የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው ወጣቱ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከፓርቲው ጋር መለያየቱን አስታወቀ፡፡
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ማክሰኞ ኅዳር 14 ቀን 2008 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ በፌስቡክ ገጹ ከፓርቲው ጋር መለያየቱን፣ ከአሁን በኋላ የሚወክለው የፖለቲካ ድርጅት እንደሌለና የሚወክለው ራሱን ብቻ እንደሚሆን ገልጿል፡፡
‹‹ከአሁን በኋላ ማንኛውንም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ቡድን የማልወክል እንደሆነ አሳውቃለሁ፡፡ የእኔ ውክልና ለራሴ ብቻ ነው፤›› ይላል በአቶ ዮናታን ፌስቡክ ገጽ ላይ የሠፈረው ማሳሰቢያ፡፡
እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰበትን ምክንያት ያልገለጸ ሲሆን፣ ሪፖርተር ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችም ሆነ ከራሱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡
አቶ ዮናታን የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ምሩቅና የ27 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ሰማያዊ ፓርቲን ከመቀላቀሉ በፊት በመምህርነት አገልግሏል፡፡ በምርጫ 2007 ወቅት ፓርቲውን ወክሎ በአዲስ አበባ ከተማ በምርጫ ክልል 17 መወዳደሩ ይታወሳል፡፡ አቶ ዮናታን ራሱን ከፓርቲ ፖለቲካ ማግለሉን ውሳኔውን ካስታወቀ በኋላ፣ በፌስቡክ ተከታዮቹ የተሰጡት አስተያየቶች የተደበላለቁ ስሜቶችን አንፀባርቀዋል፡፡