የዶክተር አክሊሉ ሐብቴ አቋም ሰውን ግራ አጋባው – ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ አቋማቸውን በየጊዜው በመቀያየር፡ የዋሽንገትን ዲሲ ቅድስት ማርያምን ወደ አቡነ ማትያስ ጉያ ለመክተት ከፈለጉት ሰዎች ጋራ መስማማታቸው ሰውን ግራ አጋባው። ሙሉውን ለማንበብ የሚቀጥለውን ሰንሰለት በመጫን ይመልከቱ። የዶክተር አክሊሉ አቋም

Dr. Aklilu

የዶክተር አክሊሉ ሐብቴ አቋም ሰውን ግራ አጋባው

ጥቅምት 15 ቀን 2008  ..

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ

[email protected]

 

ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ አቋማቸውን በየጊዜው በመቀያየር፡ የዋሽንገትን ዲሲ ቅድስት ማርያምን ወደ አቡነ ማትያስ ጉያ ለመክተት ከፈለጉት ሰዎች ጋራ መስማማታቸው ሰውን ግራ አጋባው።

በትምህርት፡ በሽምግልና፤ የዩንቨርሲቲ  ፕሬዝደንት ሆነውም፤  የምሁራንን ጭንቅላት በመምራት እና ፤  ጥራት ባላቸው መምህራን በሚቀርብላቸው የእውቀት ትምህርት እንደ ሰንጋ ፈረስ የሚቁነጠነጠውን የተማሪ አዕምሮ በመግራት ሰፊ ልምድ አላቸው የሚባሉት ዶክተር አክሊሉ  በዚህች  ጦማር ከዘረዘርኳቸው ሰዎች ጋራ  ራሳቸውን ደምረው ራሳቸውን ማስመዘናቸው የራሳቸውን ሁለንተናነት በማዋረድ ተመልካቹን ግራ እያገቡ ነው።

 ይልቁንም  ምሳሌነታቸው ለሚዛንነት ከሚጠቀስላቸው  በኢትዮጵያ ታሪክ  እና በትውልድ ጭንቅላት ላይ እንደ  ወርቅ አእማድ  ሲፈልቁ ከሚኖርት አባቶቻችን ጋራ  መደመር በተገባቸው ነበር።    የወርቅ አእማድ ያልኳቸው አባቶቻችን፤ ነፍሳቸውን ይማርን ለዶ ክተር አክሊሉ እድሜ ቅርብ የሆኑት ከዚህ በታች የምጠቅሳቸው ከብዙዎቹ ጥቂቶች ናቸው።  እነዚህም፦ ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፤ በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያትና፤ አምባ አሳደር ዘውዴ ረታ ናቸው።

ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፤ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጥቃት የበዘበት ወይም ቁጭት የተጠራቀመበት ቢሆን፡ ከሕግ ውጭ በራሱ እርምጃ ፈንታውን ሌላውን ለማጥቃት ቢነሳ፡ አጥፊዎች በተባሉት እግር ራሱ ተመልሶ ከመግባቱ በቀር የሚጠቅመው ነገር የለም። አሁን ጥፋት ሆኖ የሚታየንም ከትውልድ ተያይዞ በውርስ የመጣ ጭምር እንዳለበት ሊታወሰን ስለሚገባ እርስ በርስ ከሚያጣላን ይልቅ የሚያፋቅረን መፈለጉ ጠቃሚ ነው። በዚህ ዓይነቱ የውስጥ ሁኔታና የእርስ በርስ ጠብ በ16ኛው መቶ  ዓ. ም ግራኝ አህመድ፤  በ20ኛው መቶ ዓ.ም  መሶሊኒ  ኢትዮጵያን ለማጥቃት ተጠቅመውበታል“ (ግራኝ አህመድ ገጽ V ) ብለው በተናገሩት፤  ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅ በትውልዱ ሁሉ ጭንቅላት ሲፈልቅ የሚኖር የማይዝግ ወርቃማ ሚዛን ሰጥተውን አልፈዋል። ዶክተር አክሊሉ የክቡር ተክለ ጻድቅ መኩሪያን ማስጠንቀቂያ የኑዛዜ ቃል፤  ለከበባቸው ቡድን ከማስተጋባት ይልቅ አሁን እየሄዱበት ያሉበት አቋም ግራ የሚያገባ ነው።

ክቡር በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያትም “ለኢትዮጵያ ሀላፊነት ለሚቀበለው መሪ በኢትዮጵያዊነት ግዳጄ ለማገልገል የምቀርበውም ለአገራችን እድገት ለህዝባችን ደህንነት የሚጥር የሚያስብና የሚሰራ ሆኖ ሳገኘው እንጅ፡ በውርሱ ንጕሥ፤ በዘሩ መስፍን ነው ብየ አይደለም” ብለው  የተናገሩት የንግሥናቸውንና የምስፍናቸውን ነቃፊ ለመስበር  አንበሳና ነብር ሆነው በተሰለፉት በንጕሡና በመሳፍንቱ ፊት ነበር።   የበጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት  ቀጥ ያለው አቋማቸው፡ ለዘላለም ሲፈልቅ የሚኖር ከሰንፔር የተገነባ አምድ አርጓቸዋል(የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ገጽ፡31)። ዶክተር አክሊሉም  ይህን መሳይ ቀጥ ያለ አቋም ማሳየት ይጠበቅባቸው ነበር።

በቅርቡ  በሞት ተለይተውን  እነዚህን አባቶች የተቀላቀሏቸው  ክቡር አምባ አምባሳደር ዘውዴ ረታም፤ “የኢትዮጵያ አርበኞችና ጀግኖች ታሪክ፡ ራሱን የቻለ አንድ ትልቅ መጽሐፍ የሚወጣው ስለሆነ፡ ወደፊት እኔም  ሆንኩ ሌሎች ጸሐፊዎች አስፈላጊውን እንደምንፈጽም ተስፋ አደርጋለሁ” ብለው ያለፉ ከነዚህ አእማድ አንዱ ናቸው።

”ወደፊት እኔም ሆንኩ ሌሎች ጸሐፊዎች አስፈላጊውን እንደምንፈጽም ተስፋ አደርጋለሁ” ብለው ክቡር  አምባሳደር ዘውዴ ረታ እንደ እሳቸው ገብቶ ሊመወጣ ዜጋ ወርቃማውን በር ክፍት አድርገው በተውልን ወርቃማ በር ገብተው  ለመውጣት  ከዶክተር አክሊሉ የበለጠ መጣር ያለበት ሰው ያለ አይመስለኝም። በዚህ ወርቃማ  በር ገብተው በመውጣት የማይዝግ ወርቃማ  ውርስ ትተው ለማለፍ ከመጣር ይልቅ፤  አሁን በቆሙበት የነፋስ ሽውታ በሚጠርገው ገለባና አፈር ላይ መቆማቸው ሁሉንም ግራ አጋበው።  

ለዶክተር አክሊሉ መፈራረጃነት የምጠቅሳቸው ሌላው በዚህ ዘመን ያለው ትውልድ “አንተ ኮ ኩህ” (አንተ አለት ነህ)የሚላቸው፤ በጥቅጥቅ ጨለማ ውስጥ በሩቅ እንደ ምትታይ የጧፍ መብራት ሆነው፤ በዚህ ጨለማ ዘመን የሚታዩት፤ የተጠራቀመ  ትዝብት የከበዳቸው፤  “አርበኛ ገዳዮች ነን” እያሉ ራሳቸውን ይዘው ኢትዮጵያውያን ባሉበት ስርቻ ሁሉ እየገቡ በመጮህ ላይ ያሉት፤  ፕሮፌሰር መስፍን  ወልደ ማርያም ናቸው።  ዶክተር አክሊሉ  የፕሮፌሰር መስፍን  ወልደ ማርያምን  ያህል ለመጮኸ ትንፋሽ ቢያጥራቸው እንኳ፤  አሁን የሚናገሩትን ከመናገር ዝም ቢሉ ባፋቸው ዝምብ አይገባም ነበር።

ባንድ ወቅት ባንድ ስብሰባ ላይ ይህ ትውልድ፤  “አንተ ኮኩህ” (አንተ አለት ነህ) ስለ ሚላቸው ፕሮፌሰር መስፍን ዶክተር አክሊሉ እንዲህ ብለው ነበር።  “መስፍን ከማንም አይገጥምም፤ አብረን በምንሰራበት ጊዜ ሀሳቡን አስለውጠን ከኛ ጋራ እንዲቆም ስንፈልግ፤ ልናደርግ የፈለግነውን ነገር አክፋፍተን እንነግረው ነበር” ብለው የተናገሩትን በስብሰባው የነበሩት ያስታውሱታል።  ዶክተር አክሊሉ በፕሮፌሰር መስፍን አቋም ላይ የሰጡት የነቀፋ ዘርቅ፤  የሁለቱን አቋም በማናውቅ አዕምሮ ላይ ጥያቄ አሳድሮ ነበር። ውለን አድረን ሁለቱን ለማነጻጸር እድሉ ሲገጥመን፤  ፕሮፌሰር መስፍን ከነዶክተር አክሊሉ ጭንቅላት ጠቃሚ ነገር እንደማይመነጭ የተረዱ ቆቅ መሆናቸውን የሚገልጽ ሲሆን፤ እነ ዶ ክተር አክሊሉ ግን የሚፈልጉትን ነገር በሸፍጥ ለመፈጸም የራሳቸውን አቋም መቀያየራቸው ሳያንሳቸው፤ የሰውን ጭንቅላት በማዞር አቌም ሲያስቀይሩ መኖራቸውን የሚያረጋግጥ ነው።

