ሙስሊሙ መብቱ እስኪከበርለት ድረስ ስልቱን እየቀያየረ ከመታገል ወደኋላ አይልም ! ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የመግለጫው የፒዲኤፍ ቅጂ ሊንክ፡-

መግለጫው በድምጽ ቅጂ ቆይቶ የሚለጠፍ ሲሆን ሙሉ ቃሉ በጽሁፍ ደግሞ እንደሚከተለው ይነበባል፡-
በስልጤ ዞን ኒቃብ እና ሂጃብ ላይ የታወጀው ዘመቻ የብሔራዊው ጭቆና አካል ነው!
ሙስሊሙ መብቱ እስኪከበርለት ድረስ ስልቱን እየቀያየረ ከመታገል ወደኋላ አይልም!
እሁድ ጥቅምት 21/2008/ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
በደቡብ ህዝቦች ብሄርና ብሄረሰቦች ክልል የሚገኘው ስልጤ ዞን የክልሉን 6 በመቶ አካባቢ የህዝብ ብዛት እንደሚሸፍንና ከዚህም ውስጥ ከ97 በመቶ በላይ የሚሆነው የእስልምና እምነት ተከታይ መሆኑን ፖለቲካዊ ይዘትን የሚላበሰው የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ይገልፃል፡፡ የስልጤ ህዝብ ለእስልምና ልዩ ቦታና ክብር ያለውና ከእምነቱ ለመነጠል የተደረጉ ታሪካዊ ጫናዎችን በመቋቋም ማንነቱን ጠብቆ መቆየት የቻለ ህዝብ ነው፡፡ እምነቱን አስመልክቶ የሚደርሱበትን በደሎች ሁሉ እንደታገለው ሁሉ ዛሬም ገዢው መንግስት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ የሚያደርሰውን በደል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጎን ተሰልፎ እየታገለ ይገኛል፡፡ መንግስት በተለያዩ አጋጣሚዎች ለስልጤ ህዝብ ያለውን የተዛባ አመላካከት የገለፀ ሲሆን በቅርቡም በወራቤ ሪፈራል ሆስፒታል ምርቃት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ህዝቡን ‹‹ድንጋይ ወርዋሪ›› ሲሉ በመሳደብ ለህዝቡ ያላቸውን ንቀት ማሳየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
የብሄራዊ ጭቆናው መገለጫዎች
ገዢው ስርዓት ሙስሊም ኢትዮጵያውያንን በእምነታቸው ምክንያት መጨቆኑ በትምህርት ተቋማት ባወጣቸው ሰንካላ ህግጋት ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ተመሳሳይ መሆኑ ዘርፈ ብዙ ጭቆናውን ‹‹ብሄራዊ ጭቆና›› አስኝቶታል፡፡ በትምህርት ተቋማት አካባቢ እያደረሰ ያለው በደልም የዚህ ብሄራዊ ጭቆና አንዱ ክፍል ብቻ ነው፡፡ በእምነታቸው ጠንካራ የሆኑ አካባቢዎች እየተመረጡ የሚደረገው ትንኮሳም የዚህ የብሄራዊ ጭቆና ማስፈፀሚያ አካል ነው፡፡ በአርሲና በባሌ፣ በደቡብና ሰሜን ወሎ፣ በቤንሻንጉል፣ እንዲሁም በስልጤ ዞን እየደረሱ ያሉት በደሎች አጠቃላይ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ ለታቀደው ጭቆና ንጥልጥል እርምጃዎች እንጂ ሙሉ የጭቆናው ገፅታዎች አይደሉም፡፡ በተለይም በተለያዩ አካባቢዎች በሴኪውላሪዝም ስም የሚደረገው መንግስታዊ ተቋማትን ሳይሆን ሙስሊሞችን ከእምነታቸው የማራቅ ዘመቻ ድምር ውጤቱ ለነገው የአገሪቱ ህልውና ከባድ አደጋን የሚፈጥር ነው፡፡
