የህወኃት ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር የሚቆርጥበት›› “የከፋፍለህ ግዛ ” መጋዝ አርጅቷል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የህወኃት መንግስት ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን በጣም የተሳሳተ ግምት ነው ያለው፡፡ አይደለም ሌላው ነጻ ኢትዮጵያዊ የእነርሱ ተላላኪዎችና ጥቅም ተጋሪዎች በሰሩት ወንጀል ፍርሃትና በጥቅም የሚያዩትን አላየንም ፣ የሚሰሙትን አልሰማንም ብለው ይካዱ እንጂ በህዝቡ ውስጥ እስካሉ የሚሆነውን እያዩና እየሰሙ ስለመሆናቸው ቅንጣት መጠራጠር የለባቸውም፣ በእብሪት ታውረው እንጂ፡፡ ታዛዥ ጀሌዎቻቸው እየተፈጸመባቸው ያለውንና የሚታዘዙትን ያውቃሉና ነጻ ቢሆኑ ምን ያህል በህወኃት ጭቆና ስር እንዳሉና የህወኃት የበላይነት የቱን ያህል እንደሆነ በነገሩን ነበር፤ ግን የሚነግሩን ቀን የቀረበ ስለመሆኑ የሚያጡት አይመስለኝም ፡፡

ለመገዛትና ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት ቢወስኑም የሚሠጠውና የሚለወጠው እጃቸውና ሆዳቸው እንጂ ከአደባባይ መልስ ከእነርሱ ጋር ብቻ ለብቻ የሚቀረው ኅሊናቸው እንደሚያፋጥጣቸው የፈጣሪ ትዕዛዝ ነውና ጨርሰው ሊሸጡትም ሆነ ሊሸሹት አይቻላቸውም፡፡ ለዚህም ነው ራሳቸውን ከኅሊናቸው ለማሸሽ በተለያየ መደበቂያ ( አልኮል ፣ ሴት ጭን ፣ ….) ውስጥ የሚሸጉጡት፡፡ ህወኃቶቸ የገተሩት ህንጻ በእኛ/ህዝብ መሃል መሆኑን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዷ ቁራሽ መሬት ሳትቀር የማን እንደነበረች ፣እንዴት እጃቸው እንደገባችና እንደተዘዋወረች … ከዬት በመጣ ገንዘብ እንደተገነባና የሸሸው ዶላርና ፓውንድ እንዴትና ከየት እንደተገኘ ሁሉ የተነጠቀውም፣ የተሰጠውም ከህዝብ ነውና ከህዝብ ሊሰወር አይችልም፡፡ የት እንደተደበቀም ሆነ እንደተቀመጠ -ከቁም ሣጥን እስከ ባንክ ይታወቃል፤ የቀን ጉዳይ ነው ከተደበቀበት ሲወጣ፣ከተጫነበት ሲወርድ ጊዜ አሳይቶናል፣ ነገም ያሳየናል ፡፡ ጊዜ ለኩሉ//

የድንጋይ ክምሩንና ገንዘቡን ብቻም አይደለም የሰዎቹን ማንነት፣ መነሻና የደረሱበትን ሁሉ ህዝብ ያውቀዋል፡፡ በ1983 ጠላ ቤት የምንተዋወቃቸው ዛሬ እኛ ወደተወደደብን የቧንቧ ውኃ ስንወርድ እነርሱ ‹‹ ሽቅብ ተምዘግዝገው›› ሸራተን አንሷቸው ዱባይና ታይላንድ ለጭንና ለአረቄ ሲጓዙ እንዳላየን የምንሆነው በጊዜ ምክንያት ‹‹የቀን እንጂ የሰው ጀግና የለውም›› ብለን እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በመሳሪያ፣ በገንዘብና በሥልጣን ጊዜውና ሁኔታው ለያየን እንጂ ሁሉም የተፈጸመውም ያለውም በዚህቺው አገር ሲያልፍም ፕላኔት ነው፡፡ በታሪክ ከህዝብ የተደበቀ ምስጢር የለም፡፡ ህዝብ ሁሉንም ያውቃል፡፡ እኛም የሚያስቡንን ያህል ሞኝና ተላላ አይደለንም፣ ለጊዜውም ቢሆን ጀግናው ጊዜ ጀግኖብን ‹‹ማወቁን እናውቃለን ፣ብንናገር እናልቃለን ›› በሚል አንገታችን ደፍተን ነው፤ አሁን ግን አንገታችን ቀና የምናደርግበት ደወል ድምጽ ከአራቱም አቅጣጫ እየተሰማ ነው፡፡ ህወኃት ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር የሚቆርጥበት›› የመከፋፈያና ማናቆሪያ መጋዝ ‹‹ተበልቶ ›› እያለቀ ነው፣ አልቋል ማለትም ያስደፍራል፡፡ ከፋፍሎ ማሸማቀቅ፣የህወኃትና ጀሌዎቹ የአንገት ማስደፋትና ማጨራረስ ፣የእብሪትና ማን አለብኝነት …. ጀንበር አዘቅዝቃለች፡፡ ቀሪዋ አጭር ጊዜ የሱባኤ፣ ኑዛዜና ንስሃ ናት፣ያውም በመጨረሻም ቢሆን የፈጣሪን- የእውነትን አሸናፊነት ለመረዳት ለታደሉት፡፡ የእኛ ቀጣይ ተግባር የደወሉ ድምጽ በእኩል ከዳር እስከዳር እንዲሰማ ማድረግና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ የኅብረት ድምጹን እንዲያሰማ ማስተባበርና ማቀናጀት ነው፡፡ በቸር ያገናኘን// 27/03/08 Girma Bekele