ከሳቸው ጋራ የነበሩት ብዙዎቹ ከናቶቻቸው ማህጸን በምጥ ተላቀው፤  ወደዚህች ዓለም ከመጡባት ቅጽበት የጀመሩትን ምድራዊ ህይወት፤ በእናት አገራቸው ኢትዮጵ ማኅጸን የነበራቸውን የቆይታ ዘመን ከሚወዷት ኢትዮጵያ ማህጸን ሞት በሚባለው ምጥ ተላቀው፤ ለወዲያኛው ዓለም በሞት እስኪወለዱ ድረስ፤  እነ በጅሮንድ ተክለሐዋርያትን ያናወጡ ሁሉ ማእበላት፤  ምናልባት ዶክተር አክሊሉን ባያናውጣቸውም ፤ ወላፈኑ ውሽንፍሩ ሳይነካቸው አይቀርም ብሎ መገመት የሚቻል አይደለም።

ዶክተር አክሊሉን ሳስብ በፊቴ የሚደረደሩት በሚዛንነት የሚደነቁት ጓደኞቻቸው እነክቡር  በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት፤ ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አሁን በህይወት ለምስክርነት ለቅርጣን የቀሩት፤ ይህ ትውልድ “አንተ አለት ነህ” የሚላቸው ፕሮፌሰር መስፍን ናቸው። ከነሱ ጋራ ለማስቀመጥ  ስሞክር ሳሙና እንደነካው ጠርሙስ ከእደ ሕሊናየ ተሙለጭልጨው ወደቁብኝ።  

“አክሊለ ምክህ ርስዕ ሠናይ። ወውስተ ፍናወ ጽድቅ ይትረከብ” (ምሳሌ 16፡31)ማለትም፦ ሽምግልና ህብረተ ሰብ የሚመካበት ዘውድ ነው፤  እውነተኛውን ህግም በመጠበቅ ላይ ይገኛል” የሚለው ባህላዊ አመለካከታችን በዶክተር አክሊሉ መሰበሩን  ስናገር ፤ በሙታንና በህያዋን መካከል አለን የምትሉ ሽማግሎች አዛውንቶች ካላችሁ፤  ከምናገራቸው አንዷ ውሸት ብትሆን፤ ያለአንዳች ማስረጃ አሻቅቤ በመናገሬ አንተ ውሸታም ነህ፤  የምትናገረው የሌለና ያልሆነ ነገር ነው ብትሉኝ፤   ተግሳጻችሁንና ቅጣታችሁን እቀበለዋለሁ።

ይህንንም ስል “ሽምግልና በሀገር፤ በቤተ ክርስቲያንና  በእውነት ሲለካ ዝቅና ከፍ ካለ፤  በሽታና ድካም ከሚያስከትለው ከ80 ዘመን በላይ ባለ  ዕድሜ ውስጥ እንደሆነ ገምት። ከ80 ዘመን በላይ   የሚኖረው ሽማግሌ የሚጠብቀው ከሌለ ወደ ሕጻንነት ይመለሳል” ብለው የብሉይ ኪዳን መምህሬ የኔታ ጥበቡ ባንድምታቸው የገሩኝን ሳልረሳ ነው። ምንም እንኴ ስለ ፕሮፌሰ መስፍን የተናገሩትና በተደጋጋሚ የታየው ተለዋዋጭ አቋመቼው የተፈጥሮ ባህርይ ቢመስልም፤  በዶክተር አክሊሉ የሚታየው መቀያየር  የዕድሜ ሊሆንም ይችላል የሚለውን ከጥርጥር ውስጥ ማስገባቴን አልተውኩም።   

ከዶክተር አክሊሉ ጋራ በተመሳሳይ ዕድሜ  ያላችሁ አዛውንቶች ሆ ይ!ከናታችሁ ማህጸን በምጥ የጀመራችሁትን ህይወት በብዙ ውጣ ውረድ እያጠቃለላችሁ “ወደሰማይ ብወጣ አንተ ከዚያ አለህ፤ ወደ እመቀ እመቃት ብወርድም አንተ ከዚያ ትኖራለህ“ ለማለት ከጸሐይ በታች የሚቀድማችሁ  የለም። እንኳን ሰሚ ትውልድ ሳታጡ፤ ሰሚ እንኳ ብታጡ  “ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጭ የምድር መሰረቶችም ተናወጡ” እያላችሁ ወያኔ ጭንቅላታቸውን ያበለሸባቸው ኢትዮጵያውያ  ወጣቶች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ በመገኘት፤ እነ ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ የተናገሩትን ትንፋሽ እስኪያጥራችሁ  ጮሀችሁ የማሰማት ግዴታና እዳ አለባችሁ።

ክርስቶስ እንዳለው፤ ሽምግልና ብዙ የተሰጠው፤ ብዙ የሚፈለግበት ተቀድቶ የማያልቅ የጥበብ ባህር ነው ። ነገር ግን ብዙ በሚፈልግባቸው ጓዳችሁ በዶክተር አክሊሉ ግራ አጋቢ አቋም፤ እናንተም  ግራ ሳትገቡ፤ ዶ ክተር አክሊሉ ከዚህ በታች ከዘረዘርኳቸው ሰዎች ጋራ ያሳዩትን ተለዋዋጭ አቋም ተመልክታችሁ ታዘቡ። ታዝባችሁም ዝም አትበሉ። ዶ ክተር አክሊሉን፤ እራሳችሁንም፤  የሚሰማችሁንም ትውልድ ከዚህ መሳይ ግራ አጋቢ አቋም ለማዳን ትሞክሩ ዘንድ፤ ዶክተር አክሊሉ የተቀያየሩባቸውን ወቅቶችን፤  ክስተቶችን ከሰዎቹ  ጋራ ከዚህ በታች አቀረብኩላችሁ። ።  

1ኛ፦ዶክተር አክሊሉ ከአቡነ ማትያስ ጋራ  

2ኛ፦ዶክተር አክሊሉ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ

3ኛ፦ዶክተር አክሊሉ ከሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ጋራ

4ኛ፦ዶክተር አክሊሉ በጎናቸው ካሰለፏቸው ከርእሰ ደብር ብርሃም ጋራ  

5ኛ፦ ዶ ክተር አክሊሉ ሊቀ ሊቃውንት በጎናቸው ካሰለፏቸው ከነ መጋቤ ሃይማኖት መቆያ ጋራ ያላቸውን ተለዋዋጭ ግራ አጋቢ አቋም ታዘቡ። በ principle ከሚመራ በትምህርት ሊቅ፤ በዕድሜ ልሂቅ ሽማግሌ ይህን በመሰለ መለዋወጥ የሚያሳዩት አቋም ለእሳቸው እንደማይመጥን ሁሉም እየተናገረው ነው።

ዶክተር አክሊሉ ህሊናቸውን መርምረው ከሳቸው ጋራ በተሰለፉት ሁሉ ላይ እንዲፈርዱ፤ ከዶክተር አክሊሉ ጋራ የተሰለፉትም፤ ህሊናቸውን መርምረው በዶክተር አክሊሉ ላይ እንዲፈርዱ፤ ይህችን ጦማረ ያነበበ ሁሉ ደግሞ፤ በዶክተር አክሊሉ እና ከሳቸው ጋራ በተሰለፉት ላይ እንድትፈርዱ ጥሪየ ይድረሳችሁ እያልኩ፤  ዶክተር አክሊሉ ከአቡነ ማትያስ ጋራ ከነበራቸው አቋም በመጀመር ይህችን ጦማር አቅርቤላችኋለሁ።

1ኛ፦ዶ ክተር አክሊሉ ከአቡነ ማትያስ ጋራ፦

ዶክተር አክሊሉ ከመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መስራቾች ከመላከ ገነት ውቡ፤ ከኮለኔል አስፋው አንዳርጌ፤ ከኮለኔል ዳዊት፤ ከአቶ ተድላ ደስታ እና ከአቶ ክፍሌ ወዳጆ ጋራ ነበሩ። በሕይወት ያሉትን መጥቀስ ስላልፈለኩ እንጅ  በዚያን ጊዜ ከጠቀስኳቸው ወጎኖቻችን ጋራ የነበሩ፤  አሁንም  ባካባቢው ብዙዎች አሉ። እነዚህ ኢትዮጵያውን ወገኖች  አቡነ ማትያስን አጥብቀው የሚቃወሙ ነበሩ።

