በ1977 ዓ.ም የተከሰተው አስከፊ ድርቅ የብዙዎችን ህይወት በቀጠፈበት ወሎ ቆቦ አካባቢ የቢቢሲው ጋዜጠኛ ክሊቭ ማይሬ ተገኝቶ፣ ልጇን በሞት ያጣች ብርቱካን አሊ የተባለች እናትንና የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሮ በሠራው ዘገባ፤ በድርቁ በአንድ አካባቢ ብቻ በየቀኑ ሁለት ህፃናት እየሞቱ መሆኑን ጠቁሟል – የተባበሩት መንግስታት ሪፖርትን በመጥቀስ፡፡
በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ ከ30 አመት በፊት ከተከሰተው የ1977 ድርቅ ያልተናነሰ መሆኑን ተጐጂዎቹ እንደነገሩትም ጋዜጠኛው ገልጿል፡፡ ልጇን በረሃቡ የተነሳ በሞት እንዳጣች የገለፀችው ብርቱካን አሊም ሆነች የአካባቢው ነዋሪዎች በቂ ምግብ እያገኘን አይደለም ማለታቸውን ጋዜጠኛው ነግረውኛል በማለት ዘግቧል፡፡
የክረምቱ የበልግ ዝናብ አልነበረም፤ የክረምቱ መግቢያ ላይ ያገኘነውን ትንሽ ዝናብ ተማምነው የዘሩት የማሽላ ቡቃያ፣ ዝናቡ በዚያው በመቅረቱ አይናቸው እያየ ደርቆ መጥፋቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል – ለቢቢሲ፡፡በድርቁ የተነሳ ከብቶች የሚመገቡትና የሚጠጡት ውሃ ማጣታቸውንና ችግሩ ወደተባባሰ ሁኔታ እያመራ መሆኑን ያወሳው ጋዜጠኛው፤ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ አስቸኳይ እርዳታ ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቢቢሲን ዘገባ ፍፁም የተጋነነ ነው ሲል የተቃወመ ሲሆን በየቀኑ ሁለት ህፃናት ይሞታሉ የተባለውም ከእውነት የራቀ መሆኑን ጠቁሞ፤ ድርቁ ያስከተለው ጉዳት ከ1977 ጋር መመሳሰሉም ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡
ዊሊያም ዴቪሰን የተባሉ ፀሐፊ “ዘ ጋርዲያን” ጋዜጣ ላይ ባቀረቡት ሰፊ ጽሑፍ፤ የቢቢሲ ዘገባ መጠነኛ ግነት አለበት ሲሉ የተቹ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት አደጋውን ለመቋቋም እያደረገ ያለው ጥረትም በቂ እንዳልሆነና መዘናጋት እየታየበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
“ሁለት ህፃናት እየሞቱ ነው የሚለው ዘገባ መረጃን መሠረት ያደረገ አይደለም፤ ጉዳቱም ከ1977 ጋር የተመሳሰለበት መንገድ ትክክል አይደለም” ብለዋል ፀሐፊው፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት ድርቁን በራሱ አቅም ብቻ መቋቋም እንደሚችል አድርጐ ማቅረቡ አለማቀፍ ማህበረሰቡ ችግሩን በአፋጣኝ ተረድቶ ልገሣ እንዳያደርግ የሚያዘናጋ ነው ብሏል፡፡ “መንግስት ምንም እንኳ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ለውጥ ያመጣ ቢሆንም እስከ 15 ሚሊዮን ህዝብ ይጐዳል የተባለውን የድርቅ አደጋ በራሱ አቅም መወጣት አይችልም” ያለው ፀሐፊው፤ መንግሥት አስቸኳይ እርዳታ ሊጠይቅ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
“ኢትዮጵያ በየ10 ዓመቱ በአስከፊ ድርቅ ትመታለች” በሚል ርእስ ሰፊ ዘገባ ያጠናቀረው አልጀዚራ በበኩሉ፤ ድርቁ በጐዳቸው አካባቢዎች፣ ገበሬዎች ቡቃያቸው ባለበት ደርቆ እየጠፋ፣ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸው እየሞቱባቸው መሆኑን አመልክቷል፡፡
የአልጀዚራ ዘጋቢ በምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢ ተገኝቶ ያነጋገረው ኦማር መሃመድ የተባለ አርሶ አደር፤ “ቡቃያዎቻችን ደርቀዋል፤ እኛም ባዶ እጃችንን ቀርተናል” ብሏል፡፡ ልጆቹን ለመመገብም ከሶስት ላሞቹ አንዷን ሸጦ ምግብ ለመግዛት መገደዱን ኦማር ገልጿል፡፡
“የምንበላው የለንም፣ ምግብና ውሃ እንፈልጋለን” ያለው ኦማር፤ እስካሁን ከለጋሽ ድርጅቶችም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግስት ያገኘው እርዳታ እንደሌለ ተናግሯል፡፡ ሌላው አርብቶ አደር መሃመድ ፋኒ በበኩሉ፤ ከነበሩት ከብቶች 40 ያህሉ ሞተው፣ 5ቱ ብቻ መቅረታቸውን ለአልጀዚራ ተናግሯል፡፡ “መጀመሪያ ከብቶቹ ሞቱብኝ፤ አሁን ደግሞ ግመሎቼና ፍየሎች እየሞቱብኝ ነው” ብሏል – መሃመድ፡፡
ቢቢሲ በኢትዮጵያ ድርቅ ባስከተለው ረሃብ ላይ ያቀረበው ዘገባ አነጋጋሪ ሆኗል
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።

ሰሞኑን ቢቢሲ በሰሜን ኢትዮጵያ ወሎ አካባቢ ተገኝቶ ድርቁ ባስከተለው ረሃብ ላይ ያቀረበው ዶክመንተሪ፤ በተለያዩ አለማቀፍ ሚዲያዎች አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተ ሲሆን መንግስት በድርቁ የሰው ህይወት አልፏል የሚባለውን አልቀበልም ብሏል፡፡