፡
ከ10 ዓመታት በፊት የነበረው ተቃዋሚ ጩኸቱ የዲፕሎማቶች መንደር ጎልቶ ይሰማ ነበር፣ ዲሲ ሆኖ አዲስ አበባ ላይ ያሸብር ነበር፤ ዛሬ ነገሮች የተገላቢጦሽ ሆነው ሆድ አደር እና ዘረኛ ካድሬዎች ዲሲ ላይ ያስፈራሩ ደህንነቶች እና ጆሮ ጠቢዎች ተቃዋሚዎችን በስደትም ሆነው ያሸማቅቁ ይዘዋል፡፡
ድምጽ ለማሰማት ተጠራርቶ አዳራሽ የማይበቃው የነበረ ዛሬ የተለመዱ ፊቶች ብቻ የሚከሰቱበት ብዙዎችን ያራቀ ሆኗል፡፡
በፖለቲካችን ብዙ የተጎዱ ብዙ ዋጋ የከፈሉ ዛሬ ላይ ሆነው ሲመለከቱት አገር እናተርፋለን በሚል ሕይወታቸው የተመሰቃቀለ፤ ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ እየከፈሉም ያሉ አሉ ይኖራሉም…
ነገር ግን ተቃውሞን መምራት እኔ ብቻ ባልኩት እኔ ብቻ በምመራው መንገድ ማለት ለአገዛዙ ጥንካሬ ከመሆን ውጪ የፈጠረው ፋይዳ የለም
አገዛዙን የሚቃወም ስንል ይህ በውስጥም በውጭም ያሉትን ይመለከታል
ተቃዋሚዎች ራሳቸውን የሚመለከቱበትን መስታዎት ይስበሩት ከእውነታው ጋር ይጋፈጡ
አንድነትን የሚያክል ፓርቲ አፈር ድሜ መጋጥ የአመራሮች ድክመት ጭምር እንጂ የአገዛዙ ጥንካሬ ብቻ አይደለም፡፡
ትዕግስቱን ሸራፋ በማለት አንድነትን ማስመለስ አገዛዙንም መገርሰስ ወይም ማስገበር አንችልም!
አይደለም ኢትዮጵያን ሌላም አገር ማንቀጥቀጥ የሚችለው የሥደተኛ አቅም ሲባክን ማየት፣ ተሰላችቶም ለስርዓቱ ሲገብር ማየት ስንሰደድ አንድ ሽንፈት ፣ ወጥተን ይሄን ማየት ሁለተኛ ሽንፈት ነው፡፡ (ሂሳችንን እንዋጥ)
እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤
አገዛዙ መንግስትነት የሰጠውን አቅም እና ሃብት ተጠቅሞ ዲፕሎማቲክ ጫናውን መቋቋም ችሏል ቆዳውንም አደንድኗል፤
አገዛዙ በአገር ቤት ራሱን የሃብት፣ የሥራ እና የኅልውና ጉዳይ ምንጭ እሱ ብቻ እንዲሆን አድርጎ ዜጎችን እየገዛ ነው፡፡
…
እስከዛሬ የመጣንበትን የት መድረስም እንደምንፈልግም እናውቃለን፤ ከዜሮ መጀመር ቢመስልም የሄድንበትን ቆም ብሎ ማየት፣ እና መገምገም ፣ አዲስ አካሄድ እና ሁሉን ያካተተ አግላይ ያልሆነ አደረጃጀት አስፈላጊ ከሆነም ያለውን የሚያጠናክር ከውስጥም ከውጪ ያስፈልገናል… አሁን!
ትችት የማትቀበሉ፣ ከእኔ ወዲያ ላሳር የምትሉ ለለውጥ ካልተዘጋጃችሁ በሂደት ብቻችሁን አልያም ራሳችሁን ከገደል ማሚቱዎች ጋር ታገኙታላችሁ፡፡ አገዛዙም ባለበት ቀጥሎ ፡፡
ሌላው ወያኔ አለቀለት ዜና ለፕሮፓጋንዳ አልፎ አልፎ ቢጠቅምም ተቃዋሚዎች አገዛዙን ለመገርሰስ ወይም ለማስገበር የድርሻቸውን እንዲወጡ ከማድረግ ይልቅ ቆመው እንደደመራ እስኪወድቅ እንዲጠብቁ አድርጓል፡፡
በዚህ ያተረፈው አገዛዙ ነው፡፡
‹‹እያወቁ አለቁ›› አንሁን