አሁን ባለው ሁኔታ ለዉጥ አንጠብቅ – ግርማ ካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ኢሳት ላይ፣ የቀድሞ የወያኔ ባለስልጣን የነበረው አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ሲናገር ነው ያደመጥኩት። ዮሐንስ ታደስ ተካ ይባላሉ። በመሬት ጉዳይ የመንግስት ባለስልጣን ነበሩ። መረጃዎችን ይዘው ወደ ዉጭ ከተሰደዱ በኋላ መጽሀፍ ጽፈዋል። አቶ ዮሐንስ እንደጻፉት፣ በምርጫ ዘጠና ሰባት ማግስት ፣ በቦሌ አካባቢ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ካሬ ሜተር ነው ( ወደ አምስት መቶ ሄክትር ማለት ነው) መሬት ለሕወሃቶችና ለዘመዶቻቸው ተሰጥቷል።

በዚያ አካባቢ የሚኖር ድሃ የአዲስ አበባ ነዋሪ በግድ ተጨፍልቆ ነው ህወሃቶች መሬቱን የወሰዱት። በዚያ የሚኖሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች “መሬት የመንግስት ነው፤ ለልማት ነው” ተብለው ነው የተፈናቀሉት።

መሬት የሕወሃት የኢኮኖሚና የኃይል ዋና ምንጩ ነው።በአቋራጭ ለመክበር፣ ህወሃቶች መሬቱን ስለሚቆጣጠሩ አርቴፊሻሊ የቤት ዋጋ እንዲወጣ ያደረጉትም እነርሱ ናቸው። ድሃዉን እያፈናቀኡ የአዲስ አበባን መሬት እየቸበቸቡ ሚሊየነሮች ሆኑ። ፎቅ በፎት፣ ሕንጣ በሕንጣ …

አሁን አዲስ አበባ ቦታ ስለሌለ፣ ዘርፈው ስለጨረሱት፣ ወደ አዲስ አበባ ዙሪያ መዞር ግዴታቸው ሆነ። አቶ ኤርሚያስም ይሄን በደንብ አስረድቷል። ለልማት ይፈለጋል ይሉና ትንሽ ገንዘብ ሰጥተው ገበሬዉን ሂድ ይሉታል። ጠመንጃው የነርሱ፣ ፍርድ ቤቱ የነርሱ፣ ፖሊስ የነርሱ …..አንድ እናት ስለ ወያኔዎች የነገሩኝ አባባል ልዋስና “የዘመኑ ሰዎች” እነርሱ።

አንዳንድ ወገኖች የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ላይ ያተኩራሉ። ወያኔዎች ቀኝ እጃቸዉን ሰብሰበው ግራ እጃቸዉን መዘርጋታቸው አይቀርም። ማስተር ፕላኑን ሰርዘነዋል ብለው፣ ዉስጥ ዉስጡን በድሪባ ኩማ በኩል ለጊዜው ያላገኙትን በሙክታር ከድር በኩል ያገኙታል። ለነገሩ እኮ አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ፌዴራል ፣ ክልል፣ ብሄር ብሄረሰብ … የሚሉት እኮ ሲቀልዱብን ነው። ስለዚህ አዲስ አበባ ሰፋች ፣ ጠበበች፣ እዚም ያሉት እነርሱ፣ እዚያም ያሉት እነርሱ። ሃብት ነዉና፣ ገንዘብ ነውና ፣ ስልጣን በቃን፣ ገንዘብ በቃን ማለት የማያወቁ፣ ስግብግቦች ናቸውና፣ በዚህም ሆነ በዚያ ገበሬዉን ማፈናቀላቸው አይቀርም።

የኦሮሞ ተማሪዎች ከሁለት አመት በፊት ተመሳሳይ ተቃዉሞ በተናጥልና በግባታዊነት አድርገው ነበር። ያኔ ባደረጉት ነገር የተለወጠ ነገር አልነበረም። አሁን እንደ ያኔው የማይሆንበት ምክንያት የለም። አሁንም የተጀመረው ሰላማዊና ሕገ መንግስታዊ እንቅስቃሴ በቀላሉ ሊታፈን ወያኔዎች ሊቆጣጠሩት ይችላሉ። ነገሩ ተረስቶ እንደገና ደግሞ ከሁለት አመት በኋላ እንደገና ልናወራው እንችላለን። እርግጥኛ ነኝ ያ እንዲሆን ከወያኔዎች በስተቀር ሌሎቻችን አንፈልግም። ታዲታ ምንድን ነው መደረግ ያለበት ?

