“ልማታዊ መንግስት” ነኝ ብሎ ራሱ የሚያወድሰው ኢህኣዴግ ኣዲስ ኣበባን የሚያለማ ኣዲስ ማስተር ፕላን ኣዘጋጀው ብሎ ኣወጀ።
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።

Amdom Gebreslasie – “ልማታዊ መንግስት” ነኝ ብሎ ራሱ የሚያወድሰው ኢህኣዴግ ኣዲስ ኣበባን የሚያለማ ኣዲስ ማስተር ፕላን ኣዘጋጀው ብሎ ኣወጀ።የልማቱ ዋነኛ ትኩረቱ ደግሞ በኣዲስ ኣበባ ዙርያ የሚገኙ ከተሞችና ገጠር ወረዳዎች ሲሆን የኦሮምያ ልዩ ዞን ተብሎ የሚታወቅ ነው።
ልማት የሚጠላ ሰው ያለ ኣይመስለኝም። በዚህ ምክንያት የሚወጣው የልማት እቅድ ሁሉም ሊባል ዩሚችል ሃገር ወዳድ ሰው እንደሚደግፍ ይጠበቃል።የኦሮምያ ወጣቶች የሚበዙባቸው በርካታ ሰዎች ግን ይህ “ልማት” የተባለው የኣዲስ ኣበባ ማስተር ፕላን ክፉኛ እየተቃወሙት ይገኛሉ።ለዚህም ኣሳማኝ ምክንያቶች ያሏቸው ሃሳቦች ያቀርባሉ።
፩) ይለማሉ በተባሉት ኣከባቢ ኑዋሪ የሆኑ ገበሬዎች ከሃያ ዓመት በላይ እንዳጋጠማቸው ያለ ካሳ፣ ያለ በቂ ዝግጅት ከመሬታቸው ይፈናቀላሉ።
፪) ገበሬዎቹ የኑራቸው መሰረት ከሆነ ማሳቸው ከተፈናቀሉ በገዛ መሬታቸው ድሆች እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል።
፫) የህዝቡ ባህል ቋንቋ እየተዋጠ ይሄዳል፣ህዝቡ ወደ ጎን እየተገፋ ሲሄድ መድረሻ ያጣል ይላሉ።
እነዚ ስጋቶች ወደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተሎ ብለው ድቅን እንደሚሉ ኣየጠራጥርም። ስጋቶቹ እንድንጋራቸው የሚያስገድዱን የ20 ዓመት የኢህኣዴግ ተግባራት ጠንቅቀን ስለምናውቅ ነው።
*** የነዚህ ችግሮች ምንጭ
1) ኢህኣዴግ “መሬት የህዝብና የመንግስት ነው” የሚል ፖሊሲው በህገመንግስቱ ጭምር ማስፈሩና መሬቱ ለራሱ ጥቅም ለማዋል እዲጠቅመው ብሎ በማሰብ “መንግስት ማለት ህዝብ ነው። ስለዚ መንግስት የመሬት ባለቤት ነው። ማስተዳደርም ኣለበት” የሚል እቅድ እየተገበረ ይገኛል።
2) ሌላኛው የችግሩ ምንጭ የሊዝ ኣዋጅ ሲሆን ገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ ሲገቡ ዋነኛ መተዳደርያ ሃብታቸው የሆነ ማሳቸው ያጣሉ።
” ሃብትህ ጣራና ግድግዳ ብቻ ነው” በሚል ኣዋጅ ያለ ካሳና ያለ መተዳደርያ ስራ ሁነው መሬታቸው ይነጠቃሉ።
3) በመሬት ጉዳይ የህግ የበላይነትና ፍትህ ጠፍተው በካድሬ የበላይነትና ሙስና ተተክተው ገበሬ ተነቅሎ እየሄደ እያየ መፍትሄ ማበጀት ያልቻለ ደንታቢስ መንግስ መኖር።
4) ከህዝብ ጥያቄ ይልቅ ያራሳቸውና የሙሰኛ ካድሬዎቻቸው ጥቅም የሚያዳምጡ ባለስልጣናት መብዛት ።
