በጣና በለስና በጊቤ አንድ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በደረሰ ብልሽት በመላ አገሪቱ የኃይል አቅርቦ ተስተጓጉሏል
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
በጣና በለስና በጊቤ አንድ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በደረሰ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያና የኤሌክትሮኒክ መቆጣጠሪያ ብልሽት፣ በመላ አገሪቱ የኃይል አቅርቦ ተስተጓጉሏል፡፡ ቅዳሜ ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በአገሪቱ ትልቁና 460 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ላይ በሚገኘው ጣና በለስ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መቆጣጠሪያ ተበላሽቷል፡፡
ይህንን ብልሽት ለማስተካከል እየተሞረከ ባለበት ወቅት በነጋታው እሑድ ኅዳር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ በጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ ተመሳሳይ ብልሽት አጋጥሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከጊቤ አንድ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተነስቶ ከሰኮሩ ከተማ ወደ ጌዶ የተዘረጋው የኃይል መስመር አደጋ ደርሶበታል፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡30 እስከ 10፡30 ሰዓት፣ ኅዳር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ ከ9፡30 ሰዓት ጀምሮ በመላ አገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጧል፡፡ በዚህ የኃይል መቋረጥ ነዋሪዎች በሚያካሂዱት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ ከጥቃቅንና ከአነስተኛ አምራቾች እስከ ግዙፍ ማምረቻ ተቋማት ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት አቅጣጫዎች አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቀላል ባቡር ትራንስፖርትም መስተጓጎል ገጥሞት ነበር፡፡
የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው ተንቀሳቅሰው ችግሩን ለመፍታት እየሞከሩ መሆኑ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
460 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ያለው ጣና በለስና 184 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨቅ አቅም ያለው ጊቤ አንድ፣ በብሔራዊ የኃይል ቋት ውስጥ መግባት ባለመቻላቸው በአገሪቱ ችግር ተፈጥሯል፡፡
በዚህ ምክንያት በመላ አገሪቱ ኃይል ከመቋረጡም በላይ፣ ችግሩ እስካሁን ባለመፈታቱም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም የኃይል መቆራረጥ እያጋጠመ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ እነዚህ ችግሮች በአሁኑ ወቅት የጎላ ደረጃ ይድረሱ እንጂ ችግሮቹ ያልተፈቱባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡
ከእነዚህ ውስጥም የመለዋወጫ ዕቃዎች በወቅቱ አለማዘጋጀት፣ በግድቦች አስተዳደር የባለሙያ እጥረት፣ አሮጌ የማሰራጫና ማስተላለፊያ መስመሮች በአዲስ አለመተካትና አሻጥረኛ ሠራተኞች መኖራቸው ለችግሩ መባባስ እንደ ምክንያት ያስቀምጣሉ፡፡
አሁን በተፈጠረው ችግር ብቻ አዲስ አበባ ከ120 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት መከሰቱን መረጃዎች አመልክተው፣ በአንዳንድ መንደሮች ኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ቅንጦት እየሆነ ነው፡፡
አሁን ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን፣ በመስኩ ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ እንደሆነ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