ከሁሉም ይልቅ በከረረ ጥላቻ አቡነ ማትያስን ይቃወሙ የነበሩት ዶክተር አክሊሉ ነበሩ። ዶክተር አክሊሉ አቡነ ማትያስን በመቃወማቸው ከመድኃኔዓልም ምእመናን ጋራ ይስማሙ እንጅ፤ ከደርግ ጋራ በነበራቸው ቀራቢነት  አዲስ አበበ ይመላለሱ ስለነበር፤ በመድኃኔዓለም ምእመናን  ዘንድም ቢሆን፤ ዶክተር አክሊሉ  የነበራቸው ተቀባይነት  ሙሉ አልነበረም።  “በጃንሆይ ጊዜ የሰሩት በደል ሳያንስ አሁን ደግሞ አቋማቸውን ቀይረው የደርግ ተላላኪ ሆኑ” እየተባሉ  በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ወላፈን  ዶክተር አክሊሉ ይለበለቡ  ነበር ።  

ዶክተር አክሊሉ ከወቅቱ  ከነበረው ፖለቲካ ጋራ በነበራቸው ግንኙነት፤   በክርስትናቸውም  ለአቡነ ተክለ ሃይማኖትም ቀራቢ  ነበሩ። ዶክተር አክሊሉ “ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጽላት አስመጣሁ”  ብለው አስወሩ። “ለመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ያስረክቡ” ሲባሉ፤  “አቡነ ማትያስ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት የተወገዙ፤ ክህነት የሌላቸው ስለሆኑ አልሰጥም” አሉ።  መላከ ገነት ውቡ  “ላልተወገዝኩት ለኔ ለምን አይሰጡኝም? ክህነት የለዎ ለምን ከቤተዎ ያስቀምጡታል? ብለው ሲጠይቋቸው፤ “ቅዳሴው የሚካሄደው በአቡነ ማትያስ ቡራኬ ስለሆነ ለእርሰዎም አልሰጥም“ በማለት በአቡነ ማትያስ ላይ  እጅግ የከረረ ተቃውሟቸውን አሳዩ ።  ደርግን ለማስደሰት እንዳደረጉትም በሰፊው ተወራባቸው።  

በዚያን ጊዜ ዶክተር አክሊሉ በአቡነ ማትያስ ላይ የነበራቸው የተቃውሞ አቋም፤ አሁን ከነ አቶ አዲሱ፤ ከነ ርዕሰ ደብር አብርሃምና ተስፋየ መቆያ አቋም ጋራ ሲነጻጸር፤ ግራ የሚያጋባ ሆኗል።  

ዶክተር አክሊሉ በዚያን ጊዜ ለአቡነ ማትያስ ጽላቱን አለሰጥም  ያሉት፤ ስለተወገዙ  ለመንፈሳዊው ስርአት መጣስ  ተቆርቁረው ሳይሆን፤ አቡነ ማትያስ  እሳቸው ይደግፉት የነበረውን ደርግን በከረረ  ሁኔታ ስለተቃወሙ ነበር ማለት ነው የተቃወሟቸው በፖለቲካ ሲሆን፤ ”ስለተወገዙ  ነው“ ማለታቸውና አሁን ደግሞ ”እንቀበላቸው“ ከሚሉት ጋራ መሰለፋቸው  ካንድ የተማረና ራዥም እድሜ ከኖረ ሽማግሌ የሚጠበቅ  አቋም ነው ታዲያ ይህ አቋም ግራ አያጋባም?   

ውግዘቱን ሰብሮ  ወደ መንበረ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን ጎትቶ የከተታቸው በነአቶ ስብሀት በኩል የወያኔ መንግስት እንጅ፤ ቤተ ክርስቲያናችን በምትፈቅደው ህግና ስርአት ውግዘቱን የፈታ፤  መፈታቱንም ለህዝበ ክርስቲያኑ የገለጸ መንፈሳዊ አካል የለም። ይህንንም አቶ አዲሱ እና አቡነ ማትያስ በቪኦኤ ራዲዮ ሲነጋገሩ ሰምተናል።  እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ፤ ከዋሸንግተን ዲሲ ቅድስት ማርያም አባላት ጋራ ሳይነጋግሩ፤ በተደበቀ ምሥጢር በመጻጻፍ ከሚያድሙት ከነርዕሰ ደብር አብርሃም፤  መጋቤ ሃይማኖትና ከአቶ አዲሱ አበበ ጋራ  ዶክተር አክሊሉ መቆማቸው ግራ አያጋባም?  

በሞት ከተለዩን  ስማቸውን ከጠቀስኳቸው ወገኖቻችን በቀር፤ በህይወት ያላችሁ  የዋሸንግተን መድኃኔዓለም ምእመናን አቡነ ማትያስንም ጭምር የምጠይቀው፤   ይህ ከዚህ በላይ ያቀረብኩት ውሸት ነው  ዶክተር አክሊሉ ዛሬ አቡነ ማትያስን እንቀበል ከሚሉት ከነ ርዕሰ ደብር አብርሃም ጋራ የተሰለፉት የአቡነ ማትያስ ግዝት ተነስቶላቸው ነው? ወይስ አቡነ ማትያስ የተቀበሉትን የወያኔን ፖለቲካ ተቀብለው ነው? ምን ይሰማችኋል?ምንስ ትላላችሁ ከዚህ ቀጥየ  ዶክተር አክሊሉ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ወደነበራቸው ግራ አጋቢ አቋም እሻገራለሁ ።

2ኛ፦ዶክተር አክሊሉ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ፦

ዶ ክተር አክሊሉ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ የነበራቸውን የማይረሳና የሚያስተዛዝብ ታሪክ እንደሚከተለው እገልጻለሁ።  ታሪኩ  ከንሳስ ላይ አቡነ ማትያስ ከፈጠሩት የስህተት ትምህርት ጋራ የተያያዘ ነው።  ጉዳዩ  በሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ሰብሳቢነት በካህናቱ ጉባዔ በታየበት ወቅት የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት ተመርምረው የአቡነ ማትያስ እምነትና ትምህርት ስህተት ሆኖ  ተገኘና ፤ ሌሎች ከኛ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው የግብጽ; የህንድ; የአርመንና የሶርያ አብያተ ክርስቲያናት እና የመላው ምስራቃውያን አብያተ ክርስቲያናትስ ምን ይላሉ? የሚል ሀሳብ ተነሳ። የሁሉም ተመርምሮ የአባ ማትያስ እምነት ከማናቸውም ኦርቶዶክሳውያን እምነት የራቀና፤  የሮማ ካቶሊክ እምነት እንደሆነ ተረጋገጠ።ጉባዔው ቀጠለና  “አቡነ ጳውሎስ  በፕርስተን ሴሚናሪ በቆየበት ጊዜ  ካንዱ ሰምተው ወስደውት ይሆን?  የሚል ጥርጥር ተፈጠረ።

በወቅቱ የከንሳስ ኪደነ ምህረትን ቤተ ክርስቲያንን በሊቀ መንበርነት ይመሩት የነበሩት አቶ ይበቃል ያረጋል፤  የኒቨርሲቲውን አነጋግረው አቡነ ጳውሎስን ለዲግሪያቸው መመረቂያ ያቀረቡት መጽሐፍ ተውሰው አስመጡት።  የተፈለገውን መረጃ ብቻ ከመጽሐፉ ተርጉመው ለጉባዔው እንዲያቀርቡልን  ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ዶክተር አክሊሉን ጠይቀው ፈቃደኛ ሆኑ። ዶ ክተር አክሊሉ የአቡነ ጳውሎስን መጽሐፍ ተርጉመው ባቀረቡት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ከሚሉት ያልተለየ እና የተስማማ  ሆኖ ተገኘ። ዶክተር አክሊሉ  በጣም አዝነው የሚከተለውን ተናገሩ።

“አቡነ ጳውሎስ ምንኛ  ክፉ ሰው ናቸው? ትክክለኛውን የኦርቶዶክሱን ትርጉም በመጽሐፋቸው ጽፈው፤  እንዴት ጠላት በሆነችው በሮማን ካቶሊክ እምነት ቤተ ክርስቲያናችን ይመሯታል!ብለው ተናደው ተናገሩ።  ቀጠሉና ”ይገርማል!ይገርማል!” ብለው፤  “እኔና ደጃዝማች ወልደ ሰማእት በነበርንበት ትምህርት ቤት አስተማሪዎቻችን የሮማ ካቶሊክ መነኩሴዎች ነበሩ። ከዕለታት አንድ ቀን አሁን አቡነ ማትያስ የሚያሰራጩትን ትምህርት በትንሽ ቅጽ በተዘጋጀች መጽሐፍ አዘጋጅተው በክፍላችን አደሉን። ወደየቤታችን ይዘን ሄደንና ወላጆቻችን ተመለከቱት። ወላጆቻችንም  ደማችን ሳይደርቅ የካቶሊክ ትምህርት ለልጆቻችን እንዴት ያስተምሩብናል” ብለው በትምህርት ቤቱ መሪዎች ላይ ተቆጥተው  ከናንተ ጋራ አንነጋረርም  ከጃንሆይ መስማት እንፈልጋለን፤  እስከዚያ ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት አንልክም“ በለው ወሰኑ።

