ከአምባገነንነት ግርጃ በቀር ይህ ምን ሊባል ይችላል?
የ
መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ።
እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
Girma Bekele – የዛሬ መሪዎቻችን ማለትም የፖለቲካው ሞተር አንቀሳቃሾች ፣የፖለቲካ መኪናው መሪ ዘዋሪዎች ከ30 ዓመታት በፊት የነበረው ረሃብ (እንደዛሬው ከድርቅ የመጣው) ያስከተለውን የዜጎች ዕልቂት ለፖለቲካ ሥልጣን መወጣጫ መሰላል ማለትም- ለረሃቡ የመጣውን ዕርዳታ ለአቅም ግንባታ (መሳሪያ መግዢያና ሠራዊት መመልመያ)፣ ረሃቡን በ‹‹ገዢው መደብ›› የመጣ አድርገው ለፕሮፖጋንዳ መጠቀማቸውን ከእነርሱ በላይ ማን ሊያስታውስ ይጠበቃል?
የሚያስታውሱት ከሆነስ ከየካቲት እስከዛሬ ድረስ ድርቁ ወደ ረሃብ እንዳይሸጋገር በራሳችን አቅም (ያለውጪ ዕርዳታና እገዛ) ገትረን ይዘነዋል፤ ይህም እንደ አገር በምግብ ራሳችንን መቻላችንን ያረጋግጣል፣ ለድርቁም መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ በመከላከሉ አንድም ሰው በረሃብ መሞት ቀርቶ አንድም ህጻን ወደ መመገቢያ ካምፕ አልገባም፣ የረሃቡን መጠን የሚያጋንኑት ጽንፈኞች ናቸው … ፣ በማለት ለእኛና ለዓለም ህዝብ የፕሮፖጋንዳ ምላሽ በማዋል ጊዜ ለማይሠጠው ዜጎችን እንደ ቅጠል እያረገፈ ላለው ረሃብ ምላሽ የሰጡና ይህን በመሸፈን ተከትሎ የሚመጣውን አደጋ የሚያልፉ ይመስላቸዋል…. ? ይህ የአምባገነንነት ዓይን የመጋረድ፣ አዕምሮ የመድፈን …የማይፈወስ ደዌ በሚል ካልተገለጸ በሌላ በምን ሊገለጽ እንደሚችል የሥነ ልቡና፣ የሥነ ህዝብ ፣የማህበረሰብ ግንኙነት ወይም ተያያዥ ሳይንስ ባለሙያዎች ብትገልጹልን አርፈን እንቀመጥ ነበር፡፡
እስከዚያው ግን በእኛ እምነት ይህን ዓይነቱን ግርጃ ከአምባገነንነት በቀር በሌላ ምንም ሊከሰት አይችልም፡፡ የአምባገነኖች መጨረሻ ደግሞ ምን እንደሆነ ከዓለም፣ ከጎረቤቶቻችንና ከራሳችንም በቅርብ የተመለከትነው ፣ከታሪክ መዛግብት የተረዳነው ነውና የቤት ሥራችን አይቀሬውን ለውጥ በማፋጠን ይህ ግርዶሽ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ መቀነስ እንደሆነ ለአፍታም መዘንጋት የለብንም፡፡
ለዚህም በአንድ አገርና ወገን አድን አገራዊ አጀንዳ ተሰባስበን አቅማችንን አስተባብረን መቆም የነገ ሳይሆን የዛሬ ተግባር መሆኑን ለማስተዋል ፈቃደኝነትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት የማይታለፍ ነው፡፡ ይህ መልዕክት ስለእኛ ነው፣ እነርሱንማ ደጋግመን መከርን ፣አስጠነቀቅን፣ አልፎም ጸለይንላቸው.. ግን የአምባገነንነት ተፈጥሮ የእኛን ቀርቶ የወዳጅ ምክርን ለመስማት ፣ ከራስ ተሞክሮም ለመማር ፣ ከታሪክ ለማገናዘብ… አይፈቅድምና ከተያያዙት የጥፋት መንገድ ከመመለስ አጠናክረውት ለመቀጠል ወስነዋል፡፡ ይህ ጥሪና መልዕክት ለእኛው ነው ስንል የአገሬና የወገኖቼ ጉዳይ ያገባናል ብለን በትግል ላይ ነን ለምንል– የለውጥ ኃይሎች በአጠቃላይ ፣የፖለቲካ አመራሮች በተለይ ከራሳችን ጥቅምና ዝና ያገባናል ወደምንለው የአገራችንና ህዝባችን ጉዳይ ፊታችንን እንድናዞር የተደረገ ነው፡፡ በየወቅታዊ ጉዳይ ከመሰለብ፣ በየጥቃቅኑ ጉዳይ ከመነታረክ፣ …ያለንበትን አሳሳቢና እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ተረድተን ትኩረታችንን የአገርና ህዝብ ህልውናና መድን ከመሆን የጋራ አጀንዳ ላይ ለአፍታም ያለማንሳትና ወደ ተጨባጭ ተግባር የመሸጋገር << የየዋህ ፖለቲከኛ >> ጥሪ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ በቸር ያገናኘን//