የፀረ ሽብር አዋጁ በወጣ በወራት ውስጥ ከታሰሩት ፖለቲከኞች አንዱ ዘሪሁን ገ/እግዚያብሄር ህክምና እንዳያገኝ መደረጉ ተገለፀ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ፕሬዝደንት አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚያብሄር የህክምና አገልግሎት እንዳያገኝ መደረጉን ቤተሰቦቹ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚያብሄር በማዕከላዊ በደረሰበት ድብደባ እጁ፣ እግሩና ጆሮው ላይ ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም ህክምና እንዳያገኝ መደረጉን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አቶ ዘሪሁን በማዕከላዊ እጁን ታስሮና ተሰቅሎ በተገረፈበት ወቅት የግራ እጁ አጥንት የተሰበረ ሲሆን የእግር ጥፍሮቹም ተነቅለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ጆሮው ላይ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
በተለይ እጁ ላይ ቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልገው ተነግሮት የነበር ቢሆንም ከክኒን ውጭ ሌላ ህክምና እንዳልተሰጠው ቤተሰቦቹ ገልፀዋል፡፡ የ17 አመት ፍርደኛ የሆነውና በዝዋይ እስር ቤት የታሰረው አቶ ዘሪሁን በአሁኑ ወቅት ለህክምና ቃሊቲ የሚገኝ ቢሆንም አሁንም ህክምና እንዳላገኘ ቤተቦቹ ገልፀዋል፡፡ የዝዋይ እስር ቤትን ህክምና እንዲያገኝ በጠየቀበት ወቅት ‹‹ከቃሊቲ እስር ቤት ጋር እየተነጋገርን ነው፣ መኪና የለም›› በሚሉ ሰበቦች ህክምና ሳያገኝ ቆይቷል ያሉት ቤተሰቦቹ ወደ ቃሊቲ ከመጣ በኋላም ፖሊስ ሆስፒታል ተመርምሮ መድሃኒት ቢታዘዝለትም የታዘዘለትን መድሃኒት ‹‹ሀኪም አላየውም፡፡ ሀኪም ያረጋግጠው›› እየተባለ ህክምና እንዳያገኝ ተደርጓል ብለዋል፡፡ አቶ ዘሪሁን የፀረ ሽብር አዋጁ በወጣ በወራት ውስጥ ከታሰሩት ፖለቲከኞች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወሳል፡፡