ከ‹‹ቤዛ እንሁን!›› በወቅታዊ ሶስት ጉዳዮች ላይ የተሰጠ ማብራሪያ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
1. ይህ ስብስብ በሕግ አይን እንዴት ይታያል?
የተለያዩ ሰዎች ‹‹ይህ ጊዜያዊ ስብስብ የመንግስት እውቅናና ፈቃድ አለው ወይ?›› ሲሉ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ ይህንኑ በተመለከተ የተለያዩ የዚህ ስብስብ ዓላማ ተጋሪ የሆኑ የሕግ ባለሙያዎች እንደገለፁልንና በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፅ 862 በግልፅ እንደተመለከተው፤ የሰብአዊ እርዳታን ዓላማው አድርጎ በጊዜያዊነት የሚንቀሳቀስ ማናቸውም የበጎ አድራጎት ፍላጎት ያለው ወገን በሕግ የተቀመጠበት ክልከላ ወይም ገደብ እንደሌለ ነው፡፡
ይህንኑም ያረጋገጥ ዘንድ ሙሉ የህግ አንቀፁን እንደሚከተለው አስፍረነዋል፡፡
የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፅ 862
ያለፈቃድ ገንዘብ ስለመሰብሰብ
‹‹ማንም ሰው በሕግ ሳይፈቀድለት ወይም የክፍሉን ባለስልጣን ሳያስፈቅድ በአደባባይ እየዞረ ገንዘብ የሰበሰበ ወይም የጠየቀ እንደሆነ በገንዘብ መቀጮ ወይም በማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል፡፡
ይህ የገንዘብ መሰብሰብ ጉዳይ የተፈፀመው፤ ሃይማኖታዊ ስርዓት በሚፈፀምባቸው ሕንፃዎች ውስጥ ወይም በአንድ ስብሰባ ስፍራ ባንድ ማህበር ወይም ባንድ የግል በሆኑ የማህበር ክፍሎች፤ ይህንኑ ሙያ አድርገው በያዙ ክፍሎች፤ በስፖርትና በሌላውም ይህን በመሳሰለው ክፍል ሆኖ የገንዘቡን ስብሰባ በተለይ ለበጎ አድራጎት ወይም የዚህኑ ስራ ለማካሄጃ የሆነ እንደሆነ ይህ የተባለው የቅጣት ድንጋጌ አይፈፀምባቸውም፡፡››
በመሆኑም ከላይ ከተመለከተው የሕግ ዕይታ በመነሳት ይህ ‹‹ቤዛ እንሁን!›› የተባለው ጊዜያዊ ስብስብ ለተቋቋመለት ዋነኛ ዓላማ ማለትም፡- በድርቅ/በርሃብ ለተጎዱ ወገኖቻችን እርዳታ ለማድረግ መንቀሳቀሱ ምንም ዓይነት የሕግ ክልከላ የሌለበት ነው!
2. ይህ ስብስብ የሚሰበስበውን የገንዘብ/ቁሳቁስ እርዳታ ለማንና በምን መልኩ ያደርሳል?