ጃንሆይም  ከትምህርት ቤቱ ተገኝተው ፈረንጆችን እንዲያስተምሩ  ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያስመጣናቸው ምንም ምርጫ ስለሌን ነው። ያስመጣናቸውም የዘመኑን ትምህርት ብቻ እንዲያስተምሩ እንጅ የነሱን  ሃይማኖት እንዲያስተምሩ አልነበረም። ብናባርራቸው ትምህርት ቤት ይዘጋል። የምንጎዳው እኛ ነን። ይሁን እንጅ፡  ካሁን ጀምረው የሃይማኖት ትምህርት እንዳያሰራጩ  እናደርጋለን” ብለውን ወደ ትምህርት ቤት ተመለስን” ካሉ በኋላ፤ ዶ ክተር አክሊሉ ቀጠሉና “ ዛሬ በህይወት እያለን እግዚአብሔር ይህን ጉድ ያሳየን ምነው ምን በደልነው? አቶ መለሰ የላቲኖችን  ፊደል  በኦረሞዎች  ጭንቅላት ላይ፤  አባ ጳውሎስ የላቲኖችን  እምነት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ  ከሰከሱብን።  ጣሊያንስ ከዚህ የከፋ  ምን በደለን?“ ብለው  በብስጭት ተናግረው፡  የአቡነ ጳውሎስንም ፎቶ ቀደውት ነበር።  

ዶ ክተር አክሊሉ አቡነ ይስሀቅና ሊቀ ሊቃውንት ካህናቱን ሰብስበው በወሰዱት ርምጃ  ተደስተው ቡነ ይስሀቅና ለሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ   “ያደረጋችሁ ተገቢ ታሪካዊ ስራ ነው ጎሽ አቦታችንን ረዥም እድሜ ይስጥልን ። የውጩ ሲኖዶስ መስራት የሚገባውን ትቶ፤  እናንተ ቀድማችሁ ይህን በማድረጋችሁ እንኮራባችኋለን“ እያሉ  ለአቡነ ይስሀቅም  ለሊቀ ሊቃውንትም እንደነገሯቸው  ሁሉም ነግረውኛል። በዚያን ጊዜ የነበራቸው  የዶክተር አክሊሉ አቋም  ዛሬ የት ደረሰ?ችግራቸው ሃይማኖቱ  በመቃወስ ሳይሆን ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ነበር  ማለት ነውን? ይህስ ግራ አያጋባምን? ታዛቢዎች ታዘቡ!አሁን ከሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ጋራ ያላቸውን ግራ አጋቢ አቋም እገልጻለሁ።

3ኛ፦ዶ ክተር አክሊሉ ከሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ጋራ፦

ዶ ክተር አክሊሉ ከሊቀ ሊቃውንት ጋራ ያላቸውን ሐረግ ስንመዝ አቶ አዲሱ፤ ርእሰ ደብር አብርሃምና መጋቤ ሃይማኖት ተዛዝለው ብቅ ይላሉ። ከሊቀ ሊቃውንት ጋራ ያላቸውን አስተዛዛቢ ባህርይ ከጨረስኩ በኋላ፤  በሊቀ ሊቃውንት ጀርባ አሳዝለው አሁን ብቅ  ከዳደረጓቸው ሰዎች ጋራ ያሳዩትን አቋም በሀ፤ በለና በሐ ከፋፍየ ለማቅረብ እሞክራለሁ። መጀመሪያ ዶክተር  አክሊሉ ከሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ጋራ ያላቸውን ግራ አጋቢ አቋም እገልጻለሁ።

በአቶ አዲሱና በተስፋየ መቆያ አመራር አሁን በዋሸንግተን ከተማ  እየተመመ ያለው ጭፍራ፤  ተርቦ  የሚያድን  የበርሀ ተኩላ መስሎ ሽማግሌዎችን እናቶችን ህጻናትን እየረጋገጠ  ወደ   ቅድስት ማርያም ቤተ መቅደስ አውደ ምህረቱ በቀረበ ጊዜ፤ ሊቀ ማእምራን አማረ ” በዓሉን ካከበርን በኋላ እንደተለመደው ከአውደ  ምህረቱ ውጭ በድንኳን ውስጥ እንነጋገራለን። አሁን በዓሉን እናክብር” ቢሉም ጭፍራው እየሰነጠቀ ገባ። ክህነታቸውን ተጠቅመው በውገዘት ለምግታት ከመሞከር ሌላ ምንም ምርጫ ያልነበራቸው  ሊቀ ማእምራን አማረ ጭፍራው በአውደ  ምህረቱ ላይ የፈጠረውን ጫጫታ ለመግታት ሲአወግዙ፤ ሊቀ ሊቃውንት  ወርቅነህ ከቤተ መቅደሱ ተቆጥተው በሊቀ ማእምራን ጀርባ  ብቅ ብለው ውግዘቱን ሽረው የተወገዙትን እየባረኩ፤ እነ ሊቀ ማእምራንን አህዛብ እያሉ፤ ጭፍራውን የሚመሩትን ዶ ክተር አክሊሉን ተባበሩ። ምርጫ ያልነበረው ቦርድ ህዝቡን ከጉዳት፤ ቤተ ክርስቲያኗን ከኢንሹራስ እዳ ለመታደግ ቤተ ክርስቲያኗን ዘግቶ ህዝቡን አሰናበተ። ያተራመሰው ጭፍራ  የስድብ የዘለፋ ፉከራ እያሰማ  ተበተነ።  በስድብ በዘለፋና በእውካታ የተበተነውን ጭፍራ አሰባስበው የተዘጋውን በር ሰብረው ገቡ።

ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ  የህዝብ መንፈስ በተቋሰለበት ቅጽበት፤   በዶክተር አክሊሉ ጭፍራ ጫጫታ የታጀበ ቅዳሴ “አሐዱ አብ” ብለው በመቀደስ ዶክተር አክሊሉን “አብያተ ክርስቲያናት ይትረሀዋ” ብለው በአባ አጋግዮስ ስህተት የተዘጋውን፤ ቤተ ክርስቲያንን እንደከፈተው እንደ ጀግናው ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አርገው እንዲያቀርባቸው፤ በአባ አጋግዮስ ምክንያት አብያተ ክርስቲያናት ይዘጉ ብሎ  እንደዘጋው እንደ ዲዮቅልጥያኖስ አርገው እነ ሊቀ ማእምራንን እንዲፈርጁ ማድረጋቸው ግራ አያገባም(ሙሉውን ለማንበብ የሚቀጥለውን ሰንሰለት በመጫን ይመልከቱ። አባ አጋግዮስ “ዘአፍቀርከ ወርቀ አምህሰከ ወርቀ” “የወደድከውን ወርቅ አቅልጨ እግትሀለሁ!”)።

ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ የሊቀ ማእምራን አማረን ውግዘት ሽረው፤ በዶ ክተር አክሊሉ የሚመራውን ጭፍራ  ግቡ ማለታቸው፤ ተደጋጋሚ ስህተት ፈጸመ እየተባለ በሚወቀሰው ግለ ሰብ የተደረገውን ውግዘት፤  አዲሱ ተክል የዘመኑ ጳጳስ አባ ፋኑኤል አነሳሁ ብለው ቆሞስ ነህ ወደ ቤተ መቅደስ ግባበማለት የሰሩትን ይቅርታ የሌለው ስህተት፣  ዶ ክተር አክሊሉ ሊቀ ሊቃውንት እንዲደግሙት አላደረጓቸውምንይህስ ግራ አያጋባም(ሙሉውን ለማንበብ የሚቀጥለውን ሰንሰለት በመጫን ይመልከቱ። አባ ፋኑኤል አዲስ ተክል ናቸው

ዶክተር አክሊሉ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ያሳዩትን ግራ አጋቢ  አቋም ከሊቀ ሊቃውንትን ወርቅነህ ጋራም አገናኝቷቸዋልና ፤ የተገናኑበትን ሰንሰለት ለሰከንድ ታገሱኝና ልግለጸው።

ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ የካህናቱን ጉባዔ በሊቀ ሊቀውንትነታቸው  በመሩት ውሳኔ እንዲህ እያሉ አቡነ ማትያስን ገስጸው ነበር ”ይህ የካቶሊክ እምነትና ትምህርት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ሲዘራ፤ ማህበራችን  ዝም ብሎ ማየት ስለማይገባውና ይህን የመሰለ ኑፋቄ ትምህርት በቤተ ክርስቲያናችን ሲነሳ  ለቤተ ክርስቲያን መቆም ግዴታው ስለሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በአስቼኳይ ውሳኔ እንዲሰጥበት” ካሉ በኌላ ሊቀ ሊቃውንት በመቀጠል  “ማህበረ ካህናቱ በወሰደው ርምጃ ተገቢውን ሃላፊነት ስለተወጣ ቢያስመሰግነው እንጅ አያስነቅፈውም”  እያሉ አቡነ ማትያስን ገስጸውና ነቅፈው ነበር።  

ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ  ቀጥለውም “ኧረ ለመሆኑ ከመቼ ወዲህ ነው ነገረ ሃይማኖት እንደ ቀበሌ ምርጫ ለህዝብ ቀርቦ በድምጽ ብልጫ መወሰን የተጀመረው?ነገረ ሃይማኖት ያልተረዱትን ምእመናን ሰብስቦ በነገረ ሃይማኖት ላይ ድምጽ ሰጡበት ማለት ተገቢ ነውን? በህገ ቤተ ክርስቲያን መሰረት በነገረ ሃይማኖት ጉዳይ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ አድርገው የቀድሞው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የጻፉትን መጻህፍት አገናዝበው ተገቢውን ውሳኔ ይሰጣሉ እንጅ እርሰዎ እንዳደረጉት እንደ ቀበሌ ምርጫ በዘፈቀደ የሚንጫጫበትና በድምጽ ብልጫ የሚወስኑት አይደለም። መልካም እንደሰራ ሰው ይህን  አሳፋሪ ድርጊት በጽሁፍዎ ማውጣተዎ ለሥልጣነዎ  እንጅ ለሃይማኖትና ለቤተ ክርስቲያን አለመቆመዎን ያመለክታል“ እያለ አቡነ ማትያስን ከፍ ዝቅ በማድረግ የማህበረ ካህናቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ በፊርማቸው  ባሰራጩበት ወቅት። ዶ ክተር አክሊሉ ለሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህን  ደጋግመው እያደነቁ፤ ጉባዔውንም እያመሰገኑ ተናግረው ነበር።

ታዲያ ዛሬ ዶክተር አክሊሉ ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህን ካቋማቸው አስለቅቀው የላቲኖችን ይማኖት እንቀበል እያለ ከሚሰብከው  ከርዕሰ ደብር አብርሃም ጋራ እንዲሰለፉ ማድረቸው  ግራ የሚያጋባ አይደለምን? ፍረዱ!   ከሊቀ ሊቃውንት ጋራ ያላቸውን አስተዛዛቢ ባህርይ ከጨረስኩ በኋላ በሊቀ ሊቃውንት ጀርባ አሳዝለው ብቅ ከዳደረጓቸው ሰዎች ጋራ ያሳዩትን አቋም በሀ፤ በለና በሐ ከፋፍየ ለማቅረብ እሞክራለሁ ወዳልኩት እሻገራለሁ።

ሀ፦ከዶክተር አክሊሉ ሐብቴ  ከአቶ አዲሱ አበበ  ጋራ

ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ከአቶ አዲሱ አበበ  ጋራ የተሳሰሩበትን ሰንሰለት ለመግለጽ እሞክራለሁ።  ሲመቻቸው  ፊት ለፊት፤  ሳይመቼው በጀርባ ሆነው  የሚካሄደውን እንቅስቃሴ በመግፋት  ላይ ያሉት አቶ አዲሱ አበበ ባንድ ወቅት የአቡነ ማትያስን እምነትና  ትምህርት ጉባዔው በተካሄደበት በርዕሰ አድባራት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ማሰራጩት  ጀመሩ። ከዚያ በፊት ቃል በቃል ተነጋግረን አናውቅም። አንተዋወቅም ማለት እችላለሁ። በዚያው በርዕሰ  አድባራት ቅድስት ማርያም በሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ በተመራው ጉባዔ የተወሰነውን የሚቃረን አቶ  አዲሱ አበበ ማስራጨታቸውን ስሰማ፤ ከዶክተር አክሊሉ ጀምሮ ባካባቢው ባሉት  በራሳቸው በሊቀ ሊቃውንት እያዘንኩ፤  አቶ አዲሱን  ስልክ ደውየ በጥሞና በትህትና ላነጋግራቸው ሞከርኩ። እርቅ የማይፈታው አይነት ጥላቻ በመካከላችን ያለን የመሰለ ኃይለ ቃል  ያዘለ ድምጽ ወረወሩብኝ። አያውቁኝ  አላውቃቸው ይህን የመሰለ የከረረ ጥላቻ እንዴት በኔ ላይ ሊኖራቸው ቻለ የሚል ያድናቆት ስሜት ተሰማኝ። አቶ አዲሱ የወነጨፉብኝ ቃል፤ አሁን ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር ምክንያት የባለ አደራው ቦርድ ባቀረበው መግለጫ ላይ፤  ስሙን  London  ብሎ፤ “says” እያለ የሚዘልፍ ግለ ሰብእ  October 12, 2015 at 9:57 am በጠለሰመው  ዘለፋ የበተነውን ነገረ ዘርቅ ይመስል ነበር። ይመስላል ያልኩት ነገረ ዘርቅም የሚከተለው ነው።

“በጣም ይቀርታ የአማርኛ ቀመራዊ ጽሑፍ በዘመናዊ መረጃ ሰርጭት ውስጥ ስላልዘረጋሁኝ፣ እስካሁን በእንግሊዘኛው ስጠቀም ቆቻለሁ“ ብሎ በጀመረው ዘለፋ፤  ዶክተር አማረን ዝቅ እኔ ከፍ ያደረግ አስመስሎ “አስተራየ እርግጥነው በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የደከመ ነው። ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ዕውቀት ሰጥቶ ማስተዋል የነሳው መግባባትና የመስማማት መንፈስ ፈሊጥና ጥበብ የተለየው በመሆኑ እነ አማረ በባዶ ምዕመናኑን አታለው ሲከብሩ እሱ ካገኘው ጋር ሲንጨረጨር ለቤተ ክርስቲያን ሳይጠቅም መንፈሳዊ ዕውቀቱን የስደብ ትርጉም እየሰጠ ጭንቅላቱን ይበጠብጣል” የሚል ነው።

ይህ አነጋገር አቶ አዲሱ ከጥቂት አመታት በፊት በስልክ ከነገሩኝ ጋራ ስለተቀራረበ፤ ያቶ አዲሱ ንግግር እንደሆነ ጠርጥሬአለሁ። ሊቀ ማእምራን ካሳየንና እኔን እያወዳደረ፤ እኔን ከፍ ሊቀ ማእምራን አማረን ዝቅ እያደረገ ያቀረበው ትችት እጅግ አሳዘነኝ። ይህ ግለ ሰብ እኔንም ሊቀ ማእማርን አማረን ፈጽሞ አያውቀንም።  ለትርጓሜ ትምህርት ደብረ ሊባኖስ እግሬ ሲረግጥ ሊቀ ማእምራን የሐዲሲ ኪዳን የመጨረሻውን ክፍል ከነ አባ ዓይነ ዓለም ከነ አባ ዘካርያስ ያሁን አቡነ ቀስጦስ ጋር ሲማሩ ነው የደረስኩት፤ የሚጠሉትን በሚጠሉት ጀርባ የመግደል ርኩስ ባህርይ ያለው ሰው ይህ ተናገረ እንጅ፤ እኔ ከዶክተር አማረ ብማር እንጅ፤ ዶ ክተር አማረ ከኔ የሚማሩት እንደሌለ ቢያውቅ ኖሮ ይህ ግለሰብ ይህን ባልተናገረ ነበር።

ያም ሆነ በዚህ መሳይ ንግግራቸው በጣም አዝኘ ለሊቀ ሊቃውንት አካፈልኳቸው፤ ሊቀ ሊቃውንትም ወርቅነህም ”እዚህ ናና እንነጋገራለን“ አሉኝ። እኔም ለዚህ ብየ  ከከንሳስ አልመጣም ለሊቀ ማእምራን አማረ ይንገሯቸውና በስልክ እንነጋገር አልኳቸው። እንግዲያስ አንተም ለሊቀ ማእምራን ነገረው፤  እኔም እነግረዋለሁ ብለውኝ  አቶ አዲሱን ጨምረው ለመነጋገር በቀጠሮ ተለያየን።

