ኤርትራ የተጣለባት ፍትሐዊ ያልሆነ ማዕቀብ እንዲነሳላት ተማፀነች ::
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
የፀጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 2009 በኤርትራ መንግሥት ላይ ከጣለው የጦር መሣሪያ ማዕቀብ ማለትም የፖለቲካ መሪዎችና ወታደራዊ አመራሮች ሀብት እንዳይንቀሳቀስ፣ እንዲሁም በእነዚህ አመራሮች ላይ ከጉዞ ማዕቀብ ውጪ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን በዲሴምበር 2011 ላይ ጥሏል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ግፊት በኢጋድ በኩል የቀረበ ሲሆን፣ በተለይ አገሪቱ ከማዕድን ዘርፍ የምታገኘው ገቢ የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና ሰላም ለማወክ እየተጠቀመችበት በመሆኑ ማዕቀብ እንዲያርፍበት ተጠይቆ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን ከሚያገኙት ገቢ ሁለት በመቶ በመቀነስ ወደ አገር ቤት የሚልኩት እንዳይተላለፍ የሚያደርግ ነው፡፡
ማዕቀቡ ከተጣለ ከአራት ዓመታት በኋላ ኤርትራ በኢኮኖሚ ማዕቀቡ የተዳከመች ትመስላለች፡፡ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ጉዳይ ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት በጠራው መደበኛ ያልሆነ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት፣ በተመድ የኤርትራ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ግርማ አስመሮም ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው፡፡ በውጭ ከሚኖሩ ኤርትራውያን ዓመታዊ ገቢ ሁለት በመቶ ተሰብስቦ የሚውለው በጦርነት ለተሰው ዜጎች ቤተሰቦችና የጦር ጉዳተኞችን ለመደገፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አምባሳደር ግርማ በውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን በዓመት የሚልኩት 11 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ አጠቃላይ የኤርትራ መንግሥት የሚያወጣው ግን ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይ የፀጥታው ምክር ቤት ሊገነዘበው የሚገባው ኤርትራ ከማዕድን የምታገኘውን ገቢ በፍፁም ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ውጪ (ማለትም ለእኩይ ዓላማ) አውላ እንደማታውቅ፣ አምባሳደር ግርማ ለምክር ቤቱ የማዕቀብ ኮሚቴ አሳውቀዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ዓመታዊ በጀት ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነውን የሚያገኘው ከማዕድን ዘርፍ መሆኑን በመጥቀስ፣ የማዕቀቡ መነሳት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን አወንታዊ ተፅዕኖ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ‹‹ማንኛውም የዓለማችን አገርና ሕዝብ ወደኋላ ሊተው አይገባም›› የሚለውን ተመድ በቅርቡ ያፀደቀውን ድኅረ 2015 የልማት ግቦች ያስታወሱት አምባሳደር ግርማ፣ በኤርትራ ላይ በተጣለው ፍትሐዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ምክንያት የኤርትራ መንግሥትና ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ በኤርትራ ላይ የተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ በተመድ ከተያዘው የድህነት ቅነሳ አጀንዳ ውጪ በመሆኑ፣ ይህንን ፍትሐዊ ያልሆነ ማዕቀብ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡ አምባሳደር ግርማ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ ለመጣል ምክንያት የሆኑት ኤርትራ በሶማሊያ የሚገኘውን አልሸባብ የሽብር ቡድን ትረዳ ነበር መባሉ፣ እንደሁም በኤርትራና በጂቡቲ መካከል በተነሳው የድንበር ግጭት ሰበቦች መሆናቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኤርትራ አልሸባብን እንደምትረዳ ቀደም ባለው የፀጥታው ምክር ቤት የሶማሊያና የኤርትራ አጣሪ ቡድን ሪፖርት ማረጋገጥ አለመቻሉን ቡድኑ ራሱ መጥቀሱን እንዲሁም በቅርቡ ባደረገው ምርመራም ምንም ዓይነት ማስረጃ አለማግኘቱን ራሱ መግለጹን ለፀጥታው ምክር ቤት የማዕቀብ ኮሚቴ አስረድተዋል፡፡ ሌላኛው የማዕቀቡ ምክንያት በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የተነሳው የድንበር ውዝግብ በጭራሽ ከአካባቢውም ሆነ ከዓለም ፀጥታ መደፍረስ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ የሰጡት ምክንያትም የግጭቱ መጠን ይህንን ያህል የሚያሳስብ ባለመሆኑ፣ ሁለተኛ ደግሞ ራሱ የፀጥታው ምክር ቤት ባፀደቀው መሠረት የኳታሩ ኤሚር የማግባባት ሥራውን እያከናወኑ መሆናቸውን፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የኳታር 200 ወታደሮች በአካባቢው መሰማራታቸውን በማውሳት፣ የማዕቀቡ ምክንያቶች በአሁኑ ወቅት ትርጉም የሌላቸው መሆናቸውን ተከራክረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፀጥታው ምክር ቤት ያቋቋመው የሶማሊያና የኤርትራ አጣሪ ቡድን ገለልተኝነትን ተችተዋል፡፡ የሶማሊያና የኤርትራ አጣሪ ቡድን ሐሰተኛ የፈጠራ መረጃዎችን በመጠቀም ሪፖርቱን እንደሚያጠናክር፣ ለዚህም እንደማሳያነት መረጃዎችን ከኢትዮጵያና ከጂቡቲ እንደሚቀበል አምባሳደር ግርማ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አንድ ሰው ከእነዚህ ከኤርትራ ጋር ግጭት ካላቸው ኢትዮጵያና ጂቡቲ እንዴት እውነተኛ መረጃ ይጠብቃል?›› ሲሉ ተችተዋል፡፡
አጣሪ ቡድኑ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ለፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ይግባኝ ብትልም፣ ችግሩ ሊቀረፍ አለመቻሉን አምባሳደሩ ለኮሚቴው አስረድተዋል፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ በየመን ካለው የፀጥታ ሁኔታ ጋር ያላትን ግንኙነት መገምገም እንደሚፈልግ፣ ከዚህ በማለፍ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስላልተፈታው የድንበር ውዝግብና በኤርትራ አጠቃላይ ውስጣዊ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ሥልጣኑ እየገባ ነው ሲሉ አምባሳደሩ ይከሳሉ፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ጉዳይ የተወራሪና የወራሪ ጉዳይ ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር እንደምትገደድ እየገለጸች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በማስረጃነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም እ.ኤ.አ. ጁላይ 7 ቀን 2015 ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወታደራዊ ዕርምጃ በኤርትራ ላይ ልትወስድ ትችላለች›› ማለታቸውን በማስታወስ፣ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ይህንን የኢትዮጵያን ዛቻ በቸልታ ማለፍ ሳይሆን ሊያወግዘው ይገባል ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የሰጡት ምክንያትም በአንድ አገር ላይ ወታደራዊ ኃይል የመጠቀም ወይም ለመጠቀም መዛት የተመድ ቻርተርን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ እንደሆነ ነው፡፡