‹‹ከሃይማኖታችሁ ወይ ከትምህርታችሁ አንዱን ምረጡ!››
ባለፉት አስከፊ ስርዓቶች ሰፊ ጠባሳ ጥሎ የሄደው ሙስሊሞችን ከትምህርት የማግለል ተግባር አሁንም መልኩን ቀይሮ መምጣቱ እጅግ አሳዛኝ ሆኖ ይታያል፡፡ በቀደሙት ስርዓቶች ሙስሊሞች ወደትምህርት ሲመጡ ‹‹ኢትዮጵያዊ መሆናችሁን አስመስክሩ›› እስከመባል የሚደርስ ማጉላላት ይፈጸምባቸው ነበር፡፡ አሁን ላይ ደግሞ መልኩን ቀይሮ ሙስሊሞች ከሃይማኖታቸው እና ከትምህርታቸው አንዱን እንዲመርጡ የሚገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሰላትን፣ ሂጃብን እና ኒቃብን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች ጊዜን እና ሁኔታን እየጠበቁ በመንግስት ሀላፊዎች አነሳሽነት ሕገ መንግስቱን በሚጥስ መልኩ ሲተገበሩ ቆይተዋል፡፡ ሙስሊሞች በዓለምአቀፍ ደረጃ የትም ቦታና ከባቢ ውስጥ የሚሰጣቸውን ሃይማኖታቸውን የመተግበር እና መሠረታዊ የግዴታ አምልኮቶቻቸውን የመፈጸም መብት ሲከለከሉ ቆይተዋል፡፡
በዓለማችን በሴኪውላር አገራት በትምህርት ተቋማት ውስጥ ሙስሊሞች ሰላት መስገድን እና ሂጃብ መልበስን አይከለከሉም፡፡ በኤርፖርቶች፣ በዓለም አቀፍ ፖለቲካዊ ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት እና በስብሰባዎች ሁሉ ይህ የሙስሊሞች መብት ተከብሮላቸው ሳለ በአገራችን ግን ‹‹ትምህርት ቤት ውስጥ ሰላት አትሰግዱም፣ ሂጃብ እና ኒቃብ አትለብሱም›› በሚል በርካታዎች ይባረራሉ፡፡ ከትምህርታቸው ይስተጓጎላሉ፡፡ ትምህርቱን ዓለማዊ ለማድረግ የወጡ ሕጎች በተቃራኒው ‹‹ሙስሊሙን ሴኪውላር ለማድረግ›› ዓላማ ይውላሉ፡፡ በሕገ መንግስቱ የተቀመጠው ድንጋጌ ትምህርት ከየትኛውም ሃይማኖት ነጻ መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ሆኖ ሳለ የኢህአዴግ ጥረት ግን ትምህርቱ ሳይሆን ተማሪዎቹ ራሳቸው (በተለይም ሙስሊሞች) ‹‹ሃይማኖት አልባ›› እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡
አዎን! ሌሎች ኢትዮጵያዊያን አገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሃይማኖት ትምህርት መስጫ ተቋማት እንደልብ እንዲሰሩ እና በየዓመቱም ሺዎችን እንዲያስመርቁ እድል ተሰጥቷቸው ሳለ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ግን ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስቶ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ የመማር እድል እንኳ እየተነፈገው ይገኛል፡፡ ይህ ‹‹አገሪቱን ከታሪካዊ ሃይማኖታዊ እና ጎሳዊ ጭቆና ነጻ አውጥቻለሁ!›› እያለ ለሚደሰኩረው መንግስት እስከመጨረሻው ታሪኩን የሚያበላሽ ታላቅ ውድቀት ነው፡፡ ግማሽ ሕዝቡን ከትምህርት ለማገድ ሰበባ ሰበቦችን የሚፈጥር፣ ሃይማኖታዊ መብቶችን በመንፈግ ውጥረት ለመፍጠር የሚሰራ መንግስት በምንም መልኩ አገርን ሊያሳድግ አይችልም፡፡
ስልጤ ዞን እንደ ቤተ-ሙከራ!