የተወሰኑ ነጥቦችን ላስቀምጥ፡

1. በመካከላችን ልዩነቶች እንዳሉ ማመን አለበን። ልዩነቶች ሁለት መልክ አላቸው፡ አንደኛው ባለፈው ታሪክ ላይ ያሉን ልዩነቶች ናቸው። በድሮ ጊዜ የነበረዉን አሁን ባለን ዘመናዊ አመለካከት ማየት የለብንም። ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ አማራዉ፣ ሃዲያው…ሁሉም ግፍ ደርሶበታል፤ ግፍንም ፈጽሟል። አንዱ ሌላውን እያስገበረ ነው የኖረው። አዉሮፓ ብትሄዱ፣ እሲያ ብትሄዱ ተመሳሳይ ታሪክ ነው ያለው። ለምሳሌ፣ አሁን በእንግሊዝ የሚኖሩት ብዙዎቹ ከሳክሰኒ ጀርመን፣ ከኖርማንዲ ፈረንሳይ፣ ከስካድኔቪያ …የመጡ ናቸው። ስለዚህ በዚህ ረገድ ታሪክን ለመማሪያ እንጂ ለመፈራረጃ ባለማድረግ በዚያ ረገድ ያሉን ልዩነቶች ማጥበብ እንችላለን። በተቻለ መጠን ደግሞ ብዙ ያለፈው ነገር ላይ ባናተኩርም ጥሩ ነው።

ሌላው አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታና ወደፊት እንዴት መሆን ባለበት ዙሪያ ያሉን ልዩነቶች ናቸው። ለምሳሌ ፣ አሁን ያለችው ኦሮሚያ መቀጠል አለባት የሚሉ አሉ፤ አዲስ አበባን ያካተተ አዲስ ክልል መኖር አለበት የሚሉም አሉ። አፋን ኦሮሞ የፌዴራል ቋንቋ ይሁን የሚሉ አሉ። ያን የሚቃወሙ አሉ። አፋን ኦሮሞ በግእዝ ፊድል ይጻፍ የሚሉ አሉ፤ ላቲን ይሁን የሚሉ አሉ። እነዚህን እና የመሳሰሉ ልዩነቶች መኖራቸው ችግር የለውም። አብረን እንዳንሰራ መሰናክል ሊሆኑ አይገባም።

እነዚህን ልዩነቶች የሚያጠብ ፣ ሰጥቶ በመቀበል መርህ፣ ለእርቅና ለሰላም ሲባል ካለን አቋም ትንሽ ፈቀቅ ብለን፣ አማራጭ ሐሳቦችን ማቅረብ ይቻላል። (በዚህ ጉዳይ እንደዉም ከነበረኝ አንዳንድ አቋሞች ፣ ትንሽ ፈቀቅ በማለት አማራጭ ሐሳቦችን ይዤ ለመመለስ እሞክራለሁ)

2. ጸረ-ዴሞክራሲያዊና አፍራሽ አስተሳሰቦችን መታገስ የለብንም ። ለምሳሌ “ይሄ መሬት የዚህ ብሄረሰብ ነው፤ ሌሎች መጤዎች ናቸው …” የሚለው ዘረኛ አስተያየት የሚያንጸባርቁ ቡድኖችን በጋራ መመከት ያስፈልጋል። ማንም ኢትዮጵያዊ በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት የመኖር መብት እንዳለው መተማመን አለብን።

