የአማራ ህዝብና የህወሀቱ ብዓዴን – አቻምየለህ ታምሩ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ሰሞኑን ባህር ዳር ላይ የህወህት ስኬት የሆነው የአማራ እልቂት በራሱ በአማራው እየተዘከረ ይገኛል። የአማራ ህዝብም «በግ ካራጁ ኋላ እንደሚጎተት» እየተጎተተ ሞቱን እያነገሰ ገዳዮቹን አበጃችሁ እያለ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ይህንን እንድል ያስደፈረኝ «35ኛውን የብዓዴን ዝክረ በዓል» ለማክበር የተሰበሰበው አማራ ሁሉ በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣ በነቀምት፣ጊዳብ ሺራቦ፣ በአሰቦት፣በባሌ፣ አርሴ ፣ በቦረና፣ በጅማ፣ በኢሉባቦር፣በወተር፣ በቤንሻንጉል፣ በጉራ ፈርዳ፣ በወልቃይት፣ ወዘተ የተካሄደውን የአማሮች ጭፍጨፋና የብዓዴንን ግብረ መልስ የማያውቅ የኔዘመን ትውልድ ስለሌለ ነው።

ይህንን አስመልክቶ ከሶስት ሳምንት በፊት « ብዓዴን የህወሀት ነውረኛ ቡድን እንጂ የአማራ ህዝብ አካል አይደለም» በሚል ርዕስ የጻፍሁትን ጽሁፍ እዚሁ ፌስቡክ ገጼ ላይ አትሜ ነበር። የጽሁፌ አላማም «ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ» እንዲሉ የመጀመሪያውን የኢህዴን ሊቀመንበር አግኝቼ ስለድርጅቱ አፈጣጠርና አላማ ዛሬ በጸጸት አለንጋ እየተገረፈ ያጫወተኝን እውነት ለዘመን ተጋሪዎቼ ለማካፈል ነበር። የሆነው ሆኖ የአማራው እልቂት በራሱ በአማራው ገንዘብ አገር አቀፍ ድግስ ተዘጋጅቶ ባህር ዳር ላይ እየተከበረ ይገኛል። ይህ ክስተት እጀ መድሀኒቱ ሀኪም ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ስለአማራው የተናገሩት ሙሉ በሙሉ በዚህ ዘመን ትውልድም ገቢር እንደሆነ ማሳያ ነው።

ባህር ዳር ላይ እየሆነ ያለውን የአማራው ክራሞት ግን አንድ ነገር ደጋግሞ አስታወሰኝና ልከትበው ወደድሁ። የባህር ዳሩ የአማራው ሽርጉድ ታላቁ አርበኛና ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በፋሽስት ጥሊያን ወረራ የኢትዮጵያ መንግስት በፈረሰ ጊዜ ከራስ እምሩ ኃይለ ስላሴ ጋር ሆነው ስለነጻነታቸው በሚጋደሉበት በዚያ ወቅት፥ ቆመውም፥ ተቀምጠውም፥ ተኝተውም፥ የሚያቃጥላቸው ያገር ፍቅር እየቀቀላቸው፤ እንፋሎታቸው እየገነፈለ፤ አይናቸው እንባ እየሞላ ስላስቸገራቸው በናታቸው ስም «የኢትዮጵያ ስቅሶ» ብለው ሀዘናቸውን ለወንድሞቻቸው ለማካፋል ሲሉ በንባቸው የጻፉትን ግጥም ያስታውሰኛል።

የአማራው ህዝብ ከአራጁ ከወያኔ ኋላ እየተጎተተ ራሱ እንዲጠፋ የሞት አዋጅ የታወጀበትን፤ እንዲታረድ ካራው የተሳለበንት ቀን ለማክበር እንዲህ ሲያጀረጅር ከማየት በላይ ውርደትና ክሽፈት የለም።

የአርበኛ የሀዲስ ግጥም ምንም እንኳ በዚያ ዘመን የተቋጠረ ቢሆንም ዛሬም ባህር ዳር ላይ የህወሀቱን ብዓዴን ልደት ለማክበር ለተሰበሰበው ሆዳም አማራ ሁሉ ገላጭና ከመጠነኛ ማሻሻያ ጋር እነሆ፤

የኢትዮጵያ ልቅሶ
ልጆቼን በማመን ባለመጠራጠር፣
የሚደፍረኝ የለም፣ ብዬ እመካ ነበር፤
ግን አሁን ተደፈርሁ ላልቅስ ፣ እርሜን ላውጣ፣
ጀግኖች ያለቁብኝ ፣ ስለሆንሁ አይቶ አጣ፤
አድምጡኝ ልጆቼ ፣ ላስጠንቅቃችሁ፣
ሳምናችሁ ብትከዱኝ ፣ ስመካበችሁ ፣
ዘላለም ውርደት ነው ፣ ደመወዛችሁ።
አየ ዋዬ ፣ ልጆቼ አየ ዋዬ ፣ ከዳችሁኝ ወዬ ።