እኔና በወቅቱ የከንሳስ ቤተ ክርስቲያኑ ጸሀፊ የነበረው አቶ ወርቅነህ መዝገቡ ከንሳስ ሆነን፤ እራሳቸው ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ፤  ሊቀ ማእምራን አማረና አቶ አዲስ  አበበ ከዋሸንግተን ዲሲ ሆነው  ባደረግነው የስልክ ንግግር፤ አቶ  አዲሱ አበበ  ለብቻየ  የነገሩኝን የቁጣና የዘለፋ ቃል  ይቀይራሉ  ብየ ሳስብ፤  ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ፤  ሊቀ ማእምራምራን አማረና አቶ ወርቅነህ መዝገቡ እየሰሙ በቴሌፎን ለብቻየ ከተናገሩት ቀንሰውና  ከቁጣቸውም በረድ በልው የሚከተለውን ቃል ተናገሩ። ”አቡነ ማትያስ አይሳሳቱም፤  የሚሳሳተው አስተርአየ ነው። በነገራችን ላይ አቡነ ማትያስ  አባቴ ናቸው የሚናገሩትን ሁሉ አምናለሁ። እሱንም አውግዘውታልና፤ አንተ እልዋለሁ“ አሉ።

ሊቀ ሊቃውንት  ወርቅነህም ፤ አቶ አዲሱን “አንተ ደፋር በምን አቅምና ችሎታህ ነው? ምንስ ፈልገህ ነው? ቀሲስን  ዝቅ አቡነ ማትያስን ከፍ አድርገህ የምትናገር። የተሳሳቱት አቡነ ማትያስ እንጅ ቀሲስ አስተርአየ አይደለም። ይህንንም በጉባዔ አጣርተን ለሚመለከተው ሁሉ አቅርበነዋል። ሁሉም አፍሮና አፉን አፍኖ  የያዘውን ነገር አንተ ምን አግብቶህ ነው ከቀሲስ አስተርአየ ጋራ ቅስናውን  ገፈህ፤ አንተ እያልክ በመናገር ግብ ግብ የገጠምከው? ከቀሲስ አስተርአየ ጋራ የግል ችግር ካለህ መነጋገር ሲኖርብህ ነገረ መለኮት በተመለከተ ቀሲስንና አቡነ ማትያስን እያወዳደርክ ለመናገር  ድፍረቱን  ከየት አገኘኸው  አሁን ቀሲስ አስተርአየን ይቅርታ ጠይቅ”  ብለው  በቁጣ ስለተናገሩት ይቅርታ ጠይቆ፤ በአንዳንድ ጉዳዮች በስልክ መነጋገር የጀመርነው ከዚያ ወዲህ ነበር።

እንዲያውም በነ ሊቀ ማእምራንና በአባዛ መካከል በተፈጠረው የጸብ ግድግዳ ተለያይተው በመቅረታቸው፤ የሁለቱም የቅርብ ወዳጆች እነ ወይዘሮ  ውድነሽ  እያዘኑ ስለሚነግሩኝ ለምን አታስታርቁም አልኳቸው።  “አስታራቂ ሽማግሎችን ማስተባበር የሚችል ለሁለቱም ቀራቢ የሆነ ሰው ፈልግ” ብለውኝ አቶ አዲሱ ስለ አባ መአዛ  አባቴ እያሉ ስለሚነግሩኝ እሳቸው ቢሆኑስ  ምን ይመስለዎታል ስላቸው፤ በጣም ደስ ብሏቸው ነገረው ብለውኝ  ለአቶ አዲሱ ሳማክራቸው ለጊዜው ደስ ብላቸው ሀሳቡ ተቀበሉኝ። እኔም እውነት መስሎኝ እንግዲህ እርቅ ከተጀመረ በዚህ መቆም የለበትም። እነ አቶ  ቢልልኝ እና  ርዕሰ ድብርም ከቤተ ክርስቲያን ርቀዋል። ርእሰ ደብር አብርሃም የካዱትን አምነው፤ ስለ ሃይማኖቱ አበላሽተው የጻፉትን ለማረም ንስሀ ገብተው  ይቅርታ ከጠይቁ  አስታርቋቸውና ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው ይመለሱ፤ የኔ ስህተት ባይሆንም በጻፍኩት የጠቀስኳቸው አሉና  ይቅርታ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አልልም ብያቸው፤  እሽ ብለው ከተቀበሉኝ በኋላ፤ እንኳን ይህን ሁሉ ሊያደርጉ፤  እነ አባ መአዛን ለማስታረቅ አልፈለጉም። በመጨረሻ ከአባ መአዛ ጋራ እኔም ቅራኔ አለኝ ብለው እንዲያስታርቁ  ያገናኘኋቸውን ሰዎች አቶ አዲሱ በተኗቸው።

ከዚዚያ ወዲህ በተወገዘው አዲሱ ተክል ባቆመሱት ጉዳይ ያደረጉት ጨዋታ እጅግ አሳዝኖኝ  ሰይፈ ነበልባልን በሚል ርእስ ችግሩን የሚዳስስ ጦማር  አዘጋጀሁ። (ሙሉውን ለማንበብ የሚቀጥለውን ሰንሰለት በመጫን ይመልከቱ።  ሰይፈ ነበልባል ክርስትና እና ጋዜጠኝነት ሲወሀዱ ወደ ሰይፈ ነበልባልነት ይለወጣሉ)

ታዲያ ዶክተር አክሊሉ የሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህን አቋም አስቀይረው፤ የተዘበራረቀ ነገር በመፈጸም ላይ ካሉት ከአቶ አዲስ እና  ከርዕሰ ደብር አብርሃም ግራ እንዲቆሙ ማድረጋቸው ግራ አያጋባምን አሁን ዶ ክተር አክሊሉ ከርዕሰ ደብር አብርሃን ጋራ ወደ አሳዩት አቋም እሻገራለሁ።

ለ፦ዶክተር አክሊሉ ከርእሰ ደብር አብርሃም ጋራ፦   

ዶ ክተር አክሊሉ በዙሪያቸው ካሰለፏቸው አንዱ ርእሰ ደብር አብርሃም ናቸው። ሊቀ ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ስለ ቅድስት ድንግል እመቤታችን የተነሳውን ጉዳይ በሊቀ መንበርነት በሚመሩበት ወቅት፤ ርዕሰ ደብር አብርሃም የሳቸውን ቢጤዎች እነ ቄስ ኃይሉን ሰብስበው አቅማቸው ባማይፈቅድላቸው ንነገረ መለኮት  ውስጥ ገብተው አሉባልታ ማሰራጨታቸውን ከሰሙት ዲያቆናት መካከል ነገሩን።  እራሳቸው  ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ በርዕሰ ደብር አብርሃም በጣም  ተበሳጭተው ከሊቀ ማእምራን አማረ ቢሮ ድረስ እንዲመጡ ርእሰ ደብር አብርሃምን አስጠሯቸው።  

ርእሰ ደብር አብርሃምም ወደ ሊቀ ማእምራን ቢሮ መጡ።  ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ፤ ሊቀ ማእምራን  እና እኔን ተቀምጠን አገኙን። ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህና ሊቀ ማእምራን አማረ ርዕሰ ደብር አብርሃምን በዓያኖቻቸው ከመግረፍ በቀር ቢሮው ጸጥ አለ። አላስችለኝ አለኝና ርዕሰ ደብርን “የት የምታውቀውን ነው የምትዘባርቀው?” ብየ ተናገርኩ።  ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህም  “ልጄ እግዚአብሔር ይባርክህ ይህን ቀጣፊ አሳፈርክልኝ“ አሉ።  ከአምስት ዓመት በኋላ   ርዕሰ ደብር አብርሀሃም  ሰኔ 2002 ዓ ምህረት ”ማርያማዊ ሕገ ሃይማኖት“ በሚል ርእስ የኦርቶዶክስን  ተዋህዶ እምነትን የምታፈርስ  በአዚም የተሞላች ኩርባብች ጠለስሞ አቀረበ።  ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህን “ምነው የኔታ ራሰዎ ከሰሩት ጋራ በሚጋጭ ክህደትና ፤  በተበላሸ ምግባር  የከንሳስን ህዝበ ክርስቲያንን ሳይቀር ከፍና ዝቅ እያደረገ፤ የተዘበራረቀ አዚም ጠልሰሞ ያቀረበውን መርቀው ለህዝብ አቀረቡ?በዚህ ጠልሰም እኮ ርእሰ ደብር እጽፍ ድርብ በደል ፈጽሞበታል።

1ኛ፦ እምነቱን ማፍረሱ

2ኛ፦  ሊቃውንቱን ማዋረዱ

3ኛ፦  መሰረታውያን የሆኑትን መጻህፍት ማጣመሙ

4ኛ፦  የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ ማፋለሱ

5ኛ፦  ህዝቡን በራሱ ሃይማኖት እንዲዘምትበት ማድረጉ

6 ኛ፦ እንደገና ደግሞ  ክ1 እስከ 5 ተራ ቁጥር የተዘረዘሩትን ስህተቶችን የፈጸመበትን ጠልሰም ለሽያጭ አቅርቦ፤ ህዝበ ክርስቲያኑን ሊዘርፍበት መሞከሩን እያየንና እየሰማን ዝም ማለት ሁላችንንም በተለይ እራሰዎን ያስጠይቀዎታል አልኳቸው።