ብዙዎች የኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የደረሰውን ግፍ ቢያወግዙም፣ በተማሪዎች ሲባሉ የነበሩ መፈክሮች ግን አልተመቻቸውም። “ፊንፊኔ የኦሮሞ ነው፣ ቡራዪ የኦሮሞ ነው፣ ሰበታ የኦሮሞ ነው …” ማለት፣ ከዚህ በፊት በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ ሰሞኑን ደግሞ በአምቦ፣ በጉሩ ፈርዳ፣ በቤኔሻንጉል …የደረሱትን የዘር ማጽዳት ወንጀል ለተከታተለ፣ የችግሩም ሰለባ ለሆነ ማህበረሰብ በጣም የሚቆረቁር ነው።

በመሆኑም ይሄንን፣ በሌላው ማህበረሰብ አይምሮ ዉስጥ ሊኖረ የሚችለው አስተሳሰብ፣ እንዲጠራ ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም የኦሮሞ ልሂቃን በዚህ ረገድ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው። ተማሪዎቹ ልሂቃኑ የሚጽፈውን ነው የሚያነቡት። ፍላጎቱና ቁርጠኝነቱ ካለ፣ ልሂቃኑ ይሄንን ሊያስተካክሉ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። በቅርቡ ፕሮፌሰር ህዝቄል፣ አቶ ጃዋር በኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ፣ እንዲሁም ዶር በያን በኢሳት ጀመረዉታል። ይህ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አለበት። (በዚህ አጋጣሚ ለነዚህ ወንድሞቼ ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ)

3. የወያኔዎች ትልቁ መሳሪያቸው እኛን በዘር መከፋፈል መቻላቸው ነው። በመሆኑም ዶር በያን እንዳሉት መንቃት አለብን። መጠንቀቅ አለብን። ለኦሮሞ ተቆርቋሪ መስለው፣ የኦሮሞ ስም ይዘው ፣ ሌላው ማህበረሰብ ኦሮሞዎችን እንዲፈራና እንዲጠራጠር ለማድረግ፣ በሺሆች የሚቆጠሩ፣ ቱባ ደሞዝ የሚከፈላቸው የሕወሃት ካድሬዎች እንደሚወራጩ ማወቅ አለብን። በአሁኑ ጊዜ የወያኔ ትልቁ ራስ ምታት የኦሮሞ ተማሪዎችን እንቅስቃሴን፣ ሌሎች ሊቀላቀሉት ይችላሉ የሚል ነው። ሌሎች እንዳይቀላቀሉ ማድረግ ከቻሉ፣ ከሁለት አመት በፊት እንዳደረጉት፣ የኦሮሞ ተማሪዎች፣ ነጥለው፣ ለመጨፍለቅ አያቅታቸውም። ስለዚህ በድጋሚ እጽፋለሁ፤ መንቃት አለብን።

4. የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄያቸውን የጀመሩት ማስተር ፕላኑን በመቃወም ነው። ማስተር ፕላኑን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች አሉ። ብዙዎቻችን በመርህ ደረጃ አምስተር ፕላኑን አንቃቀምም ። ብዙዎች ደግሞ ያቃወማሉ። በማስተር ፕላኑ ያለው ልዩነት አብረን እንዳንሰራ ሊያግደን አይገባም። በመሆኑን በተቻለ መጠን የትግሉን አቅጣጫ ልዩነቶችን በማይፈጥሩ አጀንዳዎች ዙሪያ ቢሆኑ መልካም ነው። ሁላችንም ሊያስማማ የሚችል ነጥቦችን ፕሮፌሰር ሕዝቄል አስቀምጠዉልናል። የኦሮሞና የሌላው ህዝብ ጥያቄ አንድ አይነት እንደሆነ ነው ያስረዱን። “የሁሉም ጥያቄ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ነው” እንደሆነ ነው የገለጹት። ፕሮፌሴሩ አዲስ አበባ ማደጓን እንደማይቃወሙ ግን ማንኛውም ልማት ሲደረግ የሕዝቡን ፍላጎት ባካተተ መልኩ መሆን እንዳለበት ነው ለማሳየት የሞከሩት። ይሄ ደግሞ ሁሉንም ወገን የሚያስማማ መሰለኝ።

