ሰመጉ ብሔር ተኮርና ልማትን መሠረት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ እየተባባሱ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ብሔር ተኮርና ልማትን መሠረት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ እየተባባሱ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡

ሰመጉ ብሔር ተኮርና ልማትን መሠረት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተባብሰዋል አለ

የአገር ውስጥና የውጭ የመገናኛ ብዙኃን አባላት፣ የተለያዩ ኤምባሲ ተወካዮችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከአፋር ክልልና ከምዕራብ ሸዋ ዞን የመጡ የጥቃት ሰለባዎች በመንግሥትና በመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች ተፈጸመብን ያሉትን በደል አሰምተዋል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በሕግ እንዲጠየቁላቸውና መንግሥትም ወደ ታች ወርዶ ያለውን ችግር በአፋጣኝ እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን የኖኖ ወረዳ ነዋሪ የነበሩ ሁለት አርሶ አደሮች በአካባቢው ከፍተኛ ብሔር ተኮር የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን ገልጸው፣ በቅርቡም የአማራ ብሔር ተወላጆች በሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የቤት ማቃጠልና በጎተራ ውስጥ የነበረን እህል የማንደድ ወንጀል መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዓለሙ አስፋው የተባሉ የአካባቢው የሚሊሻ አዛዥ እንደነበሩ የተነገረላቸው ግለሰብ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ባሰሙት ንግግር፣ በአካባቢው ተመሳሳይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች መፈጸም የጀመሩት ቆየት ብለው ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱም አሁንም ተባብሰው መቀጠላቸውን አስታውሰዋል፡፡ ቤትና ንብረትን ከማቃጠል ባለፈ የሕይወት ማጥፋት ወንጀሎች በማናለብኝነት መፈጸማቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በ1996 ዓ.ም. መዳሉ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 52 የአማራ ብሔር ተወላጆች ቤቶች መቃጠላቸውን፣ በኖኖ ወረዳ በ2002 ዓ.ም. በ150 ቤቶች በተመሳሳይ ሁኔታ መቃጠላቸውን የገለጹት አቶ ዓለሙ፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ይህ ነው የሚባል አቋም ባለማሳየቱ በ2007 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወንጀሎች በመፈጸማቸው እነዚሁ የጥቃት ሰለባዎች ከአካባቢው በመሰደድ ጉራጌ ዞን ለመጠለል መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ዓለሙ ገለጻ የጥቃቱ ሰለባዎች በተደጋጋሚ ሕጋዊ የዜግነት ጥያቄያቸውን ለክልሉ መንግሥት ያቀረቡ መሆናቸውንና በምላሹ ምንም ዓይነት መፍትሔ አለማግኘታቸውን ገልጸው፣ ከክልሉ የፖሊስ ኮሚሽነር በስተቀር ማንም የመንግሥት አካል እንዳልጎበኛቸው ተናግረዋል፡፡ “በመከላከያ ሠራዊት አባልነት ለስምንት ዓመታት ያህል ግዳጄን የተወጣሁና የአገሬን ጥሪ ተቀብዬ ላይቤሪያ ድረስ ሰላም ያስከበርኩ ዜጋ ነኝ፡፡ ዛሬ ግን በአገሬ ውስጥ ሰላም አጥቻለሁ፣” በማለት ብሶታቸውን ያሰሙት አቶ ዓለሙ፣ በዜግነታቸው ከመኩራት ይልቅ ማፈር እንደጀመሩና ምንም ዓይነት የሰውነት ከለላ የሌላቸው ዜጋ ሆነው መቅረታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ከአፋር የመጡ አርሶ አደሮች በበኩላቸው በልማት ምክንያት የእርሻ መሬታቸው በመንግሥት እንደተነጠቀባቸውና የተከሏቸው የቴምር ዛፎችም እንደወደሙባቸው በመግለጽ፣ ምንም ዓይነት የካሳ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸውና ይህም በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ተፈጽሞ የማያውቅ ኢሰብዓዊ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከአካባቢው የመጡ አርሶ አደር በአስተርጓሚያቸው አማካይነት እንደገለጹት፣ ፍየሎቻቸውንና በጎቻቸውን ሸጠው አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ለመንግሥት አቤት ቢሉም መፍትሔ አላገኙም፡፡

የሰመጉ ምክትል የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ቁምላቸው ዳኜ እነዚህን መሰል ብሔር ተኮርና ልማትን ሽፋን ያደረጉ ኢሰብዓዊ ጥሰቶች በአገሪቱ ተባብሰው መቀጠላቸውን በመግለጽ፣ እነዚህን የጥቃት ሰለባዎች ለማግኘት የሰመጉ ባልደረቦች  በከፍተኛ ሥጋትና እንግልት ውስጥ ማለፋቸውን አስታውቀዋል፡፡ “ሰመጉ በአሁኑ ጊዜ በብቸኝነት ማለት በሚቻል ሁኔታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እየተከታተለ ለመንግሥትና ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ሒደት ውስጥ ያለና ከፍተኛ ጫናን እየተጋፈጠ ያለ ተቋም ነው፣” በማለት ድርጅቱ ምን ያህል አስቸጋሪ ጊዜ ላይ መድረሱን አቶ ቁምላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህን ጋዜጣዊ መግለጫ እንኳን በጽሕፈት ቤቱ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ለማድረግ መገደዱ ነባራዊ ሁኔታውን በግልጽ የሚያመላክት አጋጣሚ መሆኑን ይጠቁማል ብለዋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው ለምን በሌላ ሥፍራ እንዳልተሰጠ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የሰመጉ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ብዙየሁ ወንድሙ በበኩላቸው፣ ከአሥር ቀናት በፊት ለኢትዮጵያ ሆቴል ክፍያ ተፈጽሞ መርሐ ግብሩ የተያዘ ቢሆንም፣ ከጋዜጣዊ መግለጫው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሆቴሉ በስልክ የመርሐ ግብሩን መሰረዝ እንዳሳወቃቸው ገልጸዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ከተገኙ እንግዶች መካከል የቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዲሞክራሲ (ቪኢኮድ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ደርሰህ ግርማ፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት አዋጅ ከተደነገገበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች ከስመው፣ ዛሬ ሦስት ያህል ብቻ መቅረታቸውን አሁን ያለው ሁኔታ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ አመላካች መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሰመጉ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እያደረገ ባለው አገራዊ አስተዋጽኦ ሊመሰገን እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ሰመጉ በ1984 ዓ.ም. ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ 36 መደበኛ መግለጫዎችንና 139 ልዩ መግለጫዎችን ማውጣቱ የተገለጸ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ብሔር ተኮር የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዳካተቱም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡

Reporter Amharic