‹‹ ፀሀዩ መንግስታችን ›› እና እኛ Girma Bekele


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ከዲሞክራሲያዊነት ወደ ‹‹ ልማታዊ ነት›› የተሸጋገረው ድርቅን ወደ ድርቅና ያሸጋገረው መንግስታችንን ስንዳስስ፤
1.ዲሞክራሲያዊ መንግስት –ለዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብቶች ቅድሚያ የሚሰጥና የአስተዳደሩ ፖሊሲ ትኩረት ያደረገ፤
2.ልማታዊ መንግስት– ከዲሞክራሲ ይልቅ ልማትን በማስቀደምና የፖሊሲው ትኩረት በማድረግ የሚመራ መንግስት፤
3.ድርቅ — የውኃ/እርጥበት እጥረት፣
4.ድርቅና— የይሉኝታ /እውነትንና በተጨባጭ የሚታየውን የመቀበል እጥረት፣
5.መንግስታችን ድርቅና የተላበሰ ድርቅን የሚክድ ህዝቡን የሚያስርብ፣
6. እኛ- በረሃብ አለንጋ እየተገረፍን ከዲሞክራሲውም ከልማቱም ሳናይ ከልማቱ ባለ 25 ሚ ብር ቤት ነዋሪዎችን ከዲሞክራሲው ሙሰኞች በአጭር ጊዜ ያካበቱትን ሃብት እያየንና እያደነቅን እንድንኖር የተፈረደብን ፤ይህን ውርደትና ሞት ለመሸከም ደንዳና ጫንቃና ኅሊና የታደልን ጨዋና ሰላም ወዳዶች፤
7.በምግብ ራስን መቻል/Food Self-sufficiency/–በአገር ውስጥ የግብርና/የምግብ ምርት የዜጎችን የምግብ ፍላጎት ማሟላት፤
8. የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ / Food security/— በአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ በሚገዛ ምግብ የዜጎችን የምግብ ፍላጎት በማሟላት የረሃብ ስጋትን ማስወገድ፤
9.ማንኛውም ዓይነት (ልማታዊም ሆነ ዲሞክራሲያዊ፣ …) መንግስት ቢቻል በራሱ አገር ምርት ባይቻልም ከውጪ አገር በቂ ምግብ በመግዛት ለዜጎቹ በቂና ተመጣጣኝ ምግብ ማቅረብ የመጀመሪያና ቀዳሚ ተግባርና ግዴታው ነው፡፡
‹‹ፀሃዩ መንግስታችን›› እንዴት ድርቅን ወደ ድርቅና እንዳሸጋገረ፡-
• ከ77ድርቅ ጋር የሚያወዳድር — ከጨፍጫፊ ጦረኛ፣ ኢዲሞክራሲያዊ፣…. መንግስት ጋር የዛሬውን የትናንት (77) ዲሞክራሲያዊ የዛሬ ልማታዊ (10 ዓመታት ባለሁለት ዲጂት ያደገ) ጋር የሚያወዳድር፣
• ድርቅ አለ – ረሃብ የለም ፤ ረሃብ አለ – ሞት የለም/ሰው አልገደለም፤በሚል የቃላት ተጫዋች፣
• በቁጥር የሚከራከር፣ ልጄ ሞተብኝ የምትል እናት ጋር ግብግብ የሚገጥም፤
• እየሞተ/እየተራበ ላለው ህዝብ እየራበህ አይደለም ልጅህ አልሞተብህም የሚል በቃላት የሚጫወት ፣ በተራበው ቁጥር የሚከራከር 8.4 ሚሊዮን ህዝብ ብዙ አይደለም ፣… የሚል መንግስት ፤
• በጣሳ ሰፍሮ እየሰጠ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአንድ ሰው የሚያስፈልገውን ካሎሪ መጥኜ እየሰጠሁ ነው የሚል መንግስት፤
• ትናንት በምግብ ራሳችንን ችለናል ያለ መንግስት፤ ዛሬ ምግብ ጅቡቲ ወደብ ደርሷል ማለቱ፤
• ትናንት ‹‹ልማታችን›› ያለማንም ድጋፍ ድርቁ ወደ ረሃብ እንዳይሸጋገር የሚያስችል አቅም ፈጥሮልናል፣ዛሬ ዓለምን የጠየቅነው ድጋፍ በፈለግነው መጠንና ጊዜ እየደረሰን አይደለም፤
