ለመርህ የቆሙ ጠንካራ እንጂ፣ በደመነፍስ የሚመሩና በጥላቻ የታወሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለፖለቲካው አይጠቅሙም፡፡


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ኢሕአዴግ ሥልጣን ይዞ የሽግግር መንግሥቱ ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ቁጥራቸው በጣም የበዛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመሥርተዋል፡፡ ኅብረ ብሔራዊና ብሔር ተኮር የሆኑት እነዚህ ፓርቲዎች ተመሥርተው ሥራ መጀመራቸው በበጎ ጎኑ የሚወሳ ቢሆንም፣ ለረጂም ጊዜያት የተስተዋሉባቸው ችግሮች ግን ሳይቀረፉ ቀጥለዋል፡፡ በምርጫ ጊዜ እንደ መስቀል ወፍ ብቅ የሚሉትን ትተን፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ጎላ ብለው የታዩትን በተመለከተ ስንነጋገር በርካታ ችግሮቻቸው እንዳሉ ናቸው፡፡ ኅብረት ሲመሠርቱ፣ ግንባር ሲፈጥሩ፣ ትብብር ሲሉ፣ ሲቀናጁ፣ ሲዋሀዱና ሲፈራርሱ ኖረዋል፡፡ በአስቸጋሪው ምኅዳር ውስጥ በርካታ ጫናዎችን ተቋቁመው ከማይጋፉት ባላጋራ ጋር ሲወድቁና ሲነሱ እዚህ የደረሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የመጡበትን መንገድ ሲገመግሙና መዋቅራዊ ለውጥ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡ ስህተቶችን በተደጋጋሚ በመሥራት አንዱ ከሌላው መማር አልቻሉም፡፡ በአባላቶቻቸውና በደጋፊዎቻቸው ከመመካት ይልቅ ውጭ ውጩን ሲያዩ የትም የቀሩ አሉ፡፡

ፖለቲካ ሰጥቶ የመቀበል መርህ መሆኑን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እያወቁ በተግባር ላይ ማዋል ያቃታቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ በተደጋጋሚ ከፈጸሙዋቸው ስህተቶች መማር አቅቷቸዋል፡፡ የፖለቲካው ዓውድ የሚፈልገውን ፖለቲካዊ ግንኙነት (Political Engagement) ከማደፍረስ በተጨማሪ፣ በጠራ ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተ ፕሮግራም መቅረፅ አልቻሉም፡፡ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ፖሊሲዎች ሲነድፉ አልታዩም፡፡ አባላትን በብዛትና በጥራት መመልመል አልቻሉም፡፡ ለመደራደር የሚያስፈልጉ ብልኃቶችንና ክህሎቶችን ያልተላበሱ በመሆናቸው፣ ከማይችሉት ባላጋራ ጋር እየተላተሙ የትም ወድቀው ቀርተዋል፡፡ የፈለገውን ያህል የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩ ይጥበብ ለዓላማቸው ስኬት ማንኛውንም መስዋዕትነት የሚከፍሉ የሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አላፈሩም፡፡ ይልቁንም የገዥውን ፓርቲ ስህተቶችና ግድፈቶችን በማነፍነፍ ብቻ በመጠመዳቸው የሠለጠነ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ማከናወን አቅቷቸዋል፡፡ የኢሕአዴግን ተቃዋሚዎች ከማንጠራራት የዘለለ የሰፊውን ሕዝብ ልብ ማግኘት አልቻሉም፡፡

