ከዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የኢትዮጵያውያን የጋራ ግብረ ሃይል የተሰጠ የአቋም መግለጫ የተሰጠ የአቋም መግለጫ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ጥቅምት ፳፮ ፳፻፰

ከዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የኢትዮጵያውያን የጋራ ግብረ ሃይል                                                                                       
ለሚመለከተው ሁሉ
ድምጽ አልባ ለሆነው ህዝባችን፣ ነጻነቱን ለተገፈፈ ወገናችን በምርኮ ለተቀየረ በቅኝ ለተቀፈደደች አገራችን ልንቆምላት ታሪክ ግድ ስላለን ነው ለጋራ ዓላማ በጋራ የተዋቀርነው። የድልም አብነቱ ህብረቱ ነውና፤ ለዚህ ነው ከተለያየ የፖለቲካ እና የሲቪክ ማህበራት ልዩነትን ወደ ጎን ብለን ግብረ ሃይል የሆንነው። ለነጻነት ትግል መስፈርት የሆነን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ነው። የተለያየ ሀይማኖት ስላለን አብሮነታችንን ህብር አደረገው እንጂ አልለያየንም። አፅመ ርስታችን ኢትዮጵያን ስለምንወዳት አጥፊዋን ወያኔን ክፉኛ የተፀየፍነው፤ ተፀይፈን ብቻ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ሳይሆን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ የተቃወምነው የምንቃወመውም!!!
ለግል ህሊና ወይም ትውውቅ መደለያነት ስንል እውነት ብለን ያመነውን ከማስተጋባት ወደ ኋላም አንልም፤ የአቋማችን ጭብጥ በጥቅሉ ለመንደርደሪያነት ከገለፅን በኋላ በግብረ ሃይሉ ውስጥ ከተሰባሰብነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ተከታይ አባላቶች ኢትዮጵያን ለማቆየት ታሪኳ ሳይደለዝ ጥንታዊ ሀይማኖቶቿ ተከብረው አንድነቷ ጠንክሮ ትቆይ ዘንድ የትግላችን አካል ናቸውና፤ ያለፉትን ሁለት ወራት ህሊናችንን ያስጨነቀው በከተማችን ባለችው የደብረ ሰላም ቅድስት ማሪያም ቤተ ክርስቲያን የፈነዳው ድብቅ ሆነ እምቅ ስሜት ከየት ተነስቶ ወዴት ይደርስ ይሆን የሚለው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ሁኔታውንም ለመከታተል፣ እውነትንም ለማወቅ አውቀንም ለመፍትሄው አካል ለመሆንም ሆነ አቋም ለመያዝ ሙሉ መብት ያለን ኢትዮጵያዊ የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታዮች ስለሆን በደብረ ሰላም ቅድስት ማሪያም ቤተ ክርስቲያን የተካሄደው እና እየተካሄደ ያለው ሁናቴ የጋራ ግንዛቤ አስጨብጦናል፤ ስለሆነም ከወያኔም ሸፍጥ ሌላ በልዩ ሁኔታ የምንጠላው አካል በቤተ ክርስትያኗ ውስጥ የለንም፤ ይህንንም ስንል በበኩላችን እውነታውን ለመፈለግ ባለ አደራ ቦርዱንም ሆነ የተቆሮቋሪ ኮሚቴ አባላትን በአካል አግኝተን በማነጋገር እንዲሁም ለአምስት ተከታታይ ሳምንታት በቴሌኮንፍረንስ ተወካዮቹን በመጋበዝ ከምእመናኑ ጋር ለረጅም ሰአታት በመወያየት በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያኗም በአካል በመገኘት በአይናችን ያየነውን በማስረጃነት ያነበብነው ዋቢ አድርገን ነው ከዚህ በታች ያለውን የምንለው።