በቅርቡ በስልጤ ዞን ኒቃብን እና ሂጃብን ዒላማ ያደረገ ዘመቻ በመንግስት እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ ከትምህርት ተቋማት አንስቶ እስከመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ድረስ ሙስሊም ኒቃብ ለባሽ ሴቶች መብታቸው እየተገፈፈ፣ ወይ ከሃይማኖታቸው ወይ ከትምህርት/ስራቸው አንዱን እንዲመርጡ እየተገደዱ ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ የወጡት መረጃዎች በእውነቱ አገሩን ለሚወድ እና ውድቀቷን ለሚጠላ ዜጋ ሁሉ ትልቅ የራስ ምታት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ይኸው ጥረት በስልጤ ዞን ብቻ የተገደበ እንዳልሆነም ግልጽ ነው፡፡ መንግስት የተወሰኑ ሙስሊም የሚበዛባቸውን ክልሎች እንደመሞከሪያ በማድረግ ወደሌሎች ክልሎችም ጸረ-እስልምና ደንቡን ለማጽደቅ እየሞከረ ነው፡፡
ሰላትና ሙስሊም አይነጣጠሉም!
የሙስሊም ዋናው መገለጫው ሰላት መስገዱ ነው፡፡ ሙስሊም በማንኛውም ቦታ ቢሆን የሰላት ጊዜው በደረሰበት ሰዓት መስገዱ ግዴታው ነው፡፡ ‹‹የሙስሊሙን መብት አክብሬያለሁ! ሰላቱን ግን ከልክያለሁ!›› የሚለው መንግስት በሙስሊሙ ላይ የስላቅ ሳቅ በመሳቅ ላይ ይገኛል፡፡ ሙስሊም ባለበት ቦታ ሁሉ መስገድ እንዳለበት የዓለም ሀገራት ሁሉ የሚያውቁትና በነፃነት እንዲተገበር የሚፈቅዱትም ጉዳይ ነው፡፡ በሀገራችን ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንኳን ለሙስሊም ሰራተኞቻቸው የመስገጃ ቦታን አዘጋጅተው ጁሙዓና ዒድ ሰላት እንደሚሰግዱ የታወቀ ነው፡፡ በአፍሪካ ህብረትም፣ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ኢሲኤም፣ እንዲሁም በሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት ሁሉ ለሙስሊሙ አመቺ ቦታን ፈጥረዋል፡፡ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጣቢያ እንኳን ለሙስሊም ተጓዦች የመስገጃ ቦታ አለ፡፡ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀና ሙስሊሞች ይኖሩበታል በሚባል ቦታ ሁሉ መሟላት ያለበት ግዴታ (standard requirement) ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊያን በኋላ እስልምናን የተቀበሉት አገራት ዜጎች በነፃነት የሰላት ግዴታቸውን ሲወጡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ግን በተቃራኒው ‹‹ወይ ከሃይማኖታችሁ ወይ ከትምህርታችሁ አንዱን ምረጡ!›› መባላቸው የስርዓቱን ጨለምተኛነት ያሳያል፡፡
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይም ዘመቻው እየተጀመረ መሆኑን ማየት ተችሏል፡፡ እንደምሳሌ ብናይ በቅርቡ በመዲናችን አዲስ አበባ የካራቆሬ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አሻሽሎ ያወጣው ደንብ ሙስሊም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመማር የሙስሊም ማንነታቸውን አውልቀው እንዲጥሉ የሚያስገድድ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የደንቡ አንቀጽ 1.9 ከኢትዮጵያ ሕገ መንግስት እና አገሪቱ ተቀብላ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ጋር በሚጣረስ ሁኔታ ‹‹ማንኛውም ተማሪ በምሳ ሰዓት ሃይማኖትን ምክንያት በማድረግ ወደውጭ መውጣት አይችልም፡፡ በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ምንም ዓይነት የሃይማኖት እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም፡፡ አድርጎ የተገኘ በቀጥታ ከትምህርት ቤቱ ይባረራል›› ይላል፡፡
የተንጋደደው የሴኪውላሪዝም አስተሳሰብ
ሙስሊሞች ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን እንዳይፈጽሙ መከልከል በምንም መልኩ ሕጋዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ከሴኪውላር (ዓለማዊ ስርዓት ከሚከተሉ) አገራት የትምህርት ተቋማት ሕግ ጋርም ፍጹም ይጣረሳል፡፡ በትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ‹‹ከሃይማኖት ተጽእኖ ነጻ ይሆናል›› ማለት ‹‹ተማሪዎቹ ሃይማኖታቸውን አውልቀው ይጥላሉ›› ማለት አይደለም፡፡ አንድ መንግስትም የአገራዊ መስተጋብር ድርና ማግ የሆኑ ሃይማኖታዊ እሴቶች ላይ ግልጽ ጦርነት የማወጅ መብት የለውም፡፡ መንግስት ይህንን ማድረጉ ‹‹ጸረ እስልምና ነኝ!›› ብሎ ከማወጅ በፍጹም አይተናነስም፡፡ ዜጎችን ከትምህርት እድል ማግለል ከ‹‹ብሄራዊ ጭቆና›› ያነሰ በደል አለመሆኑንም ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል፡፡
ተቋማት ለሰራተኞችና ለተማሪዎቻቸው የተመቹ መሆን አለባቸው!
