በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመከላከያ ምስክርነት ይቅረቡ አይቅረቡ ዙሪያ የተነሳው ክርክር ሰበር ሰሚ ችሎት ደረሰ::


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመከላከያ ምስክርነት ይቅረቡ አይቅረቡ ዙሪያ የተነሳው ክርክር ሰበር ሰሚ ችሎት ደረሰ::የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ የተቃወመው ዓቃቤ ሕግ፣ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን በመጥቀስ ለሰበር ሰሚ ችሎት ማመልከቻ ማቅረቡን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በሽብር ድርጊት ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው ማረሚያ ቤት በሚገኙት በእነ ዘመኑ ካሴ የክስ መዝገብ በመከላከያ ምስክርነት በተቆጠሩት የግንቦት ሰባት አመራር የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣በመከላከያ ምስክርነት እንዳይቀርቡ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ የነበረው ይግባኝ ኅዳር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ውድቅ ተደረገ፡፡

ተከሳሾቹ ከተመሠረተባቸው ክስ አንዱ የግንቦት ሰባት አመራር ከነበሩትና ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ከየመን ወደ አስመራ ሊሄዱ ሲሉ ከሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው ከተሰጡት አቶ አንዳርጋቸው ጋር ተገናኝተው መመርያ መቀበላቸውን የሚመለከት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አቶ አንዳርጋቸው በፌዴራል ማረሚያ ቤት ስለሚገኙ በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ ክሱን እየመረመረ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት አመልክተው ፍርድ ቤቱም ተቀብሏቸዋል፡፡

የተከሳሾቹን አቤቱታ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ ያመለከተው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ፣ አቶ አንዳርጋቸው በእነ ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የክስ መዝገብና በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የክስ መዝገብ የዕድሜ ልክና ሞት ፍርደኛ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ምስክርነት ለመስጠት እንደማይችሉና መብታቸው የተገፈፈ መሆኑን አስረድቶ ተቃውሞ ነበር፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን አቶ አንዳርጋቸው መብታቸው የተገፈፈው ስለራሳቸው እንጂ ስለሌሎች ምስክርነት መስጠት ስላልሆነ ሊመሰክሩ እንደሚገባ ገልጾ፣ የዓቃቤ ሕግን ማመልከቻ ውድቅ በማድረግ ቀርበው እንዲሰሙ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

አቶ አንዳርጋቸውን በመከላከያ ምስክርነት እንዲያቀርብ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ታዞ የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ሳያቀርባቸው ቢቆይም፣ ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ደብዳቤ ግን ‹‹አቶ አንዳርጋቸው ማረሚያ ቤት የሉም፤›› ብሎ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ተከሳሾቹ የማረሚያ ቤቱን ምላሽ በመቃወም አቶ አንዳርጋቸው አገር ውስጥ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉና በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር እንደሚያውቁ በመጠቆም፣ ለእነሱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ተመካክሮ እንደሚያሳውቃቸው ገልጾ በቀጠሮ ላይ እንዳሉ፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ አቶ አንዳርጋቸው በመከላከያ ምስክርነት ሊቀርቡ እንደማይገባ ለሥር ፍርድ ቤት ያመለከተበትን ምክንያት ጠቅሶ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቦ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ መርምሮ በሰጠው ብይን በፍርድ ቤት እንዲቀርብ የታዘዘ ምስክር ‹‹ይቅረብ አይቅረብ›› ተብሎ ይግባኝ ሊባል እንደማይቻል በመግለጽ፣ የዓቃቤ ሕግን ይግባኝ እንዳልተቀበለው አስታውቋል፡፡የጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ የተቃወመው ዓቃቤ ሕግ፣ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን በመጥቀስ ለሰበር ሰሚ ችሎት ማመልከቻ ማቅረቡን ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር