ህገ መንግስቱ ዜጎችን በህግ የማይጠየቁና የሚጠየቁ በሚል ይከፍላልን ? – የምታውቁ መልሱልኝ – Girma Bekele
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
1.ጠቅላይ ሚ/ራችን አገራችን በረሃብ አደጋ ወድቃለች በተባለበት ‹‹ በአገር ደረጃ በምግብ ራሳችንን ችለናል፡፡›› ሲሉ ገልጸው ሲያብራሩም — ይህ ማለት ለአገሪቱ ዜጎች በሙሉ የሚፈለገውን ካሎሪ የሚያሟላ ምርት አምርተናል ማለት እንጂ በቤተሰብ ደረጃ በምግብ ራሳችንን ችለናል ማለት አይደለም፡፡ ማለትም ለሁሉም ዜጎች የሚበቃ ምርት በአገሪቱ ቢመረትም/ ቢኖርም በተለያየ ቦታ ስለሆነና የስርጭት ችግር ስላለ እንጂ እንደአገር የምግብ እጥረት የለም…. ›› ብለውናል፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስለረሃቡ ተጠይቀው ሲመልሱ ደግሞ — ‹‹ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚሰራጭ ምግብ/እህል ከውጪ ገዝተን እየተጓጓዘ ነው›› ብለዋል ፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ የአገሪቱ ምርት የት ደረሰ ?
የቅድመ ትንበያ ማስጠንቀቂያውን መረጃ አቆይተን ይህ አባባላቸውና ገለጻቸው ብቻ መዘናጋትና ህዝብን ማሳሳት አይደለምን፣ በቂ ቅድመ ዝግጅት እንዳይደረግ ብቻም ሳይሆን ለውጪ ረጂዎች የተሳሳተ መረጃ በማቅረብ ‹‹እንዳይደርሱልን›› ለሰብዐዊ እርዳታ ቸል እንዲሉ/ በተግባር እንዳደረጉት/ በማድረግ በረሃቡ ለጠፋው የዜጎች ህይወት ፣ የመተዳደሪያ ሃብት/ እንስሳትና…/ ውድመት አስተዋጽኦ ማድረግ አይደለምን ?
ይህስ ለአንድ ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆን ቀርቶ ጠጠር ባልወረወሩበት በ‹‹ሽብርተኝነት›› እና ሌሎች የፈጠራ ወንጀሎች በወህኒ ታጉረው ህክምና ተከልክለው ሥቃይ ከሚቀበሉ ፍርደኞችና በቀጠሮ ያሉ ዜጎች በሞሉበት አገር የከፋ ወንጀል አይደለምን፣ አያስጠይቅም ? በተለይ ጠ/ሚ/ሩ ካላቸው ሥልጣንና ኃላፊነት/ተጠያቂነት አንጻር ጥፋቱን/ወንጀሉን አያከብደውምን ?
2. ዛሬ ጠ/ሚ/ሩ በአገሪቱ የአሰራርና አመራር ችግሮች በተደረገ ጥናት ላይ የመንግስት ባለስልጣናትን ሲያወያዩ በውይይቱ ላይ አቶ ሙክታር ለአቶ በከር ሻሌ መልስ በሚመስል ቃል በቃል ‹…. ‹‹ critical situation ውስጥ ነው ያለነው…. >> አስከትለውም ያለንበት ችግር serious ነው…. ›› ብለዋል፡፡
በየአገልግሎት መስጫው ተገቢውን አገልግሎት በማጣታቸው በተጨባጭ በደረሰባቸው ችግር ከአቶ ሙክታር አገላለጽ በለሰለሰ መንገድ ችግሩን በመግለጻቸው ስንት ዜጎች ናቸው በቀበሌ ካድሬዎች እየተደበደቡ ለእስር የተዳረጉት፣ የሚዳረጉት፣ ይህን ህገወጥ አሰራር በመቃወማቸው ስንቶች ናቸው በፈጠራ ክስ ወህኒ የተወረወሩት?
ስለዚህ ነገ ከነገ ወዲያ አቶ ‹‹ ሺመልስ ከማል ›› ጠቅላይ ሚ/ሩንና አቶ ሙክታርን በዜጎች ላይ ክህደት መፈጸም ወይም በቸልተኝነት ዜጎችን ለሞትና ሥቃይ በመዳረግ ወይም ‹‹መንግስትን በመዳፈር ›› ወንጀል በሰው ማስረጃ የኢትዮጵያን ህዝብ ፣ በሰነድ ማስረጃ በ‹‹ኢቢሲ›› የተናገሩትን አቅርበው ‹‹ፍርድ ቤት ›› ሲገትሩኣቸው እናያለን ወይስ ህገ መንግስቱ ዜጎችን በህግ የማይጠየቁና የሚጠየቁ በሚል ይከፍላል ብለን አርፈን እንቀመጥ ? በግልጽ ይነገረን፡፡ በቸር ያገናኘን//