ንፁህ አስተሳሰብ ላለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ መሰረታዊ ሃይማኖታዊ መብቶችን መገንዘብ ቀላል ነው፡፡ ለምሳሌ የመንግስት ፓርላማን ጨምሮ በሁሉም ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚዘጋጁ ምግቦች የኦርቶዶክስ ክርስትያኖችን የፆም ስርዓቶች ያከበሩ ሆነው እናገኛለን፡፡ እነዚህ ተቋማት ‹‹ስርዓታችን ሴኪውላር ስለሆነ የፆም ጉዳይ አይመለከተንም›› አይሉም፡፡ ይህንን የፆም ስርአት ካላከበሩ የሃይማኖቱ ተከታዮች አገልግሎቱን መጠቀም እንደማይችሉ ይረዳሉ፡፡ ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች መሠረታዊ የእምነት መገለጫ አመቺ ሁኔታን ባለመፍጠራቸው ተቃውሞ እንዳይቀርብባቸው በማሰብ አስፈላጊውን ያሟላሉ፡፡ በአንፃሩ ግን ሙስሊሞች የእለታዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ‹‹ሰላት እንስገድ›› ሲሉ መጀመሪያውኑም ሙስሊሙን ለማጥቃት የተገመደው ‹‹የሴኪውላሪዝም›› ጅራፍ ይወነጨፍባቸዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በሴኪውላሪዝም ስም በሙስሊሙ ላይ ብቻ ተነጥሎ የሚተገበር የማግለል (descrimination) አካል መሆኑን ከዚህ መረዳት አይከብድም!
በደል የትግል ምንጭ ነው!
በእነዚህ እና መሰል ጥቃቶች መንግስት ኢትዮጵያዊው ሙስሊም እንደቀደሙት ዘመናት በበታችነት ስሜት እንዲታሰር እና ራሱን ከአገሪቱ ሁለገብ ዘርፎች እንዲያስገልል ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ማድረግ ግን የሚሳካ አይደለም፡፡ ዛሬ ሙስሊሙ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መብቱን በሚገባ ያውቃል፡፡ መብቱን ከማወቅ ባለፈም ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ብቁ እና ዝግጁ መሆኑንም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲያስመሰክር ቆይቷል፡፡ ትግሉን አጽንቶ የሚቀጥለውም በበታችነት ስሜት ሳይሆን ነገ ሽንፈት የበደለኞች መሆኗን አጥብቆ በሚያምን እና መብቱንም በትግል ማግስት እንደሚያስከብር በሚያውቅ ቆራጥ የታጋይ ልቦና ነው፡፡ ስለዚህም መብቶቹ እስኪከበሩ ድረስ ሳይሰለች መታገሉን ይቀጥላል፡፡ ጊዜውን እና ሁኔታውን እያገናዘበም አመቺ የትግል ስልቶችን እየቀያየረ በመጠቀም በደልን መተናነቁን ይገፋበታል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች እየተደረገ ያለው ጭቆና እርከኑን ጠብቆ ሁላችንም ቤት የሚገባ በመሆኑ በአንድነትና በርብርብ የምንታገለው ይሆናል፡፡ በመሆኑም የሚከተሉትን 3 ተግባራት በመፈጸም ነገ በራችንን በየተራ የሚያንኳኩትን ዘመቻዎች እንከላከል ዘንድ አጥብቀን አደራ እንላለን፡-