እነዚህን ለአብነት ጠቅሰን ‹‹ ፀሃዩ መንግስታችን ››ድርቁን ወደ ድርቅና በማሸጋገሩ ላይ አስምረን ወደ ቀጣዩ እንሸጋገር፡፡
የእኛ የዛሬ ኑሮ አንድ በራሺያ ሶሻሊዝም ወቅት የተነገረ ቀልድ አስታወሰኝ ፡፡
ካድሬው ህዝብ ሰብስቦ ‹‹ ነገ ጠዋት በቀዩ አደባባይ ስለምትሰቀሉ በ3፡00 ሰዓት በቦታው እንድትገኙ፣ ያረፈደ ይቀጣል›› ብሎ እንዳበቃ አንድ ሰው እጁን አንስቶ ጥያቄ አለኝ ሲል ህዝቡ ሁሉ ወደ ሰውዬው ዞሮ ምን ሊል ነው፣ አለቀለት …እያለ ሲያስብ ካድረው እሺ ጥያቄህ ምንድንነው ስለው ሰውዬው ‹‹ ገመድ ከማን ነው፣ እኛ ይዘን ነው የምንመጣው ወይስ አዘጋጅታችኋል?›› አለ ይባላል፡፡
እንግዲህ እኔም ከርዕሱ ‹‹ፀሃዩ መንግስታችን›› በሚል የጀመርኩት ይህን ተረት በማስታወስ መሆኑ ይመዝገብልኝ፡፡ለምን ቢባል አሁን ደውለው ‹‹ ነገ እዚህ ቢሮ በዚህ ሰዓት እንድትገኝ ብባል ‹‹ቀድሜ ምን ለማለት ተለማምጄ ልምጣ ፣ተለማምዶ መምጣት ያስቀጣል ?›› ብዬ እንድጠይቅ ‹‹በበሽታ›› በሞተው እናት በብርቱካን በኩል የተላከው መልዕክት ያስተምራልና ነው፡፡
እውነቱ ግን ልማታዊ መንግስታችን በግብርና -መር ፖሊሲው ለአስር ዓመት በተከታታይ በሁለት ድጂት ያስመዘገበው ውጤት በምግብ ራሳችንን ማስቻልም ሆነ ለዜጎቹ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አላስቻለውም፣ የልመና አቁማዳ ይዞ ከመዞር አላዳነውም፡፡
እንዲያው የእኛ ነገር ‹‹የአንበሣውና የአበዳሪው ›› ጉዳይ ሆኖ እንጂ የሚጠየቅ መንግስትና የሚጠይቅ ህዝብ ቢኖረን ስንትና ስንት ዓይነትና ብዛት ያለው ጥያቄ እናቀርብ ነበር፡፡ ዳሩ ‹‹አንበሳ ምን ይበላል -ተበድሮ፣ ምን ይከፍላል -ማን ጠይቆ ›› እንዲሉ ነው፡፡ መጠየቅም ከተቻለ የቪኦኤው ግርማይ ገብሩ ከትግራይ አፋርና አማራ ክልል ተገኝቶ የሚያቀርበው ዓይነት እንጂ የቢቢሲ ዓይነቶቹማ ኒዮሊቤራል ናቸው፣ እኛም ተመሳሳይ ጥያቄ ብናቀርብ የነርሱ ተላላኪ እንሆናለንና አንበሳው ‹‹አርጅቶና ጃጅቶ›› የራሱን ሞት እስከሚሞት ጥያቄኣችንን ይዘን በሰላም መቆየት ይኖርብን እንደሆነ ወይም ሌላ መፍትሄ እናበጅ ከሆነ በጊዜ ውስጥ እናያለን፡፡ግን ለነዚህ ሰዎች ማን ይሆን ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ‹‹የመርሳት በሽታ›› ተጠናውቷቸዋል ያላቸው ? ለምን ቢሉ ቢያንስ ሲዋሹን እንኳ ተነጋግረውና ተስማምተው አይዋሹንም ብለን መጠየቅ እነርሱን አይመለከትምና ለዚህች እንኳ ድፍረቱ አለኝና፣ ማን ነው የመረመረላቸው ሃኪም ? መቼም ከዚህ ሌላ ‹‹ንቀውናል፣ተንቀናል›› ማለት በፀረ ሽብር ህጉ ያስጠይቃልና ቢያንስ እኔ እንድለው አትጠብቁም፡፡
የመጨረሻው እውነት ግን ተበዳሪ አንበሳ በጉልበቱ ተማምኖ፣ አምባገነን እንበለው ‹‹ልማታዊ›› መንግስትም ህዝብን አፍኖ ከሞት የሚተርፈርበትና የተረፈበት መረጃና ማስረጃ በታሪክ እስከዛሬ አልተመዘገበም፣ የተፈጥሮ ህግም አይፈቅድም ፡፡ ግን ዕድሜውን ተበዳሪው ወይም ተገዢው ህዝብ ሊያሳጥርም ሊያረዝምም የመቻሉ ጉዳይ በጉልህ በቅርብና በሩቅ ታሪክና ተሞክሮ ተመዝግቧል፣ በተጨባጭ ታይቷል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ በቸር ያገናኘን//