ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመው በሀሰተኛ ሰነዶች በመታገዝ ከማረሚያ ቤት የወጡና ያስወጡ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ተበየነ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመው በሀሰተኛ ሰነዶች በመታገዝ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ በፌዴራል ከፍተኛ እና በጠቅላይ ፍርድ ጥፋተኛ ተብለውና ይግባኛቸው ውድቅ ሆኖ በእስር ላይ የሚገኙ 11 ሰዎችን ከማረሚያ ቤት እንዲወጡ በጥቅም ተሳስረው ረድተዋል የተባሉ 16 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ሲል የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ትናንት ማክሰኞ ታህሳስ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ብይን ሰጠ።

የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸውና በእነሰለሞን ገለታ መዝገብ ስማቸው የተዘረዘረው 16 ተከሳሾች ሲሆን፤ 2ኛ ተከሳሽ ሚስባህ ከድር፣ 3ኛ ዋርደር ኢብረሃም መሀመድ፣ 4ኛ ኢንስፔክተር ገ/መድህን አልጋ፣ 5ኛ ኢንስፔክተር ኢሳያስ ከበደ፣ 6ኛ መስፍን አደላ፣ 7ኛ ቴዎድሮስ ግደይ፣ 8ኛ ዶ/ር በድሪ ጅብሪል (በሌለበት) 9ኛሰለሞን በየነ (በሌለበት) ፣ 10ኛ አማን ወርቁ፣ (በሌለበት)  12ኛ ሸምሲ ወርቁ፣ 13ኛ አማን ጀማል (በሌለበት)፣ 14ኛ ጌታቸው አቃኔ (በሌለበት) ፣ 15ኛ ሐጎስ ኪዳነ (በሌለበት) እና 16ኛ ቃሲም ከማል (በሌለበት) ናቸው።

ዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር እንደሚያስረዳውም በተለይ 3ኛ፣ 4ኛ፣ እና 5ኛ ተከሳሾች ለራሳቸውና ከ6 እስከ 16 ለተዘረዘሩት አስራ አንድ ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማስገኘት አስበው ከነሐሴ 30 ቀን 2005 እስከ መስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ በሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶች በመገልገል የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ በመቀባበል ከእስር እንዲወጡ አድርገዋል ሲል ያትታል።

ትናንት ታህሳስ 5 ቀን 2008 ዓ.ም ለነበረው የችሎት ቆይታ፣ በጉዳዩ ላይ 40ገፅ የወሰደ ብይን ተዘጋጅቶ እንደነበርና ከጊዜ አንፃር በጭብጡ ያተኮሩ ሃሳቦች መነሳታቸውን ችሎቱ አስታውቋል። በክሱ እንደተጠቀሰውም ተከሳሾቹ በፌዴራል የመጀመሪ ደረጃ በፌዴራል ከፍተኛ እና በጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የተፈረደባቸውን እና የፀናባቸውን የእስር ቅጣት ለመፈፀም በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እያሉ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች ከተከሳሾችና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በተደረገ የጥቅም ግንኙነት ተመሳጥረው ስልጣናቸውን በመጠቀም የሙስና ወንጀል ሰርተዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ ያስረዳል።

ይህንንም በሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነድ በመጠቀም በሕግ ቁጥጥር ስር የሚኙትን 11 ተከሳሾች ከእስር ለማስወጣት በተከሳሾቹ ስም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያልደረሰባቸውን የመዝገብ ቁጥሮች በመጠቀም ሀሰተኛ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤትእና የሰበር ሰሚ ውሳኔ በማዘጋት ከእስር በዋስ ይፈቱ የሚል የመፍቻ ትዕዛዝ፣ ሀሰተኛ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ፊርማ ያለበት ሸኚ ደብዳቤ በማዘጋጀት፤ እንዲሁም ሀሰተኛ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ደረሰኝን በመጠቀም ከ11ኛ እስከ 16ኛ የተዘረዘሩትን ተከሳሾች የፍርድ ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁና ይግባኝም ጠይቀው ያልተፈቀደላቸው ሆኖ ሳለ ከማረሚያ ቤት ወጥተዋል ይላል።

መዝገቡን ሲመረምር የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎትም ዐቃቤ ሕግ ያቀረበለትን 8 የሰውና 22 ገፆች ያሉት የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ሲል ብይን የሰጠ ሲሆን፤ የ1ኛ እና የ2ኛ ተከሳሾችን የመከላከያ ምስክር ለመስማትም ለየካቲት 17 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Sendek