ጀግና አልተተካም ወይ ፣ በቴዎድሮስ ስፍራ፣
ጎበዝ አልቆመም ወይ ፣ በዮሃንስ ስፍራ፣
ሰው የለበትም ወይ ፣ በምኒሊክ ስፍራ፣
ጠላቴ ሲወርረኝ ፣ ከቀኝ ከግራ፣
የሚሰማኝ ያጣሁ ፣ ብጣራ ብጣራ፤
ወይ እኔ ኢትዮጵያ የጀግኖች እናት፣
ሁሉም አለቁና ፣ ትተው ባዶ ቤት፣
ደርሶብኝ የማያውቅ ፣ አገኘኝ ጥቃት።
አየ ዋዬ ፣ ልጆቼ አየ ዋዬ፣ ከዳችሁኝ ወዬ ።

ገንዘብ እዬዘራ ሲመጣ ጠላት፣
ከማታለል ጋራ ፣ ከውሸት ስብከት፣
ባጠመደው ወጥመድ ፣ እንድትገቡለት፣
ተንኮሉን ሳታውቁ ፣ መስሎዋችሁ እውነት፣
በግ ካራጁ ሁዋላ ፣ እንደሚጎተት፣
ትጎተታላችሁ፣ እናንተም ለሞት።
አየ ዋዬ ፣ ልጆቼ አየ ዋዬ ፣ ከዳችሁኝ ወዬ።

ገንዘብ ተበድሮ አሁን ሲሰጣችሁ፣
ሁልጊዜም እንደዚያው ፣ የሚያደርግ መስሎዋችሁ፣
እንዳትታለሉ ፣ ሁዋላ ወየላችሁ፤
አሁን ገንዘብ ሰጥቶ ፣ እንዳትታገሉት ካረገ በሁዋላ፣
እንኩዋንስ የራሱ ፣ ገንዘቡን ሲበላ ፣
የናንትም ይሄዳል ይሰጣል ለሌላ።
አየ ዋዬ ፣ ልጆቼ አየ ዋዬ ፣ ከዳችሁኝ ወየ ።

አሁን ቢሰጣችሁ ገንዘብ ተበድሮ ፣
በጁ ስትገቡለት ፣ እንዲህ ጥሮ ግሮ ፣
ከያዘ በሁዋላ ክንዱን አጠንክሮ ፣
ያጠፋውን ገንዘብ ፣ አንድ ባንድ ቆጥሮ፣
ይቀበላችሁዋል ፣ ወለዱን ጨምሮ ።
አየ ዋየ ፣ ልጆቼ አየ ዋዬ፣ ከዳችሁኝ ወይ።

አይ ሞኞች ልጆቼ ፣ ተላላዎች ሆይ ፣
ድርጅት ያቆመ በህዝባችሁ ላይ፣
እናንተን ለማክበር ፣ መሰላችሁ ወይ?
አሁን ስነግራችሁ ፣ ቢመስላችሁ ዋዛ፣
በሁዋላ መከራው ስቃዩ ሲበዛ ፣
ሞትን ብትፈልጉት ፣ በወርቅ አይገዛ፤
አየ ዋዬ ፣ ልጆቼ አየ ዋዬ ፣ ከዳችሁኝ ወየ ።

ፀፀቱ ይውጣልኝ እስቲ ልንገራችሁ፣
ምናልባት ብትሰሙኝ ፣ ትንሽ ቢቆጫችሁ፣
ጠመንጃው ጥይቱ ፣ እያለ በጃችሁ ፣
ዱሩ ሸንተረሩ ሳለ በጃችሁ ፣
አሁን ጊዜው ሳያልፍ ፣ካልተጋደላችሁ፤
ይህን ሁሉ በጁ ፣ ካረገ በሁዋላ ፣ አጥቂው ጠላታችሁ፣
ቢጭኑት አጋስስ ፣ ቢያርዱት ሰንጋ ናችሁ ።
አየ ዋዬ ፣ ልጆቼ አየ ዋዬ ፣ ከዳችሁኝ ወየ ።

ከዚህ ወድያ በቃኝ ፣ መክሬያችሁዋለሁ ፣
ለኔም ለናንተም ሞት ፣ እርሜን እውጥቻለሁ፤
መክሬያችሁዋለሁ ፣ ጠላትን በህብረት እንድትቃወሙ፣
አሁን ይህን ጊዜ ፣ በጣም ሳትደክሙ፣
የናትነት ምክሬን ፣ ቃሌን ብትፈፅሙ፣
እግዜር ይባርካችሁ ፣ አብቡ ለምልሙ፣
ግን ይህን ጨኸቴን ፣ ልቅሶየን ባትሰሙ፣
በመልእልተ መስቀል ፣ የፈሰሰው ደሙ ፣
ርጉም ያድርጋችሁ ፣ እስከ ዘላለሙ ።
አየ ዋዬ ፣ ልጆቼ አየ ዋዬ ፣ ከዳችሁኝ ወዬ።