የምርመራ ጋዜጠኝነት እና ልማታዊ ጋዜጠኝነት እንዲሁም እኛ! (የትነበርክ ታደለ)
የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ።
ባለፉት ሁለትና ሶስት ሳምንታት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስለ ምርመራ ጋዜጠኝነት ሲያወራ የሰማሁ ይመስለኛል። ስለ ልማታዊ ጋዜጠኝነትማ ጆሮዋችን ሞልቶ እስኪያፈስ ነግሮናል። ለመሆኑ እነዚህ ሁለት ጋዜጠኝነቶች ምንድናቸው?
እኛ ሀገር ስለ ምርመራ ጋዜጠኝነት ማውራት በራሱ የሚቻል አይደለም። የምርመራ ጋዜጠኝነት እንደ ቃሉ ምርምር ነው። ጋዜጠኛው አንድ አሳሳቢ ጉዳይን ይዞ ውስጥ ድረስ ዘልቆ የሚያጠናበት ወንጀል፣ የፖለቲካ ሙሰኝነት፣ የመንግስት ጥፋት እና ተመሳሳይ ነገሮችን ከመረጃ ጋር ወደ ህዝብ የሚያቀርብበት አንድ መስክ ነው።
አንድ ፋብሪካ እንዴት ተሰራ? ማን ሰራው? ምን ሰራ ማለት የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራ አይደለም። ወይም ድልድይ ተገነባ ቦይ ተቆፈረ ምናምን የሚሉ ዜናዎች ምንም አይነት ምርምር የሚጠይቁ አይደሉም። የምርመራ ጋዜጠኛ አነፍንፎ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች ብዙ ጊዜ ለፖሊስና ለፍርድ ቤት እንደ ግብአት የሚያገለግሉ መረጃዎች ናቸው።
አላማው ማህበረሰቡ ፊት ለፊት ያማያያቸውና አተኩሮ የማይገነዘባቸውን ጭብጦች አደባባይ ማምጣት ነው። ይህ በመንግስት ብቻም ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ወይም በቡድን ተደራጅተው ወንጀል የሚሰሩና ማህበራዊ ደንብን የሚጥሱ ሁሉ የሚጋለጡበት ነው።
ለምሳሌ በህጋዊ ሆስፒታሎች ተቀጥረው ሀኪሞች እንዴት ነው ህገ ወጥ ፅንስ በገንዘብ የሚያስወርዱት? እንዴት አድርገው ነው ከግል የህክምና ተቋማት ጋር ውስጥ ለውስጥ የመንግስትን ቁሳሳቁስ የሚጠቀሙት? ጊዜ ያለፈባቸው መድሀኒቶችና ምግቦች በምን አይነት ጥበብ ነው የህግ አይን ሳያያቸው ወደ ገበያ ገብተው የህዝብን ጤንነት የሚበክሉት?……አደንዛዥ እጾችን እነማን ናቸው ወደ ሀገር ቤት የሚያስገቡት? እንዴት ነው የሚያስገቡት? ወዘተ!
አሁን እንዲህ አይነት ጋዜጠኝነት በሀገራችን አለ? የቱ ደፋር ጋዜጠኛ ነው አንድን ባለስልጣን አድኖ እንዴት አድርጎ በሙስና ሀብት ንብረት እንዳፈራ የሚመራመር? ማን ደፋር ነው መንግስት አውቆም ይሁን በስህተት የሰራቸውን ጥፋቶች ከነማስረጃው ወደ ህዝብ የሚያቀርብ?…..ወጉን እንተወውና ወደ ሁለተኛው ርእስ እንሂድ!
በኛ ሀገር ልማታዊ ጋዜጠኝነት ማለት በተደጋጋሚ እንደሚነገረው ስለ ልማት ብቻ መዘገብ ነው። ተቆፈረ፣ ታረሰ፣ ተዘራ፣ ታጨደ፣ ተበላ አለቀ። ከዚህ ውጭ መዘገብ ጸረ ልማታዊ ጋዜጠኛ ያስብላል።
እስኪ አስቡት! ማንኛውም ስራ በተፈጥሮው አብሮት የሚሄድ ጠንካራም ደካማም ጎን አለው። ሰው የሚሰራው ነገር ደግሞ መቶ ፐርሰንት ንጹህ አይሆንም። እናም ትክክለኛው የልማታዊ ጋዜጠኝነትም የሚፈለገው ለዚህ ነው።
በስራ ወቅት ምን ተረሳ? ለምን ተረሳ? ምን ችግር ተፈጠረ? ምን መፍትሄ ያስፈልጋል? ቀጣይ ምን መደረግ አለበት?….ወዘተ እያለ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት ነው ልማታዊ ጋዜጠኝነት። በልማት ዙርያ ያሉ ህጸጾች እንዲታረሙ መረጃ ማቀበል ነው ስራው። እንጂ አንድን ስራ ማስሞገስና ማስወደስ አልነበረም።
ለማንኛውም ቁም ነገሩ እንደዝያ ነው! እናም የምርመራ ጋዜጠኝነት እና ልማታዊ ጋዜጠኝነትን የፈቀድን እለት በእውነት ሀገር አስር እርምጃ ወደፊት ሄዳለች ብለን በኩራት መናገር እንችላለን። ግን ያ ቀን መቼ ነው?