ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን፤ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስም በሚተላለፉ ፕሮግራሞች ላይ ጊዜያዊ እገዳ አስተላለፈ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


–    በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ መተዳደርያ ደንብ ያለው የማኅበረ ቅዱሳን ፕሮግራም ይገኝበታል

–    ጉዳዩ ለምእመናንና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ግርታና ክፍተት እንዳይፈጥር ማኔጅመንቱ ጠይቋል

 

ሕጋዊነቱና ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የኾነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (ኢ.ቢ.ኤስ) ቴሌቪዥን ሜኔጅመንት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም መንፈሳዊ ዝግጅት የሚያስተላልፉ ሦስት ፕሮግራሞችን ከመጪው እሑድ ጀምሮ ለጊዜው ከአየር ላይ ለማንሣት መወሰኑን አስታወቀ፡፡ የአየር ሰዓቱ ለሌሎች ጠያቂዎች ተሰጥቶ በቤተ ክርስቲያኒቱና በምእመናኑ ዘንድ ክፍተትና ግርታ እንዳይፈጠር በተቋማቱ ላይ ማስተካከያ ተደርጎ አገልግሎቱ በስፋት እንዲቀጥልም ጠይቋል።

የጣቢያው ማኔጅመንት፣ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት በየሳምንቱ እሑድ ለግማሽ ቀን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም መንፈሳዊ ዝግጅት ሲያቀርቡ የቆዩትን፤ የታዖሎጎስ፣ የቃለ ዓዋዲ እና የማኅበረ ቅዱሳን መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን ከኅዳር 19 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ከአየር ሰዓታቸው እንደሚያነሣ አስታውቋል።

የሁለቱን ድርጅቶችና የማኅበሩን የአየር ሰዓት ለማንሣት በጣቢያው የተላለፈው ውሳኔ፣ ያለፈቃድ እና ያለዕውቅና በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚያስተምሩ ተቋማትን ለማስቆም በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በኩል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከመረዳት፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱም ካለው አክብሮትና የመግባባት መንፈስ እንደሆነ ማኔጅመንቱ በደብዳቤው ገልጧል።

ከጣቢያው ጋር ውል በመግባት በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ሦስት መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ሲቀርቡ መቆየታቸውን ያስታወሰው ማኔጅመንቱ፣ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተጻፈለት ደብዳቤ የትኞቹን መንፈሳዊ ፕሮግራሞች የሚመለከት እንደሆነ በዝርዝር ባይጠቅስም ማኅበራቱና ተቋማቱ እንዲሁም መምህራኑ ሕጋዊ የድጋፍና የዕውቅና ሰነዶች እንዲያስገቡ እንደጠየቃቸው አውስቷል፡፡ ብዙዎቹም ከጣቢያው የአየር ሰዓት ግዥ በጠየቁበት ወቅት ያቀረቡትንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዕውቅና ያገኙባቸውን ሰነዶች አያይዘው አቅርበዋል፤ ብሏል፡፡ የሰነዶቹንም ቅጅ በአባሪነት ማያያዙን ጠቁሟል።

በቤተ ክርስቲያኒቱ ምዘናና የዕውቅና አሰጣጥ ሰነዶቹ በቂ ሆነው ካልተገኙ፣ ፕሮግራሞቹ ከቴሌቪዥኑ ጋር የነበራቸውን የአየር ሰዓት ውል በማፍረስ ለሌሎች የአየር ሰዓት ጠያቂዎች ለመስጠት እንደሚገደድ አስረድቷል። ይህ ደግሞ፣ በፕሮግራሞቹ ሥር መንፈሳዊ ትምህርቶችን ለሚከታተሉ ምእመናንና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ግርታንና ክፍተትን እንዳይፈጥር የአየር ሰዓቱን የማንሣቱ ውሳኔ በጊዜያዊነት የተላለፈ ርምጃ እንደሆነ ገልጧል።

ቀጥተኛ ውል ከጣቢያው ጋር የሚያስሩ አካላት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ሕጋዊ ዕውቅና ሲያገኙና ይህም በሀገር ውስጥ በሚገኘው ብቸኛው ወኪሉ ኢንኮም ትሬዲንግ አማካይነት ሲረጋገጥ መሆኑን ማኔጅመንቱ ጠቅሶ፤ ቤተ ክርስቲያኒቱም የማስተካከያ፣ የእርምትና የመግባቢያ ጊዜ በማግኘት ዕውቅና በምትሰጣቸው ተቋማት አገልግሎቱን በስፋት ለመቀጠል ትችል ዘንድ ለጊዜው የተቋረጠውን የአየር ሰዓት ክፍት አድርጎ እንደሚጠብቅ አስታውቋል።

የማኔጅመንቱ የአየር ሰዓት የማንሣት ጊዜያዊ ውሳኔ ለሦስቱም ፕሮግራሞች አዘጋጆች በደብዳቤ የተገለጸ ሲሆን፤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ምላሽ ሲገኝም እንዲያውቁት እንደሚደረግ ተጠቅሷል፤ አዘጋጆቹም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር በመግባባት የበኩላቸውን መፍትሔ እንዲያገኙ አሳስቧል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም ባካሔደው የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባው፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ሽፋን እያደረጉ የሚዘጋጁ የዝማሬና መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና ሥርዓቷንም ጭምር የሚያዛቡ መልእክቶችን እያስተላለፉ በመሆናቸው በርካታ ተከታዮቿን እያደናገሩ እንደሚገኙ በመጥቀስ ሕገወጥ ተግባራቸው ወደፊት እንዳይቀጥል ኢ.ቢ.ኤስን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ እንዲገለጽ፤ በጠቅላይ ቤተክህነቱ የሕግ አገልግሎቱ በኩልም የሕግ ክትትል እንዲደረግባቸው መወሰኑ ይታወሳል።

በምልዓተ ጉባኤው ስብሰባ ወቅት በስም መጠቀሳቸው ከተጠቆሙት ፕሮግራሞች መካከል፣ ታዖሎጎስ እና ቃለ ዓዋዲ የሚወክሉትን የሃይማኖት ተቋም በተመለከተ ለጣቢያው ያቀረቧቸው ሰነዶች፤ አዘጋጆቹ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ኮሌጆች ያገኟቸውን የዲፕሎማና የዲግሪ ምስክር ወረቀቶች እንዲሁም የድጋፍ ደብዳቤ እንደነበር ተገልጧል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ ዘዴዎች/በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በበራሪ ጽሑፎች፣ በካሴት፣ በኤሌክትሮኒክስ መገናኛዎችና በመሳሰሉት እንዲያስፋፋ እንደተፈቀደለት በመጥቀስ ለሦስተኛ ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ የተሰጠውን መተዳደርያ ደንብ እና ሕጋዊ የኅትመት ውጤቶቹን አያይዞ ማቅረቡ ታውቋል።¾