ኢትዮጵያዊው ሙስሊም የፍርሀት ድባቡን አሸንፎ ለአራት ዓመታት በትግል ጎዳና ላይ ፀንቷል! (ድምፃችን ይሰማ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ኢትዮጵያዊው ሙስሊም የፍርሀት ድባቡን አሸንፎ ለአራት ዓመታት በትግል ጎዳና ላይ ፀንቷል!
ረቡእ ታህሳስ 13/2008
አምባገነን ስርዐቶች የህዝቦችን መብት በማክበር፣ ነፃነታቸውን በመጠበቅ፣ ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ፣ለችግሮቻቸው መፍትሄ በመስጠት ህዝብን ከጎናቸው ከማድረግ ይልቅ የፍርሀትን ድባብ በመፍጠር ህዝብ አንገቱን ደፍቶና ተሸማቆ በፍርሀት ታፍኖ እንዲኖር ማድረግን ይመርጣሉ፡፡ ይህ የፍርሀት ድባብን የመፍጠሩ የስነ ልቦና ጦርነት ደግሞ በተቀናጀ እና በተጠና መልኩ የሚሰራ ነው፡፡ ራስን አግዝፎ ማቅረብ፣ በፕሮፓጋንዳ እና በሀሰት ውንጀላ ተቃራኒን ወገንን ማሳጣትና ማጠልሸት፣ ደካማ አድርጎ መሳል እና መከፋፈል፣ ከዚያም ሲያልፍ ጉልበት በመጠቀም ‹‹አልችልም›› የሚል ስሜት እንዲፈጠርበት በማድረግ የጭቆና ቀንበር ተሸክሞ እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ ይህ የሁሉም አምባገነኖች ስልት ነው፡፡ በታሪክ ወደኋላ ተመልሰን የአምባገነኖችን አኳኋን ብንቃኘው የስልት እንጂ የይዘት ለውጥ አናገኝበትም፡፡
በቁርዐን በተደጋጋሚ የተወሳው አምባገነኑ ፊርዐውንም የእስራዔልን ልጆች በዚሁ መልኩ የፍርሀት ድባብ ውስጥ እንዲኖሩ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ አላህ (ሱ.ወ) የእስራዔል ልጆችን ነፃ ለማውጣት ሙሳን ሲልክ ህዝቡ የጭቆናን ቀንበር ተሸክሞ መኖርን ተላምዶት ነበር፡፡ ነብዩላህ ሙሳ (ዐ.ሰ) ይህን የፍርሀት ድባብ በማፈራረስ አምባገነኑን ፊርዐውን መጋፈጥ ሲጀምሩ ግን የእስራዔል ልጆችም ተብትቦ የያዛቸውን የፍርሀት ድር በጣጥሰው ከጎኑ መሰለፍ ችለዋል፡፡ የስኬት ጉዟቸውም የሚጀምረው ከዚሁ ፍርሀትን አሸንፈው ከጭቆና ተቃራኒ በቆሙበት ቅፅበት ነው፡፡
ግፈኞች ሰዎችን የሚያሰቃዩት አካላቸውን ለመጉዳት ሳይሆን ለሰው ልጅ እጅግ ወሳኝ የሆነውን ተስፋ እና ወኔ በመስበር በፍርሀት እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡ ከፍርሀት የተላቀቁና የነጻነት ስሜትን የተላበሱ ሰዎች ለጨቋኞች ሁሉ ራስ ምታት መሆናቸውን አምባገነኖች ሳይቀር በሚገባ ስለሚያውቁት ህዝቡ ተስፋ እንዲቆርጥ እና ወኔ እንዲያጣ፣ ብሎም በፍርሀት ተሸብቦ እንዲኖር በቃልም ሆነ በጉልበት የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ አምባገነኖች የፈጠሩትን የፍርሀት ድባብ በጣጥሶ ‹‹ጭቆናው ይብቃኝ!›› ማለት የጀመረ ህዝብ የትልቁን ስኬት መስረት የሆነውን የመጀመሪያውን ድል ተጎናፅፏል፡፡ የድል መሰረት የሚገነባው የስነ ልቦና ጦርነቶችን ተቋቁሞ፣የፍርሀትን አጥር በመሻገር ሊሰብሩት የፈለጉትን ወኔ አጎልብቶ፣ ልብን በተስፋ ሞልቶ በጽናት መጓዝ በተጀመረበት ቅፅበት ነው፡፡ በትናንሽ እንቅፋቶች ተደናቅፎ ባለመውደቅ ማስፈራያ፣ ዛቻዎች፣ እስራት፣ ስቃይ እና ግድያ የማይፈታው ህዝብ ይዞት የተነሳውን የመብት ጥያቄ ከዳር ለማድረስ የሚያስችለውን የስነ-ልቦና ስንቅ አሟልቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሙስሊምም አምባገነኖች በሀገሪቷ ‹‹የፍርሀት ድባብ አስፍነናል›› በማለት በእምነቱ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት አልፈው ‹‹እኛ የመረጥንልህን አስተሳሰብ ነው መከተል ያለብህ›› ማለት ሲጀመሩ ነበር ጥልቅ የሆነ የዲን ፍቅር በወለደው ወኔ የፍርሀት ድባቡን በጣጥሶ አደባባይ በመውጣት ‹‹ሰብዐዊ መብቴን አክብሩ! ከእምነት ተቋሜ ውስጥም እጃችሁን ሰብስቡ!›› ማለት የጀመረው፡፡ ይህ ታሪካዊ ክስተት እስከተከሰተበት ቅፅበት ድረስ ማንም የኢትዮጵያ ሙስሊምን በዚህ መልኩ የጠበቀው አልነበረም፡፡ የመብት ማስከበር ትግሉም በመንግስት ማስፈራሪያና አፈና ብዙ ከመራመድ እንደሚደናቀፍ መንግስትም ሳይቀር በፅኑ ያምን ነበር፡፡ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ፍርሀትን ከጫንቃው ላይ ያስወገደው ህዝብ ከመንግስት በኩል ድምፁን ለማፈን የደረሱበትን በደሎች ሁሉ ለነገው ረጅም ጉዞው እየደለደለ መሸጋገሪያ ድልድይ አድርጎት ይኸው እዚህ ደርሷል፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት ባልቀዘቀዘ ወኔ፣ ባልደበዘዘ ብርታት ሲታገል የነበረውም አምባገነኖች የፈጠሩትን የፍርሀት ደብባ ድል ማድረግ በመቻሉ ነው፡፡
ድል የሚጀምረው ከውስጥ ነው፤ ፍርሀትን ታግሉ ከማሸነፍ! ኢትዮጵያዊው ሙስሊምም የፍርሀት ድባቡን አሸንፎ አራት አመት በትግል ጎዳና ላይ ፀንቷል! መብቱ እስኪከበርም አዋጭ በሆኑ የትግል ስልቶች መታገሉን ይቀጥላል! ያለበት ጎዳና የድል ጎዳና ነው… ከአራት ዓመታት በፊት ፍርሀትን አሸንፎ የጀመረው የድል ጎዳና!!!
ብሄራዊ ጭቆናን አንሽከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
Like ☑ Comment ☑ Share ☑
