ባለሥልጣኑ ለክልሎችም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት የጤና ቢሮዎች በላከው ደብዳቤ እንደገለጸው፣ ኮዴይን የተባለው መድኃኒት ለኢትዮጵያውያን የዘረ መል አወቃቀር (Genetic Makeup) የማይስማማ መሆኑንና ጥቅም ላይ ከዋለም እስከ ሞት ሊያደርስ እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ባለሥልጣኑ ዕገዳውን ያደረገው የአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች ላይ አተኩሮ ባከናወነው ጥናት፣ ኮዴይን የተባለው የሕመም ማስታገሻ እስከ ሞት የሚያደርስ መሆኑን በማሳወቁ ነው፡፡
የተሠራው ጥናት እንዳመለከተው በዘረ መል አወቃቀር ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ኮዴይን ሲወስዱ ወደ ሞርፊን እንደሚቀየር፣ በዚህም ምክንያት በደም ውስጥ የሚገኘውን የሞርፊን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ለመተንፈስ ችግር ብሎም ለሞት እንደሚያደርስ ተገልጿል፡፡
በመሆኑም ማንኛውም የጤና ባለሙያና የጤና ተቋም ኮዴይን የተባለውን የሕመም ማስታገሻ በየትኛውም ዕድሜ ለሚገኙ ታካሚዎች በሕመም ማስታገሻነት ወይም ለብርድና ለሳል ሕመሞች እንዳያዙ ደብዳቤው የደረሳቸው የጤና ቢሮዎች፣ በሥራቸው ለሚተዳደሩ የጤና አገልግሎት ተቋማት እንዲያስተላልፉ አዟል፡፡ ዕገዳው የተደረገው ላልተወሰነ ጊዜ እንደሆነ ቢገልጽም፣ ላልተወሰነ የተባለበት ጊዜ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ደብዳቤው አይገልጸም፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ቢደወልም ጥሪውን አልመለሱም፡፡ የአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ምርመራ ከተካሄደባቸው 122 ኢትዮጵያውያን መካከል 29 በመቶ የሚሆኑት ወይም 35 ኢትዮጵያውያን የዘረ መል አወቃቀር ኮዴይን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ሞርፊን የሚቀይር ኢንዛይም አላቸው፡፡
ይህ የጥናት ውጤት ከተገለጸ ስድስት ወራት ቢሆነውም የኢትዮጵያ የመድኃኒት፣ የምግብና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ውሳኔ ሳይወስድ እስከተጠቀሰው ቀን ቆይቷል፡፡ በተመሳሳይ ጥናት የአዲስ አበባ የወተት አቅርቦት ለካንሰር የሚዳርግ አፍላቶክሲን የተባለ ውህድ እንዳለው ከተገለጸ ከስድስት ወራት በኋላ መረጃው በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ሲለቀቅ፣ ባለሥልጣኑ የራሱን ተጨማሪ ጥናት እያከናወነ መሆኑን ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን መግለጹ አይዘነጋም፡፡