5) ባለፉት 20 ዓመታት በኣዲስ ኣበባ ስር የሚተዳደሩ ገጠር ቀበሌዎች ኑዋሪ ገበሬዎች ከልማቱ ተጎጂዎች እንጂ ተጠቃሚ ኣለመሆናቸው ለዘንድሮ እቅድ ተቃውሞ የራሳቸው ሚና ተጫውተዋል።
ከህግ ይልቅ ካድሬ የሚያሽከረክረው የመሬት ኣስተዳደር ተቃውሞውና ችግሩ በኣዲስ ኣበባ ብቻ ያጋጠመ ኣይደለም። በመላ ኣገሪቱ በስፋት እያጋጠመ ያለው ችግር ነው።
ለምሳሌ በመቐለ ዙርያ የሚገኘው የእንደርታ ህዝብ መሬቱ በልማትና በከተማ መስፋፋት ምክንያት በባለ ስልጣናትና ካድሬዎች ተነጥቀዋል ኣሁንም እየተነጠቀ ይገኛል። ለዚህም ተቃውመው በተደጋጋሚ ሲገልፅ ነበር ኣሁንም በመግለፅ ላይ ይገኛል።
መሬቱ ከገጠር ወደ ከተማ ሲገባ ከ100 እስከ 170 ካሬ ሜትር መሬት ብቻ ይዞ እንዲቀር ተደርጓል። የሚሰጠው ካሳም እጅግ በጣም ጥቂት ነው።

መሬቱ ወደ ሕጋዊ የባለቤትነትና የቤት ፕላን ለማፅደቅ ወደ ቀበሌ ወይ ማዘጋጃ ቤት ሲሄድ ሙስና እንዲከፍል ይገደዳል።
ለምሳሌ በያዝነው ሳምንት በመቐለ ኣይናለም በምትባል ቀበሌ የሚገኙ ገበሬዎች መሬታቸው ያለ ካሳ ተነጠቁ፣ የተቀረችው መሬታቸው ሕጋዊ የከተማ ፕላን ለማውጣት ወደ ሓድነት ክፍለ ከተማ ሲሄዱ ኣንድ የክፍለ ከተማ ኣንድ ካድሬ ብቻ ከ52 በላይ ኑዋሪዎች እያንዳንዳቸው 50 ሺ ብር ( ሓምሳ ሺ ብር ) እንደተቀበለ በግምገማ የተረጋገጠ ሲሆን ለዚህ ጥፋቱም በይቅርታ እንደታለፈ ታውቋል። ህዝቡም ሰውየው 50 ለቃ የሚል የሙስና መጠርያ መዓርግ ሰጥቶታል ነው።
ይህ መሰል ግልፅ ዘረፋ በህዝቡ እየተፈፀመ እየታየ የኣዲስ ኣበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ቢገጥመው የሚደገፍ እንጂ ሊኮነን ኣይገባም።
የነ ወይዘሮ ኣልጋነሽ ገብሩ ጥያቄም ” በከተማ ማስፋፋት ምክንያት ያለ በቂ ካሳ፣ ያለ በቂ ቤት መስርያ ቦታ መስጠት መሬታችን ኣሳልፈን ለነጣቂ ካድሬዎች ኣንሰጥም ” የሚል ነው።
መንግስት ለዚህ ህዝባዊ ጥያቄ ተገቢ መልስ ከመስጠት ይልቅ የህዝቡ ተወካዮች “የኣሸባሪነት” ብሎም “መንግስት በሃይል ለመናድ” የሚል ፍረጃ ተደርጎባቸው ወይዘሮ ኣልጋነሽ ገብሩን ጨምሮ 7 የእግሪ ሓሪ ኑዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸው ይታወቃል።
ልዩነቱ በኦሮምያ ያለው ወጣት የህዝቡ ችግር የበለጠ ያመዋል፣ ይሰማዋል የትግራይ ወጣት የህወሓት ባለስልጣናት ቁጣ ያስፈራዋል ነው።
መንግስት ይሁን ሌላ ኣካል ልማት ሲያስብ የኣከባቢው ማህበረሰብ ጉዳትና ጥቅም ኣስቀድሞ ግምት ውስጥ ማስገባት ይጠበቅበታል።
መንግስት በኣዲስ ኣበባ ማስተር ፕላን ዙርያ ሁለት መሰረታዊ ሃሳቦች ሊረዳ፣ ሊከውንና ሊመልስ ይገባል።
