ልማት እንዲህ ከሆነ፥ አዎ ጸረ ልማት ነኝ! ዕድገት እንዲህ ከሆነ፥ አዎ ጸረ እድገት ነኝ!
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ልማት እንዲህ ከሆነ፥ አዎ ጸረ ልማት ነኝ! ዕድገት እንዲህ ከሆነ፥ አዎ ጸረ እድገት ነኝ! Yohanes Molla
ወገን በረሀብ አለንጋ ሲገረፍ፥ እነሱ የስልጣን ዘመናቸውን ላጠናቀቁ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በ150 ሚሊዮን ብር ወጪ 6 ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን እየገነቡ፥ ከ50 ዓመት በላይ፣ በሶስት የመንግስት ለውጦች፣ “ከብዙ ደንበኛ በሚገኝ ሽያጭ ትንሽ ትርፍ ማግኘት እንጂ ከጥቂት ብዙ ማትረፍ አይደለም” በሚለው የአባታቸው መርህ መሰረት፥ በጽናትና በታማኝነት ቆሞ ምርጥ ኬኮችን በቅናሽ ዋጋ ሲያቀርብ የኖረውን፥ እንደ ቅርስ ሊንከባከቡት የሚገባውን ባለውለታ በላይ ተክሉ ኬክ ቤትን ማፍረስ ነውር ነው።
[በነገራችን ላይ “ላለው ይጨመራል” ካልሆነ በቀር፥ ግንባታውን በየትኛውም ዓይነት መለኪያ የምስማማበት ጉዳይ አይደለም። ይህን ዜና ስሰማ፥ መጀመሪያ ትዝ ያለኝ ለድርጅታቸው መኖሪያ ቤታቸውን በስጦታ ያበረከቱ ባለስልጣን ናቸው። መቼም ባለስልጣኑ አንድ የመኖሪያ ህንጻ ለድርጅታቸው ሲያበረክቱ፣ እሳቸው ቢያንስ ሌላ የመኖሪያ ህንጻ አላቸው ማለት ነው። ግን እንኳን ሁለቱን አንዱንስ ከየት አመጡት?? 10,000 ብር በማይሞላ ደመወዛቸው ገንብተውት ነበር? በየሁኔታው የሚያደርጓቸው ውድ ስጦታዎችስ ከየት የመጡ ናቸው?]
ልማት እንዲህ ከሆነ፥ አዎ ጸረ ልማት ነኝ! ዕድገት እንዲህ ከሆነ፥ አዎ ጸረ እድገት ነኝ!
በላይ ተክሉ ኬክ ቤት፥ ቢያንስ የከተማን ረኀብ በማስታገስ ረገድ የተጫወተውን ሚና ያየውና የኖረበት ብቻ ነው የሚያውቀው። በላይ ተክሉ ኬክ ቤት ብዙ ዓለም አይተናል። በልጅነት የሆያ ሆዬ ብር ስንካፈል ሮጠን በላይ ተክሉ ኬክ ቤት ተሰይመናል። የእሁድ መዋያ ሲሰጠን አጠራቅመን በላይ ተክሉ ኬክ ቤት ከቤተሰብ ተደብቀን በልተናል። ከቤት ከትልልቅ ሰዎች ጋር ስንወጣ በላይ ተክሉ ኬክ ቤትን ባልዋለችበትም ፈልገናት ተቅበዝብዘናል። በላይ ተክሉ ኬክ ቤት ስብርባሪ ኬክ በነጻ ተሰጥቶን በልተናል።
ጎርመስ ስንል ኬክ በመደጋገም ግዙ በበላ ቁማር ተጫውተናል። በወጣትነት በላይ ተክሉ ኬክ ቤት ፍቅረኛችንን ይዘን ሄደን ተዝናንተናል። በጉልምስና በላይ ተክሉ ኬክ ቤት ሄደን ምሳና ቁርስን ሸውደናል። በላይ ተክሉ ኬክ ቤት ውስጥ ታሪክና ትዝታችን ተመዝዞ አያልቅም።
በላይ ተክሉን ማንሳቴ፥ የማፍረስና የመገንባት ነገር እዚህና እዚያ መሆኑን ለማሳየት ነው።
“ሕዝብን መርዳት፣ ብዙኃኑን መጥቀም ከሁሉ የበለጠ ቀደምት ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት ታላቅ ስህተት ነው። ስለዚህ ሁሉ መንግስት መሠረቱና ዓላማው ለሕዝብ አገልግሎት መሆን አለበት። በሕዝብ ያልተደገፈ፣ ለሕዝብ ያልቆመ መንግስት መሰረት የለውምና ዘላቂ ሊሆን አይችልም፤ ጠፊ ነው።” – ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለ ማርያም “ኦቶባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ)”