ስለዚህ በጋራ የሚደረገው ትግል በሚከተሉት የትግል ማሰባሰቢ ነጥቦች ዙሪያ ቢሆኑ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ሌሎችም ሊጨምሩ ይችላሉ።

– ገበሬው የመሬት ባለቤት ይሁን
– ተታሰሩ በሙሉ ይፈቱ
– የተደበደቡ እንዲሆን የተገደሉ ወገኖች ቤተሰቦች ካሳ ይሰጣቸው
– ግድያና ድብደባ የፈጸሙ፣ ግድያና ድብደባ እንዲፈጸም መመሪያ የሰጡ ለፍርድ ይቅረቡ

5. በነጥብ አምስት ስር በተቀመጠው መስረት፣ በሁሉም ቦታዎች ሰላማዊ፣ የእምቢተኝነት ዘመቻን ለማድረግ ፣ በአገር ቤት ያሉ እንደ መድረክ፣ ሰማያዊ፣ መኢአድ ፣ ያሉ ልዩነቶቻቸውን ጠብቀው በሚያስማሙ ነጥቦች ዙሪያ በጋራ፣ ሰላማዊ ሰልፎችን የመሳሰሉትን ለመጥራት የጋራ ግብረ ኃይል በቶሎ ቢያቋቋሙ ጥሩ ነው። ለነዚህ ደርጅት ከዚህ በፊት እንደማደርገው ትልቅ ተማጽኖ አቀርባለሁ። ከዞህ በፊት ተጨቃጭቀን፣ አንድ ሁለት ተባብለን ይሆናል። ግን ጊዜው የከፋ ነው። የግድ በአንድ ላይ መሰባሰብ አለብን።

በዉጭ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማቀናጀት ደግሞ በዉጭ ያሉ ደርጅቶች እንደ ሸንጎ፣ የሽግግር ምክር በቤቱ፣ ኦዴፍ፣ የግንቦት ሰባት አርበኞች የውጭ አመራር፣ የኦሮሞ ተማሪዎች ማህበር፣ የሶሊዳሪቲ ንቅናቄ …የመሳሰሉት ኤጎዋቸውን ትንሽ ዋጥ አድርገው፣ ቢያንስ በዚህ ጊዜ ፣ ልዩነቶቻቸው እንደተጠበቁ፣ በአገር ቤት የሚደረገውን ሰላማዊ ትግል በመደገፍ አንጻር፣ እንደ ኢሳት፣ የኦሮሞ ሜድይ ኔትዎርክ የመሳሰሉትን የበለጠ በማጠናከሩ አንጻር፣ የዉጭዉን ማህብረሰብ ሎቢ በማድረጉ አንጻር፣ የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎችን በማዘጋጀቱ አንጻር በጋር የሚሰራ የጋራ ግብረ ኃይል በቶሎ ቢያቋቁሙ ጥሩ ነው።

አንድ የጋራ ግብረ ኃይል የሚባል ደርጅት አለ። በየጊዜው ሰልፍ ይጠራል። ግን የሚመጣ ሰው የለም። የኦሮሞም ኮሚኔቲ የተለያዩ ሰለፎች ያደርጋል፣ ግን እስቲ ቁጠሩት የተደረጉትን ሰለፎች ….ማንም ከቁም ነገር አልቆጠረንም። ግን በተቀናጀ መልኩ፣ በስሜት ሳይሆ በቂ ቅስቃሰሳና ዝግጅቶ በማድረግ፣ ዉጤት በሚያስገኙ ቦታዎች (ያኔ ሳዉዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት እንደተደርገው) ሰልፎችን ማድረግ ብንችላ ብዙ ሊረዳ ይችላል። ለዚህ መሰባሰብ ያስፈልጋል።

እንግዲህ አሁን እየታየ አይለው ከዚህ በፊት እንደታዪት ብልጭጭ ብሎ የሚጠፋ እንቅስቃሴ እንዲሆን ካልፈለግን፣ ከወሬ፣ ከንዴት ያለፈ ሥራ መስራት አለበን። አሁን ባለንበት ሁኔታ ለዉጥ አይመጣም። መሰረታዊ ሮኮንፊጉሬሽን ያስፈልገናል።