ሀ) የማስተር ፕላኑ ፋይዳ ለኣከባቢው ህዝብ ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዲደግፍ ማድረግ።
ለ) ማስረዳት ካልቻለ የህዝቡ ጥያቄ በሚመልስ መልኩ ፕላኑ ከልሶ እንዳዲስ ኣዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባት ይጠበቅበታል።
ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ግን ኢህኣዴግ ከመሬት ባለቤትነት ወጥቶ ወደ ማስተዳደር ስራ ብቻ መሸጋገር ለመቻል የሚያግዝ የመሬት ባለቤትነት ፓሊሲው መቀየር ኣለበት።
ኢህኣዴግ የኦሮሞ ወጣት ተማሪዎች ዓመፅ ለማስቆም እየወሰደ ባለው ያልተመጣጠነ እርምጃም ተጠያቂው ነው።
ሕገ መንግስቱ ዜጎች መንግስት በሚሰራቸው ስራዎችና እቅዶች በሰለማዊ ሰልፍ ይሁን በህዝባዊ ስብሰባ ተቃውማቸው የመግለፅ መብት ኣረጋግጦላቸዋል።
ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒ በፕላኑ ዙርያ ዜጎች የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፍም ህዝባዊ ስብሰባም እንዳያካሂዱ ከልክለዋል።
ለምሳሌ መድረክ በጉዳዩ ከህዝቡ ለመወያየት ያካሄደው ጥረት ከልክለዋል።
ስለዚ ሕገ መንግስቱ የተሰጣቸው ሰለማዊ ሰልፍና የመሰብሰብ መብታቸው መንግስት ሲከለክላቸው በራሳቸው መንገድ ኣስኬዱት።
የኣዲስ ኣበባ ኣዲሱ ማስተር ፕላን ኢህኣዴግ ራሱ ከህዝባዊ መንግስት ወደ ገዢ የብርዡዋ መደብ ወይም ካፒታሊስት ኣካል ማሸጋገሩ ያረጋገጠበት ኣጋጣሚ መሆኑ ነው።
በድህረ ምርጫ 97 በመላ ኣገሪቱ የምንገኝ የተለያዩ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ኣብዮታዊ ዲሞክራሲ የማጥመቅ ሙከራ ኣድርጎ ነበር። በወቅቱ የቀረበው ያለፉ ስርዓቶች ያካሄዱ የልማት ስራዎች ከራሳቸው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ኣንፃር #ኣዲስ_ኣበባ_ኣዳማ_ዲሬዳዋና_ሃረር መስመር ብቻ የነበረ ሲሆን የተቀረው ህዝብ ግን ተገልሎ እንደቆየ ያትት ነበር።
ዛሬ ግን ራሳቸው በቡርዥዋ ወይም ካፒታሊስት ቦታ ስላገኙት ሲቃወሙት የነበረው ስራ እየደገሙት ይገኛሉ።
የተቀረነው ኢትዮጵያውያንም በኣዲስ ኣበባ ማስተር ፕላን ዙርያ የምንጠይቅበት ምክንያት ኣለን። እሱም የሃገሪቱ ህዝብ እኩል የመልማት መብት እንዳለንና ያልተመጣጠነ የመልማት እቅድ መስተካከል እንዳለበት ማሳሰብ ነው።
የኦሮሞዎች ጥያቄ ኣክብረን ተገቢ ፍትሃዊ መልስ እንዲሰጣቸው ልንደግፍ እንጂ ልንቃወም ኣይገባም።
መንግስት በኦሮሞ ወጣቶች እያደረሰው ያለው ያልተመጣጠነ እርምጃ እቃወማለው።
ነፃነታችን በእጃችን ነው።
IT IS SO.…!