በቤተ ክርስትያኗ ውስጥ ያየነው መረን የለቀቀ አሠራር የወለደው ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ ቤተ ክርስትያኗን ወደ መዘጋት እየተጓዘች እንደሆነ የተረዳነው። የኛ አቋም ይህ ለአምልኮተ እግዚአብሄር ሲባል በህዝባችን የተገነባች እድሜ ጠገብ ቤተ ክርስቲያን ዳግም መዘጋት የለባትም የሚል ጽኑ ፍላጎት ያለን።
ወደ መፍትሄ ሀሳብ ከመሄዳችን በፊት ከዚህ በታች የምንገልጸው ችግር ብለን የተመለከትነውን ነው፦
ሀ)ከፈጣሪ በታች የቤተ ክርስቲያኗ ባለቤት ህጋዊ አባላት መሆናቸውንና ሿሚ ሻሪዎቹም እነዚሁ አባላቶች ብቻ መሆናቸውን አለመገንዘብ።
ለ)ባለፈው ወር የታወጀው ሹም ሽር ፍፁም የህዝብን የማሰብ ችሎታ የናቀ የቤተ ክርስቲያኗን ህግ የነቀነቀ ለቀጣዩ ትውልድም መጥፎ አርአያ የሆነ፣ በአውደ ምህረቱም ላይ የታየው እና የሚታየው ስሜትን ያልገራ አካሄድ መሆኑን።
ሐ)በግራ በቀኙ ጎራ የተሰለፉ ሃላፊነት ያለባቸው ክፍሎች ችግርን በሰለጠነ ውይይት የመፍታት ክህሎታቸውን የተፈታተነ ሁኔታ በመከሰቱ፦
መ)በተከፈተው ቀዳዳ ፀረ ህዝብና ፀረ አንድነት የሆነው ወያኔ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን መስሎ ሰተት ብሎ እንዲገባ ያመቻቸ ሁኔታ መፈጠሩ።
ሠ)በኋላም ለሁለት ሳምንት በተገኘ የግለሰቦች ያሸናፊነት ሰላም በፈጠረው አጉራ ስሜት እንደ አሁኑ ሰላም አልተገኘም በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መጓዝ ዋጋቢስነቱ በመታየቱ።
ረ)በዋናነት ፈሪሃ እግዚአብሄር የሆነው ምእመናን ለሀይማኖቱ ቀናኢ ስለሆነ እምነቱን እንደ መያዣ በመያዝ በተፈጠረው ሁናቴ በገዛ ቤተ ክርስቲያኑ ሃዘንተኛ መደረጉ ሳያንስ በሀሰት ቅስቀሳ እልል በል፣ አጨብጭብ እየተባለ ነገ እውነቱ ሲወጣ የሚደርስበትን ህሊናዊ ቁስል ሊገናዘብ አለመቻሉ ክፉኛ አሳዝኖናል።
ሰ)በተለይ አወቁ በቁ የተባሉ የተማሩትን ትምህርት ያካበቱትን እድሜ ያካበቱትን እውቀት ሁከት ማራገቢያ ማድረጋቸው በኦርቶዶክስ እምነት ላይ ጥቁር ነጥብ ማስጣሉ፤
ሸ)  በመጨረሻም የዚህ ሁሉ ችግር አባላት ተስማምተው ያወጡት ለ ፳፯ አመታት የተመራበትን መሰረታዊ ህግ ተግባራዊ አለማደረግ፤ ህጉንም አለማክበር የፈጠረው ክስተት ዛሬ ምእመኑን ከመከፋፈል አልፎ ነገ ከሚከሰተው ከንብረት አልፎ በሰው ላይ እስከ ደም መፋሰስ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ቤተክርስቲያኗን የመዘጋት የመሳሰሉ አደጋ እንዲዣበብባት አድርጓል።
ለዚህም ዋቢ የሚሆነው መብታችን ይከበር ብለው በሚጮሁት አባላት እና ወያኔ ከነመርዟ የበለጠ እንዳትገባ ችግሩ ወደ ጠረጴዛ ውይይት ይሂድ ከማለት ውጭ ሌላ አቋም የሌለውን የዋሽንግተን ዲሲ የጋራ ግብረ ሃይልን ለማጥቃት “በዚህ በምንኖርበት ሀገር ጉልበት መፍትሄ እንደማይሆን እየታወቀ አግአዚን መሰል” የሰላም እና የጸጥታ የወጣቶች ሃይል የሚል እስከማቋቋም መደረሱን እየሰማን እንገኛለን፤ እነዚህና የመሳሰሉ ግንዛቤዎች ሲኖረን በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ የተዘረዘሩት ችግርች እንዲፈጠሩ የባለ አደራ ቦርዱ የአሰራር ድክመት አስተዋጽኦ አለው የሚል እምነት አለን።