1/ የዘመቻዎቹን መረጃ እና ዜናዎች በማህበራዊ ሚዲያ እና በሌሎችም መንገዶች በማሰራጨት እየተፈጸመ ያለውን በደል ማሳየት፤
2/ በዘመቻዎቹ ላይ እየተሳተፉ ያሉትን ግለሰቦች በመለየት የማንነታቸው መረጃ ለማህበራዊ ቦይኮት እንዲውል ማመቻቸት፤
የመንግስት መጠቀሚያ ሆነው የአፈናውንና የጭቆናውን በትር በሙስሊሞች ላይ ለማሳረፍ የሚታትሩትን ሰዎች በማጋለጥ የማህበራዊ ቦይኮት አካል እንደሚሆኑ ማወቅ ይገባቸዋል፡፡ በቅርቡም የፈፃሚዎቹን ማንነት ለማውጣት የሚያግዝ የጥቁር መዝገብ ፎርም (black list) ይዘጋጃል፡፡ ፎርሙን በመሙላት ሁሉም የበኩሉን ማድረግ አለበት፡፡ በተለይም የአካባቢውን ቋንቋ የሚያውቁ ተወላጆች ይህንን መረጃ የማሰባሰብ ልዩ ሀላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ትንኮሳ ውስጥ መሪ የሆኑትንና ተሳትፎ ያላቸውን አካላት በመለየት ሙሉ መረጃዎቻቸውን በመሰብሰብ በጥቁር መዝገብ ማስፈር ጊዜ ሳንሰጠው ልንተገብረው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
3/ የተቃውሞ ግራፊቲዎችን (በብርም ሆነ በግድግዳዎች ላይ ጭምር) በየቦታው መፃፍ እና የትግሉን ተጽእኖ እና ተሰሚነት ማስፋት፤
በዚሁ መሰረት ከዚህ ቀደም የተቃውሞ መግለጫ ተብለው ሲሰሩ የቆዩ ስራዎች በመሰራት የሚቀጥሉ ሲሆን በተለያዩ ቦታዎችና የብር ኖቶች ላይም የግራፊቲ መልእክቶችን የመፃፍ ተግባሮቻችን ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ ‹‹በደሎች ሲበረቱ የፍርሀት ድባብን መፍጠር እንችላለን›
› ብለው የሚገምቱት ባለስልጣናት ትግላችን ለዓለማዊ ጥቅም ሳይሆን የሁለት ዓለም ስኬትን ያለመ በመሆኑ በደሎች ፍርሀትን ሳይሆን ቁጭትና ብርታትን እንደሚፈጥሩልን ባሰለፍናቸው የትግል አመታት ቢመለከቱትም በትዕቢት ተወጥረው በጀመሩት የጥፋት ቁልቁለት መንደርደን መርጠዋል፡፡ ማስፈራሪያ፣ ማዋከብ፣ እስርና ዱላ ትግላችንን የማቆም አቅም ቢኖራቸው ኖሮ ትግላችን የአመታት እድሜ ሊያሰቆጥር ቀርቶ ወራትን መሻገር ባልቻለ ነበር፡፡ ለእምነት የሚደረግ ትግል በማስፈራሪያ የማይለዝብ፣ በእስርና ድብደባ የማይቀዘቅዝ፣ በአዋጆችና ህጎች የማይደበዝዝ አስፈላጊና ተገቢ በሆነው ቦታ ሁሉ ማንኛውም አይነት መስዋእትነት የሚከፈልበት የህልውና ትግል ነውና!!!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
Like ☑ Comment ☑ Share ☑