እሳቸውም ደንግጠው “እንዳይናችን ብሌን የምናያቸው ሊቅና ሽማግሌ ዶክተር አክሊሉ፤ የህግ ምኒስትር ሆኖ በደርግ ጊዜ ኢትዮጵያን ይመራ የነበረ አቶ ቢልልኝ፤ ሲያደንቁት ሰማሁ እንጅ መጽሐፉን አላየሁትም። በተጨማሪም የአቡነ ማቴዎስን  ፎቶ ተለጥፎበት   ታትሞ መጥቶ ሳየው ደስ አለኝ እንጅ ውስጡን ገልጭ አላየሁም። ከዚህ ቀደም እኛ አይተን ተስማምተን  በውሳኔ ባሳለፍነው  ነገረ መለኮት  ውስጥ ገብቶ  የሚያፈርስ ነገር እየተናገረ ከዘባረቀ መጽሐፉ መታገድ አለበት። ይህንም ለሊቀ ማእምራን አማረ እነግረዋለሁ። አንተም ንገረው፤  ስለ  መጽሐፉ ይዘት ዶ ክተር አክሊሉንና አቶ ቢልልኝ አናግራቸው” ብለውኝ፤  ለዶክተር አክሊሉ  በስልክ ከዚህ በታች የምጠቅሰውን ሀሳብ አቀረብኩላቸው።

   “ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ለመሩት ጉባዔ የአቡነ ጳውሎስን መጽሐፍ ተርጉመው ባቀረቡልን  ጊዜ፤  ከደጃዝማች ወልደ ሳማያት ጋር በልጅነታችሁ  የገጠማችሁን  ታሪካዊ ትዝታ  ጠቅሰው አቶ መለሰ የላቲኖችን  ፊደል  በኦሮሞዎች  ጭንቅላት ላይ፤  አባ ጳውሎስ የላቲኖችን  እምነት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ከሰከሱብን።  ዛሬ በህወት እያለን እግዚአብሔር ይህን ጉድ ያሳየን ምነው ምን በደልነው? ጣሊያንስ ከዚህ የከፋ ነገር ምን በደለን?“ ብለው ተናገረው  የአቡነ ጳውሎስንም ፎቶ ቀደውት ነበር።   ያን ጊዜ ያስቆጣወትን የተሳሳተ ትምህርትና እምነት የተሸከመውን  የላቲኖችችን እምነትና ምሳሌ እንቀበል እያለ የሚዘላብደውን  ርዕሰ ደብር ጠልሰሞ ያቀረበውን፤ እርሰዎና አቶ ቢልልኝ፤  ሊቀ ሊቃውንት መርቀውና ባርከው ለህዝብ እንዲያቀርቡት ለምን አደረጋችሁ? ብየ ጠየኳቸው።

ዶ ክተር አክሊሉ የሰጡኝ  መልስ፤  ”እኔና ቢልልኝ ስለነገረ መለኮት ምን እናውቃለን፡ ነገረ መለኮት እናውቃለን ብለው የተጎለቱትን ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህንና ሊቀ ማእምራን  አማረ ናቸው፤ በእኔ  በኩል ርዕሰ ደብር አብርሃም አዲስ አበባ ሄጄ፤ በሊቃውንቱ አስመርምሬ፤ በአቡነ ጳውሎስ  አስባርኬ  መጽሑፉን አሳትሜ እመጣለሁ ብሎ የገንዘብ ርዳታ ስለጠየቀኝ በገንዘብ ረድቸዋለሁ። አቶ ቢልልኝም  መጽሐፉን አርምልኝ ብሎ ስለጠየቀው አማረኛው መነበብ የማይችል፤ አቀራረቡ የተዘበራረቀ  ስለነበረ አዘጋጀለት እንጅ ስለ ነገረ መለኮት ይበላሽ አይበላሽ የሚውቀው ነገር የለውም።  ስለዚህ እኔና ቢልልኝን  አይመለከተንም” አሉኝ። ሊቀ ማእምራን አማረ ካሣየን ስጠይቅ፤  በያሬድ በዓል ላይ ዶክተር አክሊሉና አቶ ቢልልኝ አንተርሰው ሲያቀርበት ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፉን አየሁ እንጅ ከዚያ በፊት ስለ መጽሐፉ የማውቀው ነገር የለኝም“ አሉኝ።

የነበረኝ አማራጭ ራሳቸውን ርዕሰ ደብር  አብርሃምን ማናገር ነበር። ስልካቸውን ለማግኝት ሞከርኩ። ስልኩን ለማግኘት የጠየኩት ሁሉ “ከስድብ በቀር ከአብርሃም አፍ ቁም ነገር አይወጣምና ንቀህ ተወው”  የሚል ብቻ ሆነ። “አብርሃም   ስለሰደቡኝ  ዝቅ አልል፤ ስላከበሩኝ ከፍ አልልም ስልካቸውን  ፈልጉልኝ ብልም የሚሰጠኝ  አላገኘሁም።  ከርዕሰ ደብር ይልቅ፤  ነገሩን ሸፋፍነው  ለማለፍ በሞከሩት በነ ዶ ክተር አክሊሉ በጣም አዘንኩ።  

ከዚያ በኋላ ለዶክተር አክሊሉ ስልክ ደውየ “ ከኛ የራቁ የሚመስሉን ሰዎች ሲሳሳቱ መንቀፍ፤ ቅርብ ጔደኞቻችን ሲደግሙት ደግሞ ሸፋፍኖ መደገፍ ስህተት ነው። “አቶ መለሰ የላቲኖችን  ፊደል  በኦሮሞዎች  ላይ፤  አባ ጳውሎስ የላቲኖችን  እምነት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ  ከሰከሱብን።  ዛሬ በህወት እያለን እግዚአብሄር ይህን ጉድ ያሳየን ምነው ምን በደልነው ጣሊያንስ ከዚህ የከፋ ነገር ምን በደለንእያሉ የአቡነ ጳውሎስን ፎቶ እስከመቅደድ ያደረሰዎን ርዕሰ ደብር አብርሃም ሲያደርገው የምንደግፍ፤  ወይም ዝም ብለን የምናልፍ  ከሆነ ለሁላችንም፤ በተለይ ለእርሰዎ መልካም አይደለምና አስበውበት ይደውሉልኝ ብያቸው ተለያየን። ለሁለት ሳምንታት ከጠበኳቸው በኋላ የራሴን ድርሻ ለመወጣት ጠልሰም በዲሲ ደፍተራበሚል ርዕስ ሕዳር 2003  እና  የሰይጣን መፈክር በዋሸንግተን ዲሲ ቅድስት ማርያም ቤተ መቅደስ” በሚል ርዕስ ታህሳስ 2003 ጦማሮች አቅርቤ  በሰፊው ተነበበ።  

በነዚህ ጦማሮች ምክንያት የቤተ ክርስቲያናችን ገቢ ቀንሶብናል በማለት፤ ራሳቸው እነ ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ እንድከስስ መንቀሰቀሳቸውን ሰማሁ።  የምከሰስበት ምክንያት አቅፈው የያዙት ርዕሰ ደብር የጠለሰመው አዚም ስለሆነ ምን ማድረግ አለመቻላቸውን ተርደተው፤  የቀሲስ አስተርአየን ስም አታንሱ፤  ስለተጻፉትም ጦማሮች አታውሩ፤ እንዲያውም ጽሁፉን ስታገኙት እየቀደዳችሁ ጣሉት” በማለት  አለፉት። ታዲያ ይህ የነ ዶክተር አክሊሉ አቋም ግራ አያጋባም ሊል የሚደፍር ማነው ፍርዱን በወቅቱ ታዝባችሁ  ለነበራችሁ እየተውኩ፤ አሁን  ዶክተር አክሊሉ ከነ መጋቤ ሃይማኖት ተስፋየ እንቅስቃሴ ጋራ ያላቸውን አቋም  አንባቢ  በጥሞና እንዲመለከተው እማጸናለሁ።

ሐ፦ዶክተር አክሊሉ ከመጋቤ ሃይማኖት ተስፋዬ ጭፍራ ጋራ

መጋቤ ሃይማኖት ተስፋየን አላውቅም።  አብረን የተያየንባቸው ሁለት ቀናት ያውም ለጥቂት ሰአታት ነው። በሞንመንቱ  ስለተደረገው  ስብሰባ  ቅድመ ዝግጅት ላይ በተካሄደው ውይይት የሚናገረውን  በሰማሁበት ቅጽበት እንደ ቀትር እባብ ምላስ ተርገብጋቢ  ስሜት እንጅ፤ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሰረታዊ እውቀት እንደሌለው ተገነዘቤአለሁ።

የከንሳስ  ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የቅርብ ጓደኞቹ እንደሆኑ ሲነገር እሰማለሁ። እንዲያውም የክብር እንግዳ ሆኖ በመጋበዝ  ወደ መሰረትኳት ወደ ከንሳስ  ኪደነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን መጥቶ፤ በተርገብጋቢ ምላሱ ሰውን አርገብግቦት እንደተመለሰ ሰምቻለሁ።

በሞንመንቱ ጉባዔ ለተደረገው ቅድም ዝግጅት ስብሰባ ላይ መገኘቴ፤ መጋቤ ሃይማኖት  የሚለውን የክብር ቅጽል የተሸከመው ተስፋየ ፤ የስንት ሊቃውንት አባቶቻችን እናት ለሆነችው ለተማርኩባት ላደኩባት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መጋቤ ሃይማኖት ተብሎ መሰየሙ ቤተ ክርስቲያናችን ከማትወጣው አዘቅት እንደገባች  ተረዳሁ። ይህ ስው ስለ ሃይማኖትና ስለ  ፖለቲካ ብዙ የተዘበራረቀ ነገር ያወራል።  ገንዘብ ለማግኘት አቋራጭ መንገድ ፈላጊነቱን ብቻ እንጅ ስለሚያወራቸው ነገሮች ምንም ግንዛቤ እንደሌለው ተረድቻለሁ።

መጋቤ ሃይማኖትን እንድረዳው የረዳኝን ለመግለጽ ፈቃዳችሁ ይሁንና በማሳጠር ላቅርብላችሁ። በሞንመንቱ ላይ ለሚደረገው ጉባዔ በተደረገው ቅድመ ዝግጅት ስብሰባ ላይ በተገኘሁበት “በዝግጅቱ ላይ ወያኔ እንዳይነሳ አስጠነቀቀ። ከተነሳ ግን  ፖለቲካ ይሆናልና አልገኝም”  ብሎ ሁላችንንም ሽባ የሚያደርግ መንፈስ ረጭቶብን ቀጠሮ  አለኝ ብሎ ሊሄድ  ከመቀመጫው ብድግ አለ።   የረጨብንን አዚም መሳይ መንፈስ ረጭቶብን  ሳልጠይቀው እንዲሄድ ህሊናየ አልፈቀደልኝምና፤  “ከመሄድህ በፊት ጥያቄ አለኝ” ብየ የሚከተለውን ጠየኩት።

“ወያኔ የራሱን ፓትርያያርክ አላስቀመጠም አስቀምጧልስለው “አዎ አስቀምጧል” ብሎ መለሰ። የዋልድባን ገዳም ደፍሯል ወይስ አልደፈረምስለውም፤  “አዎ ደፍሯል“ ብሎ መለሰ። ሰውሳ እየገደለና እያሳደደ  ነው ወይስ አልገድልም አያሳድድም ብየ ስጠይቀውም፤  “አዎ  እየገደለና እያሳደደም ነው ” ብሎ መለሰ። ታዲያ ህገ ቤተ ክርስቲያንን ጥሶ የራሱን ፓትርያርክ መሰየሙን ካወክ፤  ሰው ማሳደዱንና  መግደሉን ካመንክና ገዳማት መድፈሩን ከተቀበልክ፤ የምታውቀውን መናገር እውነት መመስከር በለው እንጅ እንዴት  ፖለቲካ ነው ትላለህ? እንዲህ ያለውን ሀሳብ  ከየት ትምህርት ቤት ከማንስ መምህር ተማርክ?” ስለው፤ ሀሳቡን ቀየረና “ይህን ለማለት የፈለኩበት ምክንያት  እኔ ኢትዮጵያ እየተመላለስኩ የምሰራው ነገር ስላለኝ፤ ከወያኔ ጋራ እንዳያጋጨኝ ብየ ነው” የሚል መልስ ሰጠ።

እኔም “እውነቱን በመግለጽህ አመሰግንሀለሁ። ሁለተኛ ግን ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው ስለህዝባቸው ለመስራት ሲያስቡ አንተ ለግል እቅድህ  ስትል ይህን የመሰለ ደካማ ሽፋን አርገህ አትጠቀም። ኢትዮጵያ የምሰራው አለኝ ስለምትለው እቅድህ፤  ከገለጽክልንና ካመንበት እንረዳሀለን“ ብየው ሀሳቤን ተቀብሎ ከተስማማ  በኌላ፤  ሌላው የሱ ቢጤ ”የተሻለ ሀሳብ አለኝ“ ብሎ፤  ”አሁን ተስፋየ እንዳለው እሞኑመንቱ ላይ የወያኔን ስም ሳናነሳ ለተገደሉት ሰዎች ጸሎተ ፍትሀት ብቻ አድርገን እንለያይ። በሌላ ጊዜ ህዝቡ ወያኔን ሲቃወም ከኌላ ሆነን እንግፋ“ የሚል ሀሳብ አመጣ። እኔም አላስችለኝ  አለና “እናንተ ለመጨበት የፈራችሁትን እሳት በህዝብ እጅ ለመጨበጥ በኋላ ሆኖ  ህዝቡን መግፋትን  ከየት ነው  የተማራችሁት ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት አይደለም“ በማለት መለስኩለት።  

ከዚያ በኋላ “እንዲያውም የ40 ቀን ተዝካር ከአባ ፋኑኤል ጋራ ለማውጣት በመምህር ዘበነ ተጠርተናል” ብለው ወጡ። በሞንመንቱ ላይ መጋቤ ሃይማኖት ተስፋየ፤ ቄስ ሃይሉና የሰንበት ተማሪዎችን አላየናቸውም። ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ  በኢትዮጵያ የተለያዩ  ድርጅት የከፈቱ፤  ንብረት ያፈሩ፤ እንደነሱም ለመሆን የፈለጉ ሁሉ ከአባ ፋኑዔልና ካቆመሱት ታደስ ጋራ እየተገናኙ በሊቀ ማእምራን  አማረ እና አብረዋቸው በተሰለፉት ካህናት ላይ ጥላቻና ግፊያ እንዳበዙባቸው በግልጽ እየታየና እየተነገረ መጣ።

መጋቤ ሃይማኖት የኛን የማስተዋል አቅም እየፈተነ በራሱ ስሜትና እቅድ ሊያሸከረክረን የሞከረበትን መሰርይ ተግባር ይዞ፤  በቀላሉ ወደ ሚታለሉለትና ወደ ሚስማሙት ሰዎች ፊቱን አዞረ። እኛን ሊያታልለን ከሞከረና  ከፈተነን፤ እምነት እየፈለገ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣውን የዋሁን  ህዝብንማ  በለበሰው ልብስ፤  በጨበጠው መስቀል እራሱን ደብቆ  እንደቀትር እባብ ምላስ በተርገብጋቢ አንደበቱ  ወደፈለገበት  ቢነዳው ምን ያስደንቃል ምንስ ግራ ያጋባል?

የሚያስገርመውና ግራ የሚያገባውስ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  “ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ አደራም ከተሰጠው ሰውም አብዝተው ይሹበታል”ሉቃ 12፡48እንዳለው፤ ዛሬ በምድር ላይ ካለነው ኢትዮጵያውያን  ይልቅ፤ ክቡር አቶ ተክለ ጻድቅመኩሪያ  ”እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ   ከሕግ ውጭ በራሱ እርምጃ ፈንታውን ሌላውን ለማጥቃት ቢነሳ አጥፊዎች በተባሉት እግር ራሱ ተመልሶ ከመግባቱ በቀር የሚጠቅመው ነገር የለም። እርስ በርስ ከሚያጣላን ይልቅ የሚያፋቅረን መፈለጉ ጠቃሚ ነው። በዚህ ዓይነቱ የውስጥ ሁኔታና የእርስ በርስ ጠብ በ16ኛው መቶ  ዓ. ም ግራኝ አህመድ፤  በ20ኛው መቶ ዓ.ም  መሶሊኒ  ኢትዮጵያን ለማጥቃት ተጠቅመውበታል“ ብለው የተናሩትን፤  እግራቸው እስኪመለጥ ድረስ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ እየሄዱ ሰሚ እንኳ ቢያጡ “ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጭ የምድር መሰረቶችም ተናወጡ” እያሉ፤  ጮኸው የማሰማት ከዶክተር አክሊሉ  የበለጠ  እዳና ግዴታ  ያለበት ማንም አልነበረም። ይህን ግዴታና ሀላፊነት ከመወጣት ይልቅ፤ በማነኛውም መለኪያ ከሳቸው ጋር ከማይመጥኑ ሰዎች ጋር አቋማቸውን እየቀያየሩ መሰለፋቸው ሰውን ግራ አጋባው።

ይቀጥላል

አንቼ ጦማርእስካሁን በጻፍኳቸው ጦማሮች ለመጀመሪያ ጊዜ “ይበል” የሚለኝን የክቡር ሙሉ ጌታ ሉሌን ድምጽ ያጣሁብሽ በመሆንሽ፤ ከእጄ ስትወጭ በእንባ ከመሸኝት በቀር ሌላ ምን እልላለሁ