እንዲህ ዓይነት ትችቶች መቅረብ ያለባቸው በሠለጠነና በተመቻቸ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ ለሚሠሩ ፓርቲዎች ነው የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ መነሳቱም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ የሚታወቁት ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቁ ችግራቸው ባላጋራቸውን ጠንቅቀው አለማወቃቸው ነው፡፡ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር በሚደረግ ሙግት አንድ አዳራሽ ውስጥ ቢገኙ፣ በአገሪቱ ሁለገብ ጉዳዮች ላይ ያላቸው አመለካከት አንድ ነው፡፡ ሁሉም በአንድነት ለክርክር ተዘጋጅተው የመጡ እስኪመስሉ ድረስ ገዥው ፓርቲ ላይ ይረባረባሉ፡፡ ለምሳሌ መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓ፣ መኢአድ፣ ወዘተ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ኢሕአዴግን አንድ ላይ ሲዘምቱበት አንድ ለመሆን ምን ያቅታቸዋል? በመካከላቸው ፈጥጦ የማይታየውን አብዛኛውን ልዩነት በማቻቻል ለምን አማካይ የሆነ ፕሮግራም ነድፈው አይዋሀዱም? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቁ ችግር የመርህ ነው፡፡ የሚተዳደሩት እንደ መሪዎቻቸው ፍላጎት ነው፡፡ ብዙዎቹ ቀለብ የሚሰፈርላቸው ከውጭ በመሆኑና በአባላትና በደጋፊዎች ላይ ስለማይተማመኑ ምርጫ ውስጥ የሚሳተፉት በተከፈለ ልብ ነው፡፡ ግንባር ለመፍጠርም ሆነ ለመዋሀድ እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ ደጅ ያሉት ‹‹አዛዦች›› ይሁንታ ከሌለበት ይከሽፋሉ፡፡ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን እውነታ መሠረት ያላደረገ ምስቅልቅል እንቅስቃሴ ይጀምሩና ሕዝቡን ግራ ያጋቡታል፡፡ ይኼ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የትኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም እንደሚያራምድ በግልጽ በማይታወቅበት አገር ውስጥ ሊበራል፣ ግራ ዘመም፣ ቀኝ ዘመም፣ ሶሻል ዴሞክራት፣ ወዘተ. ሲባል ቀልድ ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታና የአገሪቱን ሕዝብ ፍላጎት ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ እያቀረቡ፣ በርዕዮተ ዓለም አለመጣጣም አንድ መሆን አይቻልም ሲሉ ከቀልድም በላይ ነው፡፡ አሁን ያለው የተመሰቃቀለ አካሄድ ቆሞ በሰከነ መንገድ የሚመራ፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ቁርጠኛ የሆነ፣ አባላትንና ደጋፊዎችን አደራጅቶና አንቅቶ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራሱን ያላዘጋጀ ፓርቲ ባይኖር ይሻለዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዥውን ፓርቲ ጫና ይቋቋሙ ሲባል አጉል ምክር መሆን የለበትም፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ገዥውን ፓርቲ በመርህ ላይ ተመሥርቶ የሚወዳደር ጠንካራ ፓርቲ የግድ ይላል፡፡ ሁልጊዜም ለሕግ የበላይነት መቆም፣ ከሕገወጥ ተግባራት ራስን ማራቅ፣ ፖለቲካን የትርፍ ጊዜ ሥራ አለማድረግ፣ ወጣቶችን ለአመራር ማብቃትና በወሳኝ ቦታዎች መሰየም፣ ጊዜው የሚፈልገውን ሥልጡን ፖለቲካ ማራመድ፣ ከጥላቻና ከጽንፈኝነት ውስጥ መውጣት፣ ከሸፍጥና ካልተገባ ተግባር ራስን በማፅዳት በመርህ መመራት፣ ለዓላማቸው ፅኑ የሆኑ ጠንካራ አባላትን መመልመል፣ ከጠባብነትና ከቡድንተኝነት ፀድቶ ለብዙኃን እምነት መገዛት፣ ከፓርቲው ዓላማና መርህ ጋር ግጭት የሚፈጥር የውጭ ጣልቃ ገብነትን መከላከል፣ የሕዝብን ፍላጎት የሚወክሉ ፕሮግራሞችና የፖሊሲ አማራጮች መንደፍ፣ በሚያግባቡ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ጋር መመካከር፣ በፖሊሲ ጉዳዮች ተሳታፊ መሆን፣ ለብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ከሆኑ ተግባራት ራስን ማራቅና በአገር ጉዳይ ዋነኛ ተሳታፊ የሚሆን ጠንካራ ፓርቲ መምሥረት የወቅቱ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ ከአሁን በኋላ በደመነፍስ የሚመሩና በጥላቻ የታወሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለፖለቲካ ምኅዳሩ አይጠቅሙም፡፡ በምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የሚያኮራ ውጤት የሚያስመዘግብ እንጂ፣ ልፍስፍስ ተቃዋሚ ፓርቲ ለማንም አይጠቅምም፡፡ አዲሱ ትውልድም ገፍቶ መጠየቅ ያለበት ለመርህ የቆመ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እንጂ፣ በገጠመኝ የሚኖር ምስኪን አይደለም፡፡