ታዲያ ምን መፍትሄ አለው ለሚለው የብዙሀን ጥያቄ፦ ችግሩ በአሜሪካ ህግ ፊት ቀርቧልና የሀገሪቷ ህግ መፍትሄ እስኪሰጥ ወይም ዘላቂ የሽምግልና መፍትሄ እስኪያገኝ የሚፈጀው ግዜ በውል ስለማይታወቅ፤ እኛም ከላይ የጠቀስናቸው የሚታዩ ችግሮች ቤተ ክርስቲያኗን በአጭር ግዜ ውስጥ ሊያዘጋት ስለሚችል ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስ በግዚያዊነት ቤተ ክርስትያኗ ለምእመናን ክፍት እንድትሆን እና አገልግሎቷ እንዳይቃረጥ ከሁለቱም በኩል እኩል ቁጥር ያለው እንዲሁም ሁለቱም ወገኖች የሚስማሙባቸው ገለልተኛ ግለሰቦችን በእኩል ቁጥር ጨምረው ቤተ ክርስትያኗ ዘላቂ መፍትሄ እስክታገኝ ድረስ ቤተክርስቲያኗን በገለልተኝነት ያስተዳድሯት ዘንድ እንደ መፍትሄ ስናቀርብ እኛም እንደማንኛውም ምእመን ቤተ ክርስትያኗ ለአንድም ሰንበት እንኳን ቢሆን እንዳትዘጋ ካለን ቁርጥ ፍላጎት በመነሳት ሲሆን ለዚህም ተፈጻሚነት ሁሉንም ወገኖች በእመቤታችን ስም እንጠይቃለን። ይህም የመፍትሄ ሀሳብ እውን እንዲሆን በኛ በኩል ከምኞት አልፎ ትብብር ባስፈለገበት ሁሉ እንገኛለን።
ነገር ግን ይሄንን የመፍትሄ አማራጭ በእንቢተኝነት ባለመቀበል ቤተ ክርስትያኗ የመዘጋት አደጋ ቢያገጥማት እንቢተኛው ወገን ሙሉ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ እና በታሪክም ዘንድ ተጠያቂ እንደሚሆን እናስገነዝባለን።
በማጠቃለያም በዲሲ ያለን የጋራ ግብረ ሃይል አባላት ከሌሎች አገር ወዳዶች ጋር በመሆን ያለንበትን ሀገር ህግ በማክበር ህሊናችን ያመነበትን እውነት ባደባባይ ለመመስከር የምናስፈቅደው አካል ወይም የምንፈራው ሃይል እንደሌለ ከዚህ በፊት ያሳየነው ተግባር ይገልጻል፤ የአቋማችንንም ገለጣ ስንደመድም ስለ ሰላም፣ ስለ እርቅ በመዘመር ነው፤ ታዲያ ግብዝ ጉልበትን መከታ አድርጎ በትእቢት ታጅሎ ስለ ሰላም ቢያወሩ እኔ የመረጥኩልህን እሬት ተጋት ቢሉት በሮ በሮ ሜዳቆ ዘላ ምድር እንዳይሆን ፣ ሆድንም በጎመን ቢደልሉ ጉልበት በዳገት ይለግማልና ስለሚሆን ከአጉል ስሜት ተገርተን የዛሬውን ሳይሆን የነገውን አሻቅበን በመመልከት ለግል ስሜት ሳይሆን የሺ ዘመናት እድሜ ያላትን ጥንታዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በማየት ገፋ ሲልም ለወያኔን እኩይ አካሄድ በር ሳይከፍት ቤተ ክርስቲያናችንን እንድናፀና ከፈለግን ነገ ሳይሆን ዛሬ ዛሬ ሳይሆን አሁኑኑ ወደ መፍትሄው እንሂድ እንላለን።
ከግል ክብርና ጥቅም በፊት የሀይማኖታችን ክብር እና የቤተ ክርስትያኗ ደህንነት ይጠበቅ!!!

ከዋሽንግተን ዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል የእምነቱ ተከታዮች    [email protected]