እስካሁን ባደረግናቸው እንቅስቃሴዎች ከተለያዩ ዓለም-ዓቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች አበረታች አዎንታዊ ምላሽ አግኝተናል፡፡ አንዳንዶቹ እስካሁን በግለሰብ ደረጃ ተነሳሽነትን ወስደው የመጡ ስብስቦች እንዳላጋጠሟቸውና ነገር ግን አብሮ ለመስራት የማያስችሉ እንቅፋቶች እንዳልታያቸው በመግለፅ፤ አብረን ለመስራት የምንችልባቸውን አግባቦች ከየድርጅቶቹ ዋና ኃላፊዎች ጋር በመፈተሸ በቅርቡ እንደሚያሳውቁን ገልፀውልናል፡፡
ከእነዚህም መካከል አንጋፋ የሆነው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር (Ethiopian Red Cross Society) ግን ከወዲሁ ባለን ደረጃ አብሮ ለመስራት እንደሚችል አሳውቆናል፡፡ በመሆኑም ከቀይ መስቀል ጋር ስምምነት ደርሰንና እነርሱ በጥናት በለዩዋቸው አጣዳፊ እርዳታዎች ዙሪያ ተባብረን ልንሰራ እንደምንችል ተነጋግረናል፡፡ በአሳሳቢነት ከለዩዋቸው ችግሮችም ዋነኛው የእናቶችና የሕፃናት አልሚ ምግቦችን የተመለከተው ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ባለን የመረጃና የተራድኦ ድርጅት ግንኙነት በመመርኮዝ፤ አጣዳፊ የአልሚ ምግብ ለሚፈልጉ ተረጂ እናትና ሕፃናቶች ይህንኑ ከኢትዮጵያ ገበያ ላይ በመግዛት፤ ከቀይ መስቀል ጋር ያሉበት ቀበሌ ድረስ ሄደን መስጠት እንችላለን፡፡
ከቀይ መስቀል ኃላፊዎች ጋር በነበረን ገንቢ ቆይታ ይህ የድርቅ ሁኔታ ዘለግ ላለ ጊዜ ሊቆይ የሚችል እንደሆነና መፍትሔውም ለረጅም ጊዜ የሰብአዊ እርዳታ ተግባራትን ሊሰራ የሚችል ማህበር ማቋቋም እንደሆነ ተረድተናል፡፡ በመሆኑም እነርሱ ባመላከቱን አዎንታዊ ጥቆማ ላይ ተወያይተን በዘላቂነት የምንወስነውን ወደፊት እንደምናሳውቅ እንገልፃለን፡፡
3. የስራ ድርሻ ክፍፍልን በተመለከተ
ይህ ስብስብ በነበሩት የተለያዩ የውይይት ወቅቶች በጋራ ግንዛቤ በያዘበት መሰረት፤ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራው አካውንት ከመክፈት በተጨማሪ የተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስልቶችን ነድፎ የሚንቀሳቀስ ንዑስ ግብረ-ኃይል የማቋቋሙን አጣዳፊነት ተመልክቷል፡፡ ስለሆነም አንዳንድ የሚና ሽግሽጎችንና ለውጦችን አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት፡-
ሶስት ሰዎችን በአባልነት የያዘ ‹‹የገቢ አሰባሳቢ ንዑስ ግብረ-ሀይል›› በፋይናንስ ክፍል ሥር እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡ ይህ ‹‹የገቢ አሰባሳቢ ንዑስ ግብረ-ሀይልም›› አዳዲስ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝርዝር ስልቶችን ነድፎ እንዲያሳውቅና እንዲንቀሳቀስ አቅጣጫ ተሰጥቶታል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በግል ጉዳይ ምክንያት የተነሳ ሒሳብ በማንቀሳቀስ ሚና ውስጥ ልትቀጥል ባልቻለው ወ/ሪት ሜሮን አዲስ ገብረፃዲቅ ምትክ፤ አቶ ሮቤል አያሌው ሃይሌን በመተካት በአዲስ የአካውንት ቁጥር መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ የባንክ አድራሻውና አካውንት ቁጥሩም፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራዳ ጊዮርጊስ ቅርንጫፍ ሂሳብ ቁጥር፡- 1000144438907 ስዊፍት ኮድ CBETETAA መሆኑን እንገልፃለን፡፡
እስካሁን በነበረው ሂደት እጅግ ተስፋ ሰጪ የወገን አለኝታነትን የሚያሳይ መጠን ያለው ገንዘብ ተሰብስቧል፡፡ የዚህንም የመጨረሻ ይፋዊ ውጤት በጥቂት ቀናት ባላነሰ ጊዜ ውስጥ እናሳውቃለን፡፡
ምንም እንኳ ይህን በጎ ተግባር በግል ተነሳሽነት ብንጀምረውም በእኛ አቅምና ደረጃ ብቻ እንደማንወጣው የታወቀ ነው፡፡ በመሆኑም በሀገር ቤትም ሆነ በውጪ ሀገራት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለዚህ አሳሳቢ ሀገራዊ ቀውስ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ርብርብ ላይ ፈጥናችሁ የእርዳታ እጃችሁን እንድትዘረጉና ለወገናችንም በጊዜ ‹‹አለንልህ!›› እንለው ዘንድ በአፅንኦት ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
‹‹ቤዛ እንሁን!››
ለወገን!
ከሕዝብ ግንኙነት ክፍል/ አናንያ ሶሪ/
ሕዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም